Cardinale Fernando Filoni in Malawi Cardinale Fernando Filoni in Malawi 

ብጹዕ ካዲናል ፌርናንዶ ፊሎኒ አንጎላንና ሳዎቶሜን እንደሚጎበኙ ተነገረ።

የጉብኝታቸው ዓላማም የሁለቱ አገሮች የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ የተመሠረተበትን 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ ክብረ በዓል ላይ ለመገኘት እንደሆነ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በቅድስት መንበር ለሕዝቦች የወንጌል አገልግሎች ስርጭት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ፌርናንዶ ፊሎኒ ከዛሬ ሕዳር 1 ቀን እስከ ህዳር 11 ቀን 2011 ዓ. ም. ድረስ ሁለቱን የአፍሪቃ አገር የሆኑትን አንጎላንና ሳዎቶሜን እንደሚጎበኙ ታውቋል። የጉብኝታቸው ዓላማም የሁለቱ አገሮች የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ የተመሠረተበትን 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ ክብረ በዓል ማጠቃለያ ላይ ለመገኘት እንደሆነ ታውቋል።

ብጹዕ ካዲናል ፊሎኒ ዛሬ ማምሻውን ወደ አንጎላ ዋና ከተማ ሉዋንዳ መድረሳቸው ታውቋል። ብጹዕ ካርዲናል ፊሎኒ በእነዚህ ሁለቱ አገሮች በሚያደርጉት ቆይታ የተለያዩ የቤተክርስቲያን ተቋማትን እንደሚጎበኙ የተገልጸ ሲሆን ነገ ሕዳር 2 ቀን 2011 ዓ. ም. በሉዋንዳ ሃገረ ስብከት የሚገኙትን የቅድስት ኪያራ ፍራንችስካዊያን ደናግልንና ከሰዓት በኋላም ካህናትን፣ ገዳማዊያንንና ገዳማዊያትን እንደሚጎበኙ ታውቋል። ሕዳር 3 እና 4 2011 ዓ. ም. በአንጎላ ውስጥ ወደ ሳውሪሞ ክፍለ ሃገር በሚያደርጉት ጉብኝታቸው ከሀገሪቱ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት፣ ብጹዓን ጳጳሳት፣ ሚሲዮናዊያን፣ ካህናት፣ የዘርዓ ክሕነት ተማሪዎች፣ ገዳማዊያት፣ ወጣቶችና የቤተክርስቲያኒቱ መንፈሳዊ እንቅስቃሴ አባላት ጋር እንደሚገናኙ ፊደስ የዜና አገልግሎት ተቋም ገልጿል። ሕዳር 4 ቀን 2011 ዓ. ም. ከሰዓት በኋላ በሃገረ ስብከቱ ካቴድራል መስዋዕተ ቅዳሴን እንደሚያሳርጉ ከጉብኝታቸው መርሃ ግብር ለማወቅ ተችሏል።

