2018.10.26 Sinodo: Briefing 26 - 3 2018.10.26 Sinodo: Briefing 26 - 3 

ብጹዕ አቡነ ማርቲን የመንፈስ ቅዱስ ሃይል መገለጡን ተመልክተናል ማለታቸው ተገለጠ።

የመንፈስ ቅዱስ ሃይልና ደስታ ወደየሃገረ ስብከቶች ዘንድ መድረስ አለበት ብለው ወደ መጡበት ሀገረ ስብከት ስመልስ የሲኖዶሱ አምባሳደር እሆናለሁ ብለዋል። ቤተክርስቲያን ከመላው ዓለም ወጣቶች ጋር በመሆን ለወጣቶች ብቻ ሳይሆን ከወጣቶች ጋር መስራት ትፈልጋለች ብለው ወጣቶችም በመንፈስ ቅዱስ በመታገዝ የወንጌል መልዕክተኞች ይሆናሉ ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

15ኛውን የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ አጠቀላይ መደበኛ ጉባኤን በመካፈል ላይ የሚገኙት የአይርላንድ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንትና የአርመግ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኢሞን ማርቲን ትናንት በቫቲካን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ 15ኛው የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ የመንፈስ ቅዱስ ሃይል የተገለጠበት የጸጋ ጊዜ ነበር ብለዋል። በማከልም ይህ የመንፈስ ቅዱስ ሃይልና ደስታ ወደየ ሃገረ ስብከቶች ዘንድ መድረስ አለበት ብለው ወደ መጡበት ሀገረ ስብከት ስመልስ የሲኖዶሱ አምባሳደር እሆናለሁ ብለዋል። ቤተክርስቲያን ከመላው ዓለም ወጣቶች ጋር በመሆን ለወጣቶች ብቻ ሳይሆን ከወጣቶች ጋር መስራት ትፈልጋለች ብለው ወጣቶችም በመንፈስ ቅዱስ በመታገዝ የወንጌል መልዕክተኞች ይሆናሉ ብለዋል።

ጋዜጣዊ መግለጫቸውን ከሰጡት መካከል የኦስትሪያ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንትና የቬና ሊቀ ጳጳሳ ብጹዕ ካርዲናል ክርስቶፍ ሾንቦርን በበኩላቸው ጉባኤውን የተካፈሉት የሲኖዶስ ብጹዓን ጳጳሳትና ወጣቶች በየአገሮቻቸው የሚደርሱ ጭቆናዎችና ስቃዮች በሕዝቦቻቸው ጩሄት እንደሚቀንሱ ተስፋ አላቸው ብለዋል። የቬና ሊቀ ጳጳሳ ብጹዕ ካርዲናል ክርስቶፍ በማከልም ሕዝቦች በየአገሮቻቸው ሆነው የሚያሰሙትን የስሞታ ድምጽ የፖለቲካና የኤኮኖሚው ዓለምም ልብ እንደሚያደርገው ተስፋ አለኝ ብለዋል። 

የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ጉዞ በዓለማችን በተለያዩ ማሕበራዊ ዘርፎች የሚከናወኑ ተግባራትን ጥበብ በተመላበት አካሄድ በመከታተል፣ ድምጽ ማሰማት እንደሆነ ካርዲናል ክርስቶፍ አስረድተው ከዚህ በፊትም እንደተናገሩት የብጹዓን ጳጳሳት ሃሳብ ካዳመጡ በኋላ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለሲኖዶሱ ንግግር እንደሚያደርጉ ገልጸዋል። የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ታላቅ ምልክት በመሆኑ ተሰሚነት እንደሚኖረው ገልጸው፣ በጦርነት ከተጎዳ አፍሪቃዊ አገር የመጣ የጉባኤው ተካፋይ የእኛ ብቸኛ ተስፋችን፣ አንደ መኖሪያ ቤታችን የምንመለከታት መጠለያችን ቤተክርስቲያን ናት ያለውን አስታውሰዋል።

