ፈልግ

Gesucristo Gesucristo 

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ር.ሊ.ጳ.ን የሚቃረን ምእመን ለካቶሊክ የእምነት ልማድ ታማኝ አይደለም።

“የእውነት ብሩህነት” የተሰኘ ሐዋርያዊ መልዕክት መሠረታዊ በሆኑ የስነ ሞራላዊ አስተምህሮች በመመራት፣ ቅዱስት መጽሐፍት እና ሕያው ሐዋርያዊ መርህን በመከተል የሚያቀርቡት መሠረትዊ መንገዶችን በመከተል የሰው ልጅ የመልካም ሆነ የክፉ ሃሳብ ምንጭ ከወዴት እንደሆነ መልስ የሚፈልገው ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ በመቅረብ ነው።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ሁለተኛ ከ25 ዓመት በፊት ይፋ ያደረጉት “የእውነት ብሩህነት” የተሰኘ ሐዋርያዊ መልዕክት ለመላው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጹዓን ጳጳሳት መላኩ ይታወሳል። ይህን ሐዋርያዊ መልእክት በመጥቀስ አስተያየታቸውን የገለጹት ሞንሲኞር ሪኖ ፊዚኬላ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን የሚቃረን ምዕመን ለካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ባሕል ታማኝ አይደለም ማለታቸው ታውቋል።   

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ 2ኛ የጻፉት “የእውነት ብሩህነት” የተሰኘ ሐዋርያዊ መልዕክት መሠረታዊ በሆኑ የስነ ሞራላዊ አስተምህሮች በመመራት፣ ቅዱስት መጽሐፍት እና ሕያው ሐዋርያዊ መርህን በመከተል የሚያቀርቡት መሠረትዊ መንገዶችን በመከተል የሰው ልጅ የመልካም ሆነ የክፉ ሃሳብ ምንጭ ከወዴት እንደሆነ መልስ የሚፈልገው ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ በመቅረብ ነው ብለዋል። በቅድስት መንበር የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ፕሬዚዳንት የሆኑት ብጹዕ ሞንሲኞር ሪኖ ፊዚኬላ እንደገለጹት የሐዋርያዊ መልዕክቱ ይዘት እና ከዚህ በፊት የተጻፉ የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ባሕሎችን ስንመለከታቸው፣ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን አስተምህሮች የሚቃወም ምንም ዓይነት ሃሳብ አልተገኘም።

ብጹዕ ሞንሲኞር ሪኖ ፊዚኬላ “የእውነት ብሩህነት” በሚል አርዕስት የሚታወቀውን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ሁለተኛ ሐዋርያዊ መልዕክት ይዘት ሲያስረዱ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ በማደግ ላይ ያለውን የዓለማዊነት ባሕል እና የሚያስከትለውን ፍልስፍናዊ ተለዋዋጭነት ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ እንደሆነና ከዚህም በተጨማሪ ክርስቲያናዊ አስተምህሮችን ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ የባልታዛር የምርምር ሥራንም ያጠቃልላል ብለዋል።

ከሁሉም አስቀድሞ ስለ እውነት ስንናገር ተጨባጭ የሆነ ጽንሰ-ሐሳብ ሊኖረን ይገባል። እውነት አንድ የተወሰነ አቅጣጫ ብቻ ያለው ሊሆን አይችልም ያሉት ብጹዕ ሞንሲኞር ሪኖ ፊዚኬላ ለክርስቲያኖች እውነት ማለት ከሁሉም በፊት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትቶልን የሄደው ቃሉ ነው ብለዋል። ኢየሱስም፦ “እኔ መንገድ፣ እውነትና ሕይወት ነኝ” ያለውን መዘንጋት የለብንም። ስለዚህ ኢየሱስ ክርቶስ የገለጸው እውነት አንድ ሰው ከወንጌል መልዕክት ጋር ሊኖር ስለሚገባው ግንኙነት እና በዚህም ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን ከገለጠበት እውነት ጋር ግንኙነት እንዲኖር ያደርጋል ብለዋል። የኢየሱስ ክርስቶስ እቅድ ይህ እውነት ከሐዋርያት ጀምሮ እስከ እኛ እንዲደርስ፣ በእኛም ዘንድ ተውስኖ ሳይቀር የእርሱ አምላካዊ ምስጢር ከጊዜ ወደ ጊዜ የበለጠ እንዲገለጥ ይፈልጋል ብለዋል። በስነ መለኮት ጠበብት አስተያየት ለምሳሌ “የእውነት ብሩህነት” አስተምህሮ ተለዋዋጭነት የሌላቸው የቤተ ክርስቲያን ሕግጋትና የስነ ሞራላዊ አስተምህሮች መኖራቸው ይታወቃል። እነዚህ የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮዎችም ቢሆኑ የተመሠረቱት በወንጌል ላይ በተገለጸው እውነት ነው። መሠረታቸውን ቅዱስ ወንጌል ያደረጉት የቤተ ክርስቲያን አስተምሮዎች፣ የእግዚአብሔር ቃል፣ እውነት መሆኑን መረዳት እንድንችል የተለያዩ መንገዶችን በማቅረብ የሚያግዙን መሆን አለባቸው ብለዋል።

ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ምን ጊዜ ቢሆን እውነትን ለማወቅ የሚደረጉ ጥረቶችን ትቀበላለች እንጂ አትከለክልም። እውነት በራሱ የነጻነትና የታማኝነት ይዘት አለውና “እውነት ነጻ ያወጣችኋል” የሚል ቃል ተጽፏልና። ይህ ነጻነት እያንዳንዱ ምእመን በየጊዜው እየሰፋ እና ግልጽ እየሆነ የሚመጣውን እውነት እንዲያገኝ የሚያግዝ መሆን አለበት። ይህን እውነት ለማግኘት የምእመኑ ታማኝነት እንዲኖር ያስፈልጋል። በታማኝነት እና

በእውነት መካከል ያለው ግንኙነትም መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነትን የተከተለ ፅንሰ-ሐሳብ ያለው ነው።

ለቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ እድገት ተብሎ የቤተ ክርስቲያን ሕገ ቀኖና እንደ ማነጻጸሪያ መሣሪያ መቀመጥ የለበትም። እውነትን ለማግኘት ያለንን ነጻነት ስለሚገድብ የቤተ ክርስቲያንን ሕገ ቀኖና እንደ አንድ መንገድ መጠቀም አስፈላጊ አይሆንም። ምክንያቱም ለቤተ ክርስቲያን የእምነት ባሕል ያለንን ታማኝነት ስለሚቀንስ ነው። ይህ በመሆኑ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን አስተምህሮ ለመቃወም የሚያስችል ምንም ምክንያት ሊኖር አይችልም። ነገር ግን መረዳት ያለብን ነገር ቢኖር፣ እውነትን ለማወቅ የሚደረገው ጥረት ምን ያህል ዘላቂነት አለው የሚል ነው። ከዚህም በተጨማሪ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስተምህሮች በሙሉ ተያያዥነት ስላላቸው ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ማጥናትና መረዳት እንደሚያስፈልግ ብጹዕ ካርዲናል ሪኖ ፊዚኬላ አስገንዝበዋል።   

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስተምህሮች ለወንጌል ስርጭት አገልግሎት በር ከፋች ናቸው ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ፊዚኬላ፣ በዚህ ሂደት ሁሉ እጅግ አስፈላጊ እና መዘንጋት የሌለበት ዋናው ነገር ቢኖር በመጀመሪያ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር መገናኘት መቻል፣ ቤተ ክርስቲያንም ሳታቋርጥ የወንጌል ስርጭት አገልግሎትን ማዳረስ እንዳለባት፣ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችም አገልግሎታቸውን ወደ ዓለም ሁሉ ለመሄድ መጠራታቸውን እንዲያውቁ ያስፈልጋል ብለዋል። የቤተ ክርስቲያን ቀዳሚ እቅድ ይህ በመሆኑ የወንጌልን እውነት እና ደስታን ለሁሉም በብቃት ማዳረስ እንዲቻል ውጤታማ የሆነ መንገድ መከተል ያስፈልጋል ብለዋል። ይህን ለማከናወን የምሕረትን መንገድ መጓዝ የግድ ይሆናል ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ሪኖ ፊዚኬላ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያወጁት የምሕረት ኢዮቤልዩ ይህን የሚገልጽ ነበር ብለዋል።    

07 August 2018, 14:26