ከአንጎላው ፕሬዚደንት ጋር ይገናኛሉ፣

ብጹዕ ካርዲናል ፌርናንዶ ፊሎኒ ረቡዕ ሕዳር 5 ቀን 2011 ዓ. ም. ከአንጎላ ሪፓብሊክ ፕሬዚደንት፣ ከክቡር አቶ ዮዋዎ ሎረንሶ ጋር እንደሚገናኙ ታውቋል። ብጹዕ ካርዲናል ፊሎኒ በሉዋንዳ ሀገረ ስብከት የከፍተኛ ዘርዓ ክህነት ተማሪዎችን፣ የዘርዓ ክህነት ትምህርት ቤት መምሕራንን እንደዚሁም በሉባንጎ ክፍለ ሀገር የመንግሥት አስተዳደርን፣ የሀገረ ስብከቱ ጳጳሳትን፣ ካህናትንና ዲያቆናትን፣ ገዳማዊያትንና ገዳማዊያንን፣ የሀገረ ስብከቱ የዘርዓ ክህነት ትምህርት ቤት ተመካሪያንንና መምህራኖቻቸውን፣ በማፑንዳ ሃገረ ስብከትም በያኡ የዘርዓ ክህነት ትምህርት ቤት የፍልስፍናንና የነገረ መለኮት ተማሪዎችን፣ ደናግልንና ምዕመናንን  እንደሚያገኟቸው ታውቋል። ብጹዕ ካርዲናል ፊሎኒ የዕለቱ ጉብኝታቸውን በያኡ የዘርዓ ክህነት ትምህርት ቤት በሚያሳርጉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ስነ ስርዓት እንደሚያጠቃልሉ የጉብኝታቸው መርሃ ግብር ያስረዳል። የብጹዕነታቸው የቅዳሜ ህዳር 8 ቀን 2011 ዓ. ም. እቅዳቸው ጠዋት ከሐዋርያዊ እንቅስቃሴዎች ተወካዮች ጋር እንደሚገናኙ ከሰዓት በኋላም ከሃገረ ስብከቱ ወጣቶች ጋር በቪያና በሚገኘው የሃገረ ስብከቱ ካቴድራል እንደሚገናኙ ታውቋል።

በአንጎላ እና በሳዎቶሜ የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ምስረታ 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ መስዋዕተ ቅዳሴ፣

በቅድስት መንበር ለሕዝቦች የወንጌል አገልግሎች ስርጭት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ፌርናንዶ ፊሎኒ፣ እሁድ ህዳር 9 ቀን 2011 ዓ. ም. በአንጎላ ዋና ከተማ በሉዋንዳ በሚገኘው በፋጢማ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ካቴድራል፣ የአንጎላ እና የሳዎቶሜ የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ የተመሰረተበት 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ ክብረ በዓል  መስዋዕተ ቅዳሴ እንደሚያሳርጉ ታውቋል። ከሰዓት በኋላም ከሀገሪቱ ብጹዓን ጳጳሳት ጋር በመሆን በሚያቀርቡት የማታ ጸሎት የአንጎላ ጉብኝታቸውን እንደሚያጠቃልሉ የጉብኝታቸው መርሃ ግብር ያመለክታል። ብጹዕነታቸው በማስከተልም በሳዎቶሜና ፕሪንቺፔ ደሴቶች የሚያደርጉትን ጉብኝት ሕዳር 10 ቀን 2011 ዓ. ም. ጀምረው በደሴቲቱ ትሪንዳድ፣ አልማስ፣ ፓንቱፎ፣ ጓዳሉፔንና ነቨስ የሚባሉ አካባቢዎችን ጎብኝተው ከአካባቢው የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ካህናት፣ ገዳማዊያንና ገዳማዊያት፣ ሚሲዮናዊያንና የቁምስና ተወካዮች ጋር ከተገናኙ በኋላ ማክሰኞ ሕዳር 11 ቀን 2011 ዓ. ም. ወደ ሮም እንደሚመለሱ ከጉብኝታቸው መርሃ ግብር ለማወቅ ተችሏል።

በአንጎላ እና በስዎቶሜ የሚገኝ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን፣

የአንጎላ እና የሳዎቶሜ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ የተመሠረተው በ1959 ዓ. ም. ሲሆን አስቀድሞ ሞዛምቢክንም ይጨምር እንደነበር ነገር ግን የፖርቱጋል የቅኝ ግዛት ካከተመበት ከ1967 ዓ. ም. በኋላ በአንጎላ እና በሳዎቶሜ ሁለት ሃገረ ስብከቶች መቋቋማቸው በሃገሮቹ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ታሪክ ትልቅ እድገትን በማስመዝገብ ዛሬ በአንጎላ በሚገኙት 5 ሊቃነ ጳጳሳት ስር 14 ሀገረ ስብከቶች እንደሚገኙና በሳዎቶሜና ፕሪንቺፔ ደሴቶች ውስጥ አንድ ሀገረ ስብከት እንደሚገኝ ፊደስ የዜና አገልግሎት ከላከልን ዘገባ ለማወቅ ተችሏል።                                        

10 November 2018, 15:35