ትናንት ጥቅምት 16 ቀን 2011 ዓ. ም. በቫቲካን ጋዜጣዊ መግለጫቸውን ከሰጡት ብጹዓን ጳጳሳት መካከል በኬንያ የኒየሪ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ አንቶኒ ሙሄሪያ፣ 15ኛው የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ በወጣቶች መካከል አዲስ ጉልበትና ስሜት እንደሚቀሰቅስ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል። ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ አንቶኒ በመግለጫቸው እኛ ጳጳሳት ወጣቶችን በእግዚአብሔር ፍቅር በመታገዝ መቀስቀስ ይኖርብናል ብለዋል።  ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ አንቶኒ 15ኛውን የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ አጠቃላይ መደበኛ ሲኖዶስን በመካፈላቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው በጉባኤው ወቅት መንፈስ ቅዱስ በመካከላቸው በመሆን እንደመራቸው ምስክርነታቸውን ገልጸዋል።

ቤተክርስቲያንን የሚመራት መንፈስ ቅዱስ ነው፣

በትናንትናው ዕለት ጋዜጣዊ መግለጫቸውን የሰጡት በካንቦዲያ የባታምባንግ ሐዋርያዊ አስተዳዳሪ የሆኑት ክቡር ሄንሪክ ፊጋረዶ ከ15ኛው የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ አዲስ የማበረታቻ ሀይል መምጣቱን ገልጸው በእርግጥም ሲኖዶሱ ስለ ወጣቶች ጥሪ በማሰብ፣ ይህን ጥሪ በጥበብ አስተውለውና ተገንዝበው ለአገልግሎት የሚያዘጋጃቸውን አዲስ ሃይል እንደሚቀበሉ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል። ቤተክርስቲያንም በወጣትነትን መንፈስ በመላበስ፣ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ጉዞዋን ወደ ፊት እንደምትቀጥል አስረድተዋል።

ወጣቶች ተመልካች ብቻ ሆነው አይቀሩም፣

15ኛውን የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ አጠቃላይ መደበኛ ጉባኤን ከተካፈሉት መካከል በኩባ የቅዱስ ኤጂዲዮ ማህበር አባል የሆነው ወጣት ኤርድዊን አልበርቶ ኦርቴጋ፣ ወጣቶች በቤተክርስቲያን ውስጥ ዋነኛ ተዋናይ እንጂ ተመልካች ሆነው መታየት ወይም መቆጠር  የለባቸውም ብሏል። በበርካታ ችግሮች ውስጥ የሚገኝ ዓለማችን ከችግሮች መውጣት የሚችልበትን ጊዜያዊ መፍትሄን ብቻ እያፈላለገ እንደሆነ አስረድቶ ነገር ግን ወጣቶች ስለ ወደፊት ሕይወታቸውም ማሰብ መጨነቅ ይኖርባቸዋል ብሏል። በማከልም 15ኛው የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ጉባኤ እንድናዳምጥና እንድንደመትም ዕድል ሰጥቶናል ብሏል።

በቅድስት መንበር የመገናኛ ክፍል ተጠሪ ክቡር አቶ ፓውሎ ሩፊኒ፣ በብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ የቀረበ የመጨረሻ ሰነድ አንድ ባንድ ድምጽ እንደተሰጠብት ገልጸዋል። አቶ ሩፊኒ በማብራሪያቸው የመጨረሻው ሰነድ ከፍተኛ ተስፋ የተጣለበትና እንዲጸድቅ የሚጠበቅ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ውጤት እንደሆነ ገልጸዋል።

