ጋዜጣዊ መግለጫ ጋዜጣዊ መግለጫ 

በታዳጊ ሕጻናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለመከላከል ተጨባጭ ሥራዎች እንደሚሰሩ ተገለጸ።

በታዳጊ ሕጻናት እና አቅመ ደካማ በሆኑ ሰዎች ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን ለመከላከል ሕጋዊ መንገዶችን የሚያቀርብ፣ ክህሎት ያለውን የሰው ሃይልን ማደራጀት የሚሉ እንደሚገኙበት ክቡር አባ ፌደሪኮ ሎምባርዲ ገልጸዋል። በተጨማሪም አስተባባሪ ኮሚቴው በቅድስት መንበር ከሚገኙ የተለያዩ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች ጠቅላይ ጸሐፊዎች ጋር በመሰብሰብ በሚቀጥሉት ጊዜያት ምን ማድረግ ያስፈልጋል በሚለው ጥያቄ እንደሚወያይ እና እንደሚመክር አባ ፌደሪኮ ሎምባርዲ ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በታዳጊ ሕጻናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለመከላከል የሚያስችሉ ውጤታማ መንገዶች ለማግኘት በቫቲካን ከተማ ከየካቲት 14 ቀን እስከ የካቲት 17 ቀን 2011 ዓ. ም. ሲካሄድ የቆየው ስብሰባ ተጨባጭ የሆኑ ሥራዎችን ለማከናወን መወሰኑን በመገለጫው አስታውቋል። ስብሰባው በተካሄደባቸው አራት ቀናት ውስጥ አራት ጋዜጣዊ መግለጫዎች መቅረባቸው ታውቋል። በእያንዳንዱ የስብሰባው ቀን ማጠቃለያ ላይ በስብሰባው የተደረጉት ውይይቶች ጭብጦች የቀረቡ ሲሆን ይህም ጋዜጠኞች ጥያቄዎችን እና መልሶቻቸውን ማዳመጥ እንዲችሉ ጥሩ አጋጣሚን እንደፈጠረላቸው ከቫቲካን የዜና አገልጎሎት የደረሰን ዘገባ አመልክቷል። ትናንት እሁድ የካቲት 17 ቀን 2011 ዓ. ም. የቀረበው የመጨረሻ ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳብራራው፣ መላው ዓለም በጉጉት የሚጠብቀውን እና ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በስብሰባው መጀመሪያ እለት እንዳሳሰቡት ሁሉ ቤተክርስቲያን በታዳጊ ሕጻናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለመከላከል የሚያችሉ ተጨባጭ ሥራዎችን ለመስራት መወሰኗን ገልጿል።

ትናንት እሁድ የቀረበውን ጋዜጣዊ መግለጫ ያስተባበሩት ክቡር አባ ፌደሪኮ ሎምባርዲ፣ ቤተክርስቲያን በታዳጊ ሕጻናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለመከላከል የሚያግዙ መንገዶች ሦስት መሆናቸውን አስታውቀዋል። ከእነዚህም መካከል የመጀመሪያው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የግል ውሳኔዎችን ለማስተላለፍ የሚያስችላቸውን ሐዋርያዊ ስልጣን ተጠቅመው ከቫቲካን መንግሥት ይፋ የሚያደርጓቸው ሕጎች እና ደንቦች እንዳሏቸው፣ ሁለተኛ በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ሕጋዊ የሐዋርያዊ አገልግሎት ሥራን እና ሃላፊነትን የሚያብራራ እና የሚገልጽ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያወጧቸው ሕጎች እና ደንቦች እትም እንደሚደርሳቸው፣ ሦስተኛ በዓለም ዙሪያ የሚገኙትን የካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎችን የሚያግዙ፣ በታዳጊ ሕጻናት እና አቅመ ደካማ በሆኑ ሰዎች ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን ለመከላከል ሕጋዊ መንገዶችን የሚያቀርብ፣ ክህሎት ያለውን የሰው ሃይልን ማደራጀት የሚሉ እንደሚገኙበት ክቡር አባ ፌደሪኮ ሎምባርዲ ገልጸዋል። በተጨማሪም አስተባባሪ ኮሚቴው በቅድስት መንበር ከሚገኙ የተለያዩ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች ጠቅላይ ጸሐፊዎች ጋር በመሰብሰብ በሚቀጥሉት ጊዜያት ምን ማድረግ ያስፈልጋል በሚለው ጥያቄ እንደሚወያይ እና እንደሚመክር አባ ፌደሪኮ ሎምባርዲ ገልጸዋል።

