ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ የሮም ካኅናት ተግዳሮትን ከመሸሽ ይልቅ መጋፈጥ እንደሚገባ አሳሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ቤተ ክኅነቱ አብሮ መጓዝ እንዳለበት ያሳሰቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ዓመፅ በበዛበት ዓለም ውስጥ፣ በሮም ሀገረ ስብከት ድህነት እና የመኖሪያ ቤቶች እጥረት በተከሰተበት በዚህ ወቅት ጥሪያቸውን እንዲያድሱ በማሳሰብ፥ ካኅን የኅብረት ሰው እንዲሆን የተጠራ፣ የወንጌል የማደስ ኃይልን በገሃድ ማሳየት የሚችል እና የትኅትና ሕይወት ምስክር እንደሆነ አስረድተዋል።
የመላዋ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ መሪ ከመሆናቸው በተጨማር የሮም ሀገረ ስብከትም ጳጳስ የሆኑት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በሀገረ ስብከታቸው ውስጥ ከሚያገለግሉ ካኅናት እና የዘርዓ ክኅነት ተማሪዎች ጋር በቫቲካን ሐሙስ ሰኔ 5/2017 ዓ. ም. ተገናኝተው ባሰሙት ንግግር፥ ቤተ ክኅነቱ ለሀገረ ስብከቱ ውድ ሃብት መሆኑን በማስታወስ አድናቆታቸውን ገልጸውለታል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ የሮም ሀገረ ስብከት ዋና መቀመጫ የሆነውን የቅዱስ ዮሐንስ ዘላቴራን ጳጳሳዊ ባዚሊካ ሃላፊነት ግንቦት 17/2017 ዓ. ም. ከተቀበሉ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሀገረ ስብከቱ ቤተ ክኅነት ጋር ተገናኝተዋል። ቅዱስነታቸው በዚህ ወቅት የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስ ብጹዕ ዮሐንስ ጳውሎስ ቀዳማዊን በመጥቀስ እንደተናገሩት፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስ ብጹዕ ዮሐንስ ጳውሎስ ቀዳማዊ ለአጭር ጊዜ ብቻ ያገለገሉ ቢሆንም ነገር ግን አለኝታነታቸውን፣ ፍቅራቸውን እና ጥንካሬያቸውን በተጨባጭ ማሳየታቸውን አረጋግጠው፥ ከቤተ ክኅነቱ ጋር በቅርብ በመተዋወቅ አብረዋቸው ለመጓዝ ፍላጎት እንዳላቸው በድጋሚ ተናግረዋል።
“ሁላችንም ታማኝ እና አርአያ ለመሆን ራሳችንን ለአገልግሎት እንስጥ! ውስንነታችንን እናውቃለን፤ ይህን እግዚአብሔርም በጥልቅ ያውቀዋል፤ ከእርሱ ዘንድ ልዩ ጸጋን ተቀብለናል፥ የእርሱ አገልጋዮች የሆንንበትን ክቡር መዝገብ ሰጥቶናል፤ አገልጋዩም ታማኝ እንዲሆን ተጠይቋል” ሲሉ አስረድተዋል።
በካኅናቱ መካከል ወንድማማችነት ማሳደግ
ወጥመዶች የሚታገሉት ከውጪ ብቻ ሳይሆን ከውስጥም ንቁ በመሆን፣ ለግለሰባዊ ግንኙነቶች እና በልብ ውስጥ ላለው ነገር ትኩረት በመስጠት ነው” ይሉት ቅዱስነታቸው፥ “በተለይ ልዩ ችግር ሲያጋጥመን የሚመጣው የድካም ስሜት፣ ሌላውን መረዳት እና ማዳመት ስለጠፋ ወይም በሌሎች ምክንያቶች ሊሆን ይችላል” ብለዋል።