የሲኖዶስ አጠቃላይ ስታትስቲክስ፣

ከመስከረም 23 ቀን 2011 ዓ. ም. ጀምሮ በቫቲካን ከተማ፣ 15ኛ የብጹዓን ጳጳሳት አጠቃላይ መደበኛ ጉባኤ ላይ የቀረቡትን ሦስት ዙር የጠቅላላ ጉባኤ ውይይቶችን 240 ብጹዓን ጳጳሳት መካፈላቸውን፣ 32 በአድማጭነት መካፈላቸውን፣ ነጻ ውይይቶችን 69 ብጹዓን የሲኖዶሱ አባቶች 13 እንደ አድማጭ ሆነው መካፈላቸውን በቅድስት መንበር የመገናኛ ክፍል ተጠሪ የሆኑት ክቡር አቶ ፓውሎ ሩፊኒ ገልጸዋል።

የቅድስት መንበር የመገናኛ ክፍል በማከልም፣ 15ኛውን የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ አጠቃላይ መደበኛ ጉባኤ በማስመልከት የመጀመሪያ ጋዜጣዊ መግለጫ ከተሰጠበት ከሰኞ መስከረም 21 ቀን 2011 ዓ. ም. ጀምሮ የብጹዓን ጳጳሳት ሲንዶስ ሂደትን በማስመልከት የቫቲካን ዜና ክፍልና የቫቲካን ሬዲዮ በዘረጉት የተለያዩ ማሕበራዊ ሚዲያ መስመሮች 1400 የቲዊተር መልዕክቶች በሃሽ ታግና በሲኖድ 2018 ድረ ገጽጾች በኩል መሰራቸታቸውን ክቡር አቶ ሩፊኒ ገልጸው፣ በየዕለቱ በሲኖድ 2018 ድረ ገጽ በኩል የቀረቡ 15 የሚሆኑ ጋዜጣዊ መግለጫዎችን የቫቲካን ዜና አገልግሎት በአራት ቋንቋዎች ማለትም በእንግሊዘኛ፣ በስፓንኛ፣ በፈረንሳይኛና በጣሊያንኛ ቋንቋዎች፣ በዓለም ዙሪያ ሆነው በማሕበራዊ ሚዲያዎች በኩል ለሚከታተሉት ተመልካቾች መተላለፉን አስረድተዋል።

ሲኖዶስ2018 የተባለ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ድረ ገጽ ከአንድ መቶ ሺ በላይ የቲዊተርና የምስል መልዕክቶችን ያስተላለፈ ሲሆን በማሕበራዊ ድረ ገጽ ወደ 500,000 የሚጠጉ ስለ ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ አጠቃላይ መደበኛ ጉባኤ የሚገልጹ የቲዊተር፣ የፎቶግራፍና የቪዲዮ ምስል መልዕክቶች መሰራጨታቸው ታውቋል። እነዚህን መልዕክቶች በብዛት ለመቀበል የቻሉት የደቡብና የሰሜን አሜርካ አገሮች ሲሆኑ ሌሎች አገሮችን ጨምሮ የሩሲያና የቻይና ሕዝቦችም በብዛት ተከታተላቸውን አቶ ሩፊኒ ገልጸዋል።

በርካታ አንባቢዎች ያሉት ሎዘርቫቶሬ ሮማኖ የተሰኘ የቅድስት መንበር ጋዜጣ 15ኛውን የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ አጠቃላይ መደበኛ ጉባኤን በየቀኑ ተከታትሎ በመዘገብ በውይይቶችንና በጠቅላላ ጉባኤዎች የቀረቡ ርዕሶችን ተንትኖ በማቅረብ ለአንባቢያኑ በቂ መረጃን ማቅረቡ ታውቋል። የጋዜጣ ክፍሉ የየቀኑን ጉባኤ ተከታትለው ትንታኔን እንዲሰጡ በመደቧቸው ተወካዮቹ አማካይነት የሲኖዶሱ አባቶች ላከናወኗቸው 19 ጠቅላላ ጉባኤዎች ገለጻና ትንታኔ መስጠታቸውን በቅድስት መንበር የመገናኛ ክፍል ተጠሪ ክቡር አቶ ፓውሎ ሩፊኒ ገልጸዋል።

27 October 2018, 17:27