በስብሰባው ወቅት የብዙሃን መገናኛዎች ሚና፣

ስብሰባው በተከናወነባቸው አራት ቀናት ውስጥ የስብሰባውን ሂደት እንዲከታተሉ ለብዙሃን መገናኛ አውታሮች ሰፊ ዕድል ተሰጥቶ እንደነበር ታውቋል። የቫቲካን የመገናኛ ጽሕፈት ቤት ዳይሬክተር የሆኑት ክቡር አቶ ፓውሎ ሩፊኒ እንደገለጹት የተሰጣቸውን ዕድል ተጠቅመው የስብሰባውን ሂደት፣ የተነሱትን ጥያቄዎችን እና አስተያየቶችን በዜና ማሰራጫዎቻቸው ለዓለም ይፋ በማድረግ የተባበሩትን የዜና አውታሮችን በሙሉ አመስግነዋቸዋል። የጋዜጠኞች ቀዳሚ ተግባር በእውነት ላይ የተመሠረተ ዘገባን ማቅረብ እንደሆነ ገልጸው ቶሎ ብለው ፍርድን ከመስጠት ይልቅ በሚገባ ካዳመጡ በኋላ ያገኙትን መረጃ ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ ገልጸው መደማመጥ ሳይኖር ቀርቶ ሁሉም የሚናገር ከሆነ ትክክለኛ መረጃን መለዋወጥ አይቻልም ብለዋል። አቶ ሩፊኒ ጋዜጣዊ መግለጫውን የተካፈሉትን በሙሉ አመስግነው ሜክስካዊ ጋዜጠኛ ቫለንቲና አላዝራክ ለሰጠችው ገንቢ አስተያየቷ ምስጋናቸውን አቅርበውላታል። ጋዜጣዊ መግለጫውን የተካፈለችው ጋዜጠኛ ቫለንቲና አላዝራክን በበኩሏ በታዳጊ ሕጻናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን በተመለከተ በጋራ መሥራት እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ገልጻ ብጹዓን ጳጳሳት ከጋዜጠኞች ለሚቀርብላቸው ጥያቄዎች መልስ እና አስተያየት ከመስጠት መቆጠብ የለባቸውም ብላለች።

በሕንድ የቦምቤይ ከተማ ሊቀ ጳጳሳት የሆኑት ካርዲናል ኦስቫልድ ግራሲያስ በበኩላቸው ስብሰባው ጠቃሚ እና አስፈላጊ እንደነበር፣ ስብሰባውን የተካፈሉ ብጹዓን ጳጳሳት ጠቅላላ ግንዛቤን እንዳገኙ፣ ቤተክርስቲያንን ካጋጠማት ችግሮች መካከል ለታዳጊ ሕጻናት ጥቃት ቅድሚያን በመስጠት መጸጸት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።         

በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የኢየሱሳዊያን ማሕበር አባል እና የስብሰባው አዘጋጅ ኮሚቴ አባል የሆኑት ክቡር አባ ሃንስ ዞልነር በሚቀጥሉት ዓመታት ውስጥ ችግሩን በተመለከተ ሰፊ ጥናት እና አሰሳ እንደሚደረግ አስታውቀው አሁን ከስብሰባው የተገኙ ሃሳቦችን እና መንገዶችን በመጠቀም፣ የተነሱትን ጥያቄዎች እና የተሰጡትን መልሶች በማስታወስ ብዙ መሥራት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። 

25 February 2019, 16:31