2018.10.11 Congregazione Generale Sinodo 2018.10.11 Congregazione Generale Sinodo 

የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ፣ ቤተክርስቲያን ሕገ ወጥ ስደትንና የሰዎች ዝውውርን እንደምትቃወም ገለጸ።

ስለ ወጣቶች ነጻነት የተወያዩት የሲኖዶሱ አባቶች እንደገለጹት ወጣቶች በሌሎች እንዳይታለሉ የሚከላከላቸው ውስጣዊ ነፃነት እንዲኖራቸው፣ ኢየሱስንና የእርሱን ትዕዛዛት መከተል እውነተኛ ነጻነትን እንደሚሰጥ ገልጸዋል። ወጣቶች፣ እውነተኛ ነጻነት በውስጣቸው እንዲሰማቸው፣ የሐዋርያዊ አገልጋዮች ዕለታዊ የሕይወት ምስክርነትን፣ የሚያስተምሩትን የወንጌል መልዕክት በተግባር መኖራቸውን በመመልከት እንደሚፈልጉና፣ በዚህ እውነተኛ ምስክርነት በመታገዝ ወደ እውነተኛ ነጻነት መድረስ እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በቫቲካን 15ኛ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ጠቅላላ መደበኛ ጉባኤያቸውን በማካሄድ ላይ የሚገኙት የመላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጳጳሳት፣ ቤተክርስቲያን ሕገወጥ ስደትንና የሰዎች ዝውውርን እንደምትቃወም ትናንት፣ ጥቅምት 1 ቀን 2011 ዓ. ም. ባደረጉት ውይይት ገልጸዋል።

ከመስከረም 23 ቀን 2011 ዓ. ም. ጀምሮ በቫቲካን ከተማ 15ኛ አጠቃላይ መደበኛ ጉባኤውን በማካሄድ ላይ የሚገኝው የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ፣ ሕገ ወጥ ስደትንና የሰዎች ዝውውርን መቃወምና ተስፋን ማስቆረጥ የቤተክርስቲያን አንዱ ሥራ ነው ያለው የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ጉልበት፣ እውቀትና ልዩ የፈጠራ ችሎታ በከንቱ በባሕር ውስጥ ሰጥሞ ሲቀር ማየት አንፈልግም ብሏል። የሲኖዶሱ አባቶች ይህን ካሉ በኋላ በኢንዱስትሪ ያደጉ አገሮች ቴክኖሎጂንና ዕውቀትን በማደግ ላይ ወዳሉት አገሮች በማሸጋገር ወጣቶች በተወለዱበት አገር ሆነው ራሳቸውን በእውቀት የሚያሳድጉበትን፣  ለአገራቸው ብልጽግና እንዲሰሩ የሚያበረታታ ዕድል እንዲፈጥሩ ጠይቀዋል።

የሕሊና ምርመራ እንዲኖር ያስፈልጋል፣

የሲኖዶድሱ አባቶች በዕለት ባካሄዷቸው ውይይቶች መካከል፣ ከቤተክርስቲያን ቅዱሳት ምስጢራት አንዱ የሆነው የይቅርታ ምስጢር ሲሆን፣ ይቅርታን ማድረግ በሰዎች ላይ ከተጫኑት የሐጢአትና የበደል ሸክምች ነጻ የሚያደርግ የእግዚአብሔር ስጦታ በመሆኑ በሰዎች መካከል ይቅርታን መደራረግ ያስፈልጋል ብለዋል። ወደ ይቅርታ ከመደረሱ በፊት ወጣቶች የሕሊና ምርመራን በማድረግ የሐጢአትንና የበደልን ትክክለኛ ትርጉም በሚገባ ተገንዝበው፣ እግዚአብሔር በሕይወታቸው ውስጥ መኖሩን እዲገነዘቡ ማስተማር ያስፈልጋል ብለዋል። የሲኖዶሱ አባቶች በማከልም የሕሊና ምርመራ ለወንጌል ምስክርነት መሠረታዊ መንገድ መሆኑንም ተመልክተዋል። ወጣቶች በወጣትነት ደረጃ ብቻ የሚቀሩ ሳይሆን ዕድሜአቸው እየጨመረ በሄደ ቁጥር ቤተክርስቲያናቸውን ለማሳደግ የሚፈለግባቸውን አስተዋጽዖ እንዲያበረክቱ መጠራታቸውንም የሲኖዶሱ አባቶች አስረድተዋል። ምክንያቱም በቤተክርስቲያን አገልግሎት ውስጥ ካህን፣ ደናግል፣ ወላጅ፣ ያገባ፣ ያላገባ የሚል ልዩነት ሳይደረግበት የእግዚአብሔር ጥሪ እያንዳንዱ ሰው በተሰማራበት የአገልግሎት ዘርፍ በርትቶ በመሥራት ለቅድስና እንዲበቃ ነው ብለዋል። የሲኖዶሱ አባቶች፣ የጥሪ አገልግሎት በተለያዩ የሕይወት አቅጣጫዎች የተሰማሩት ሰዎች በሚሰጡት ሕያው ምስክርነቶች በመታገዝ፣ እያንዳንዱ ወጣትም የራሱን ጥሪ መገንዘብ እንዲችል ያግዛል ብለዋል።

