ካርዲናል ቤቹ በሕዝብ መካከል ፍርሃት የሚወገደው የግንኙነት ባሕልን በማዳበር እንደሆነ አስታወቁ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የሕይወት ትርጉም ቀውስ ገጥሞታል፣ ሕዝቦችም በያሉበት በፍርሃት ተውጠዋል ያሉት ካርዲናል ጆቫኒ አንጀሎ ቤቹ፣ የሕዝቡን ፍርሃት ማስወገድ የሚቻለው በሰዎች መካከል የእርስ በርስ ግንኙነት ባሕልን በማዳበር እንደሆነ አስረድተው ስደትን አስመልክቶ የሚነሱ ጥያቄዎችን መመልከት የሚቻለው አፍሪቃ ውስጥ እንደሆነ ገልጸዋል።

ዓለማችን በሕዝብ ቁጥር እየሰፋ መጥቷል፣ ይህን ለመቆጣጠር መንግሥታት ሃላፊነታቸውን በውል ሲወጡት አይታይም፣ በመሆኑም በሕዝቦች መካከል ፍርሃት ነግሷል ያሉት ካርዲናል ጆቫኒ አንጀሎ ቤቹ፣ በሕዝቦች መካከል የሚታየው ፍርሃት በአጠገቡ ካለው ጋር ብቻ ሳይሆን ከሩቅ አካባቢ ከሚመጡትም ጋር እንደሆነ አስረድተዋል። በቅድስት መንበር ስለ ቅዱሳን ሕይወት የሚያጠና ምክር ቤት አስተባባሪ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ጆቫኒ አንጀሎ ቤቹ ይህን ማብራሪያ የሰጡት በሮም ከተማ ስለ ሰዎች ደህንነትና ነጻነት የሚገልጽ መጽሐፍ የምረቃ ስነ ስርዓት ላይ እንደሆነ ታውቋል። በመጽሐፉ የምረቃ ስነ ስርዓት ላይ አሸባሪነት፣ የሰዎች ፍልሰትና ፍርሃትን ማስወገድ በሚሉት ርዕሶች  ላይ ውይይቶች መደረጋቸው ታውቋል። በስነ ስርዓቱ ላይ ጥናታዊ ጽሑፋቸውን ያቀረቡት በቅድስት መንበር ስለ ቅዱሳን ሕይወት የሚያጠና ምክር ቤት አስተባባሪ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ጆቫኒ አንጀሎ ቤቹ፣ በኢጣሊያ የሁፍንግተን ፖስታ አገልግሎት ዳይረክተርና ጋዜጠኛ ሉቺያ አኑንሲያታ፣ የቺቪታ ማሕበር ፕሬዚደንት አቶ ጃኒ ሌታ፣ ጋዜጠኛና ደራሲ አቶ ዋልተር ቨልትሮኒና በኢጣሊያ ፓርላማ የዴሞክራቲክ ፓርቲ ምክትል ጸሐፊ አቶ ማርኮ ሚኒቲ መሆናቸው ታውቋል።     

ደካማ እና ረዳት የሌለቸው ድሆች፣

የጸጥታ ማስከበር ሥራ እየተጠናከረ ቢመጣም በሕዝብ መካከል ፍርሃት እየጨመረ መጥቷል ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ጆቫኒ አንጀሎ የፍርሃቱ ምክንያት ብዙና ጥልቅ ናቸው ብለው ከእነዚህም መካከል የሥራ ዕድል ማጣት፣ የወደፊት ተስፋ መጨለምና የሕይወት ትርጉም መቀነስ ጥቂቶቹ እንደሆኑ አስረድተዋል። ብጹዕ ካርዲናል ጆቫኒ በማከልም እርሳቸው ያደጉባት ኢጣሊያ ከበርካታ ዓመታት በፊት ምንም እንኳን አገሪቱ በዚያን ዘመን ደሃ ብትሆንም ሰዎች ማንነታቸውን በሚገባ የሚያውቁበት፣ አሁን ግን ከድህነት ወጥታ ከሃብታም አገሮች ብትቆጠርም ሕዝቡ ግን ማንነቱን ለይቶ ለማወቅ የተቸገረበት የጸጥታ ችግር ያለበት ዘመን ላይ መድረሱን አስረድተዋል።

