ብጹዕ ካርዲናል ኩርት ኮክ፣ ብጹዕ ካርዲናል ኩርት ኮክ፣  

ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ከሩሲያ ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ጋር ለሰው ልጅ ሕይወት ጥበቃ በጋራ ይሠራሉ

በቅድስት መንበር የክርስቲያኖችን ሕብረት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት ፕሬዚደንት የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ኩርት ኮክ፣ በሁለቱ ቤተክርስቲያኖች መካከል አዲስ የውይይት ርዕሥ እንዲጀመር በመደረጉ የሞስኮ ከተማ ሊቀ ጳጳስ እና ከፍተኛ የነገረ መለኮት ተቋም ዳይሬክተር የሆኑትን ብጹዕ አቡነ ሂላሪዮን አመስግነዋቸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ፖትሪያርክ ብጹዕ ወ ቅዱስ አቡነ ኪሪል ጋር በ2008 ዓ. ም. በኩባ ዋና ከተማ ሃቫና ላይ ተገናኝተው ያደረጉትን ስምምነት ተከትሎ ሁለቱ ቤተክርስቲያኖች ለሰው ልጅ ሕይወት ጥበቃ በጋራ እንደሚሰሩ ትናንት በሞስኮ የተገኙት ካርዲናል ኮክ እና ብጹዕ አቡነ ፓሊያ ገልጸዋል።

የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ከፍተኛ ልኡካን ከኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን አባቶች ጋር ሲገናኙ ይህ ለሦስተኛ ጊዜ ሲሆን ከዚህ በፊት በ2009 ዓ. ም. በፍሪቡሮጎ ጀርመን፣ ቀጥለውም በ2010 ዓ. ም. በቬና አውስትሪያ መገናኘታቸው ይታወሳል። ዘንድሮ በሞስኮ ሲገናኙ የሚወያዩበት ርዕሥ “የሰው ልጅ ሕይወት ማብቂያ” በሚመለከት እንደሆነ ታውቋል። ስብሰባቸውን ሞስኮ በሚገኘው የቅዱስ ኪሪል እና ሜቶዲዮስ የነገረ መለኮት ከፍተኛ የትምህርት ማዕከል እንደሚያደርጉ ለማወቅ ተችሏል። በቅድስት መንበር የክርስቲያኖችን ሕብረት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት ፕሬዚደንት የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ኩርት ኮክ፣ በሁለቱ ቤተክርስቲያኖች መካከል አዲስ የውይይት ርዕሥ እንዲጀመር በመደረጉ የሞስኮ ከተማ ሊቀ ጳጳስ እና ከፍተኛ የነገረ መለኮት ተቋም ዳይሬክተር የሆኑትን ብጹዕ አቡነ ሂላሪዮን አመስግነዋቸዋል። ከዚህም ጋር በማያያዝ በሩሲያ ወደሚገኙ ሁለት ታላላቅ ከተሞች መፈሳዊ ጉዞን በማድረግ በክብር የተቀመጠውን የቅዱስ ኒኮላ ቅዱስ አጽም በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ ክርስቲያኖች እንደጎበኙት አስታውሰው የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን ባለፈው የነሐሴ ወር ላይ ወደ ሩሲያ በመሄድ በበጋ ወራት በተዘጋጀው እና በሁለቱ ቤተክርስቲያኖች መካከል ያለውን የእርስ በርስ ትውውቅ ለማዳበር እንዲያግዝ ተስቦ በተዘጋጀው የወጣት ካህናት ስልጠና ላይ መገኘታቸውንም አስታውሰዋል።