ወጣቶች የነጻነትን ትርጉም ይወቁ፣

ስለ ወጣቶች ነጻነት የተወያዩት የሲኖዶሱ አባቶች እንደገለጹት ወጣቶች በሌሎች እንዳይታለሉ የሚከላከላቸው ውስጣዊ ነፃነት እንዲኖራቸው፣ ኢየሱስንና የእርሱን ትዕዛዛት መከተል እውነተኛ ነጻነትን እንደሚሰጥ ገልጸዋል። ወጣቶች እውነተኛ ነጻነት በውስጣቸው እንዲሰማቸው፣ የሐዋርያዊ አገልጋዮች ዕለታዊ የሕይወት ምስክርነትን፣ የሚያስተምሩትን የወንጌል መልዕክት በሕይወታቸው ውስጥ በተግባር መኖራቸውን በመመልከት እንደሚፈልጉና፣ በዚህ እውነተኛ ምስክርነት በመታገዝ ወደ እውነተኛ ነጻነትን መድረስ እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።

በምኞት የተሞላ ልብ እንዲኖር ያስፈልጋል፣

ወጣቶችን በሕይወት ጉዞአቸው ለማገዝ የሚያስችል ትክክለኛው መንገድ በሙሉ ልብ እና ፍላጎት ተነሳስቶ በፍቅር ማዳመጥ፣ ብርታትንንና ተስፋን በመስጠት፣ በእያንዳንዱ የእድገት ደረጃ የሚያስፈልገውን እንክብካቤን በመስጠት እንደሆነ የሲኖዶሱ አባቶች አምነዋል። አመጽ፣ ጦርነትና ሙስና በተስፋፋበት፣ ፍትህ በጎደለበት ዓለም ውስጥ የሚገኙት ወጣቶች በራስ መተማመን እንደሚያንሳቸውና የወደ ፊት ተስፋቸውንም እንደሚያጨልምባቸው ተገንዝባ ቤተክርስቲያን ወጣቶችን ተቀብላ ሳታቋርጥ መደገፍ፣ ማበረታታት፣ እውነተኛ ውስጣዊ ነጻነት ተሰምቷቸው ሃላፊነትን የሚወጡ የማድረግ ግዴታ እንዳለባት ብጹዓን ጳጳሳት አስረድተዋል። 

የሲኖዶሱ አባቶች በውይይታቻው ወቅት፣ ቤተክርስቲያን ከቤቷ የራቁ ልጆቿን በምሕረት ዓይን በመመልከት ተመልሰው የሚመጡበትን ዕለት በናፍቆት በትዕግስትና በተስፋ እንደምትጠባበቃቸው ገልጸዋል። ወጣቶች በችግር ላይ ወድቀው፣ የሚደርስላቸው ጠፍቶ፣ ብቸኝነት እንዲሰማቸው ፈጽሞ አትፈልግም ያሉት ብጹዓን ጳጳሳት፣ ቤተክርስቲያን በወጣቶች ላይ ምንም ዓይነት ጫናን ሳታሳድር፣ ግዴታም ሳታደርግ ነጻነታቸውን በትክክል እንዲያውቁ ማገዝ ትፈልጋለች ብለዋል። ቤተክርስቲያን ለወጣች የምትሰጠው ድጋፍ ውጤታማ ሊሆን የሚችለውና በወጣቶች ልብ ውስጥ የሚገኘው እውነት ሊገለጥ የሚችለው እውነተኛውን ነጻነት የተከተለ የኢየሱስ ክርስቶስ ክብር ሲገለጥ እንደሆነ አስረድተዋል።

ቤተክርስቲያን የወጣቶች ሕልም ትጋራለች፣

ቤተክርስቲያን የተጠራችበትን የወንጌል ተልዕኮ ተግባራዊ ማድረግ የምትችለው ክርስቲያኖች ለወንጌል ያላቸውን ፍቅር በማሳደግ፣ በመካከላቸው የአንድነት ፍቅር እንዲያድግ በማድረግ እንደሆነ አሳስበዋል። በግልጽ ወጥቶ የማይታይ ድብቅ የክርስቲያኖች ሕብረት፣ በተግባር የማይገልጥ ፍቅር ወጣቶች በቤተክርስቲያን ውስጥ ተቀባይነት እንዳላቸው አያሳይም ያሉት ብጹዓን ጳጳሳት ቤተክርስቲያን ሁሉ አቀፍ፣ ደስተኛና ሁሉን ተቀባይ በመሆን የወጣቶችን ምኞትና ሕልም እውን የምታደርግ መሆን ይኖርባታል ብለዋል።

ወሲባዊ ጥቃት የተፈጸመባቸው በቤተክርስቲያን ተልዕኮ ቅድሚያን ያግኙ፣

ቤተክርስቲያን የምዕመናኖቿ እምነት እንዲቀዘቅዝ ካደረጉት የተሳሳቱ አካሄዶች መካከል አንዱ ከዚህ በፊት የተፈጸሙ ወሲባዊ ጥቃቶች እንዳሉ የተረዱት የሲኖዶሱ አባቶች እነዚህ የተሳሳቱ አካሄዶች ቤተክርስቲያንን እንደጎዱ ተገንዝበው እንዳይደገሙ ለማድረግ ጥብቅ ክትትል ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ጥቃቱ የተፈጸመባቸውን በማጽናናት ምሕረትን መጠየቅ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

11 October 2018, 17:30