በፍርሃት የተዋጠ ውይይት፣

ካርዲናል ጆቫኒ አንጀሎ ቤቹ በፍርሃት ውስጥ ብንገኝም እንኳን ማሕበራዊ ጥያቄዎችን በማቅረብ እርስ በርስ መወያየት ያስፈልጋል ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከወንጌል የሚገኝ ደስታ በሚለው ሐዋርያዊ መልዕክታቸው ወደ ሕዝብ ዘንድ ዘልቆ በመግባት፣ ከሕዝብ ጋር መወያየት፣ ሕዝብን ማጣመት ያስፈልጋል ያሉትን አስታውሰው፣ ለምዕመናን የሚኖርበትን ማሕበረሰብ ማወቅ ማለት ለጥያቄዎቻቸው መልስ መስጠት፣ ችግራቸውን መጋራት ማለት ነው ብለዋል። በመንግሥት የፖለቲካ ዘርፍ ያየን እንደሆነ ደግሞ ወደ ሕዝብ ዘንድ ዘልቆ መግባት ማለት ደግሞ የሕይወት መሠረታዊ ጥያቄዎችን ለምሳሌ ትምህርትን ማዳረስ፣ የሥራ ዕድሎችን መክፈትና የጤና አገልግሎትን ማዳረስ እንደሆነ አስረድተዋል።

አፍሪቃና የሕዝቦቿ ፍልሰት፣

ብጹዕ ካርዲናል ጆቫኒ አንጀሎ የሰዎችን ፍልሰት አስመልክተው ባደረጉት ንግግራቸው፣  የሰዎችን ፍልሰት ማስቆም ወይም መቆጣጠር  እንደማይቻል ገልጸው መፍትሄ ሊገኝ የሚችለው የሰዎች ፍልሰት ከሚጀምርበት አካባቢ ላይ ላሉት ወይም ለሚከሰቱት ችግሮች መፍትሄን በማግኘት እንደሆነ አስረድተዋል።  በኢጣሊያ ፓርላማ ውስት የዴሞክራቲክ ፓርቲ ምክትል ጸሐፊ የሆኑት አቶ ማርኮ ሚኒቲ በበኩላቸው የአውሮጳ አገሮች ለአፍሪቃ መንግሥታት ቀጥታ ዕርዳታን ከመስጠት ይልቅ የሕዝቦች ፍልሰት በሚታዩባቸው አገሮች ለሚኖሩ ወጣቶች የስልጠናና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ማቋቋም፣ ወጣቶች ወደ ሌላ አገር ሳይሰደዱ በአገራቸው ውስጥ ራሳቸውን የሚችሉበትን አጋጣሚዎች ማመቻቸት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።    

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ ባንጊ ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት፣

በቅድስት መንበር ስለ ቅዱሳን ሕይወት የሚያጠና ምክር ቤት አስተባባሪ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ጆቫኒ አንጀሎ ቤቹ በመጨረሻም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ ባንጊ ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ያስታወሱ ሲሆን የኢጣሊያ መንግሥትም በማደግ ላይ ላሉ አገሮች ለሚያደርገው ዕርዳታ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ወደ ባንጊ ባደረጉበት ወቅት በኢጣሊያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ምክትል ዋና ጸሐፊ የነበሩት አቶ ማርኮ ሚኒቲ ቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ባካሄዱበት ጊዜ የመካከለኛ አፍሪቃ ሪፓብሊክ በእርስ በስር ጦርነት ውስጥ እንደነበረች አስታውሰው የቅዱስነታቸው ጉብኝትም እውን የሆነው በመጨረሻ ሰዓት ላይ እንደነበር ብጹዕ ካርዲናል ጆቫኒ አንጀሎ ቤቹ አስታውሰዋል።   

10 November 2018, 16:20