የሰው ልጅ ሕይወት ማብቂያን በተመለከተ፣

በቅድስት መንበር የክርስቲያኖችን ሕብረት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት ፕሬዚደንት የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ኩርት ኮክ ንግግራቸውን በመቀጠል፣ ከፍጥረታት መካከል ስለ ራሱ ነፍስ ትርጉም እና የሕይወቱን ማብቂያ የሚያውቅ የሰው ልጅ ብቻ እንደሆነ አስረድተው ብጹዕነታቸው ዘመናችን ያስገኘውን እና በነገረ መለኮት አካሄድም የሕክምናው ዘርፍ የደረሰበት ደረጃ አስታውሰው የሰው ልጅ ስቃይ ለክርስቲያን ምን ትርጉም እንደሚሰጥ በመገንዘብ፣ ምንም እንኳን በሕመም ላይ ቢገኝም ለሰው ልጅ ሕይወት የሚሰጠውን ክብር ማወቅ፣ ለሰውነቱም የሚሰጠውን እንክብካቤን አለመዘናጋት ለሰው ልጆች ከሚደረጉት ሁለ ገብ ሐዋርያዊ አገልግሎቶች መካከል አንዱ እንደሆነ አስረድተዋል።

በሰው ልጅ ሕይወት ማብቂያ የቤተክርስቲያን አቋም፣  

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛ በ1949 ዓ. ም. በሮም ለተሰበሰቡት 500 ለሚሆኑ የሕክምና ባለሞያዎች ያደረጉትን ንግግር ያስታወሱት፣ በቅድስት መንበር የክርስቲያኖችን ሕብረት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት ፕሬዚደንት የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ኩርት ኮክ፣ ለሕሙማን በሚደረግ እንክብካቤ መካከል የሕመም ማስታገሻ የሕክምና አገልግሎትን የሚደግፍ ሕግ ቅዱስነታቸው ማጽደቃቸውን አስታውሰዋል።

ዓለም አቀፋዊነት ያለ ክርስትና እሴቶች ከሆነ ፍቅር ይጎድለዋል፣

በሮም የጳጳሳዊ አካዳሚ ፕሬዚደንት የሆኑት ብጹዕ አቡነ ፓሊያ በበኩላቸው ዓለም አቀፋዊ አንድነት ክርስትናዊ እሴቶች ካልታከሉበት ፍቅር እንደሚጎድለው አስረድተው የክርስትናው ዓለምም በሰዎች መካከል እየጎደለ የመጣውን ፍቅር መልሶ ለመገንባት በሰዎች መካከል ጠንካራ ግንኙነቶችን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ለሰው ልጅ እንክብካቤን ማድረግ ማለት ቅዱስ ወንጌል እንደሚያስተምረን ሌሎችን ማፍቀር ማለት እንደሆነ አስረድተዋል። ለሰው ልጅ ሕይወት የሚያስፈልገውን ፍቅር እና እንክብካቤን ማድረግ የሚያሳስብ ሐዋርያዊ መልዕክት በሩሲያ ቋንቋ ተተርጉሞ መቅረቡንም አስታውሰዋል። በሕክምና እገዛ የሰው ነፍስ ከስጋው እንዲለይ ሲደረግ ወይም በግልጽ ቋንቋ የሰው ልጅ እንዲሞት ሲደረግ ብቻውን እንደማይሞት፣ ነገር ግን ሌሎችም የቤተሰብ ክፍሎች እንዲጎዱ ወይም እንዲሞቱ ማድረግ ስለሆነ ጉዳቱ የከፋ ይሆናል ብለዋል።

የክርስትና እምነት ለሰው ልጅ ሕይወት ክብር እንዲሰጠው ጥረት ማድረግን ያስተምራል፣

የጳጳሳዊ አካዳሚ ፕሬዚደንት የሆኑት ብጹዕ አቡነ ፓሊያ በንግግራቸው መጨረሻ፣ የነፍስ እና የስጋ ፈዋሽ የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሕይወት በፍቅር የታገዘ እንክብካቤን ለመስጠት የሚያስችለንን ጸጋ ይስጠን በማለት ንግግራቸውን ፈጽመዋል።       

13 February 2019, 15:40