“ከእናንተ ጋር በኅበረት በመራመድ ልረዳችሁም እፈልጋለሁ” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ እያንዳንዱ ካኅን በአገልግሎቱ መረጋጋትን ማግኘት እንደሚችል ተናግረው፥ “ከእግዚአብሔር ጋር በመገናኘት እና ቃሉን በመስማት በጠንካራ መንፈሳዊ ሕይወት ውስጥ የተመሠረተ የካኅናትን ወንድማማችነት እጠይቃችኋለሁ” ብለዋል።
ልዩ የአገልግሎት ስሜት እና የወንጌል ታማኝነት
በሮም ሀገረ ስብከት ውስጥ ያለው አንድነት ወደ ቁርጠኝነት መተርጎም እንዳለበት አጽንኦት የሰጡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ይህን ማጽናት የሚቻለው በልዩ ተነሳሽነት፣ በስልጠና እና በአገልግሎቶች እንደሆነ ገልጸው፥ ለማስቀጠል የሚደረገው ጥረት የተለየ እንደሆነ እና በአንድነት ለመቀጠል የሚያግዝ ሐዋርያዊ ጉዞ፥ ለወንጌል በመታመን እና ቤተ ክርስቲያንን በማበልጸግ እንደሆነ ገልጸው፥ በዚህ ሁሉ መካከል መሪው ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን ልብ ማለት እንደሚገባ አሳስበዋል።
የሰላም እና የፍትህ ነቢያት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለቤተ ክኅነቱ ባቀረቡት ግብዣ፥ ታሪክን ከወንጌል አገልግሎት ጋር ማጣመር የቻሉትን ቅዱሳን ካህናት፥ አባ ፕሪሞ ማዞላሪ እና አባ ሎሬንዞ ሚላኒ፥ የሰላም እና የፍትህ ነቢያት መሆናቸውን መመልከት እንደሚገባ አሳስበው፥ በሮም ውስጥ የድህነት ሕይወት የኖሩ፣ ለፍትህ እና ለሰው ልጅ ዕድገት ሲሉ የተሰውትን አባ ሉዊጂ ዲ ሊግሮን በመጥቀስ፥ “በከተማችን ውስጥ የቅድስና ዘር መዝራትን ለመቀጠል እነዚህን የጥንካሬ ምሳሌዎችን መውሰድ ይገባል” ብለዋል።
ቅዱስነታቸው በመጨረሻም፥ ከሮም ሀገረ ስብከት ቤተ ክኅነት ጋር በመቀራረብ በፍቅር አብሮ ለመራመድ እንደሚፈልጉ ገልጸው፥ በአንድነት፣ በአርአያነት እና በትንቢታዊ ቁርጠኝነት ጌታን በማገልገል ማደግ እንደሚገባ በማሳስብ፥ የቅዱስ አውግስጢኖስን ጥሪ በማስታወስ፥ ቤተ ክርስቲያንን እንዲወዱ እና የጠፉት በጎች የእግዚአብሔርን ፍቅር እንዲያውቁ መጸለይ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጳጳስት ታማኝ የሆነ የተዋሃደ ሀገረ ስብከት
ብፁዕ ካርዲናል ባልዶ ሬይና የሮም ሀገረ ስብከት ረዳት ጳጳስ እና የቅዱስ ዮሐንስ ላተራን ጳጳሳዊ ባዚሊካ ሊቀ ጳጳስ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እና 809 ካኅናት እና 149 ቋሚ ዲያቆናትን ላቀፈው የሮም ሀገረ ስብከት ቤተ ክኅነት ሰላምታ ካቀረቡ በኋላ ባደረጉት ንግግር፥ ከላይ ከተጠቀሱት መካከል 132 ቱ በተልዕኮ ላይ መሆናቸውን እና ከ50 በላይ የሚሆኑት በጥሪያቸው ላይ እንደገና ለማስተንተን ወይም በሌላ ችግር አገልግሎታቸውን ለማቆም መወሰናቸውን ገልጸዋል።
ከ50 በላይ አረጋውያን ካኅናት በዕድሜ እና በጤና እክል ምክንያት በእንክብካቤ ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል። ሀገረ ስብከቱ 333 ቁምስናዎች እንዳሉት የገለጹት ብፁዕ ካርዲናል ባልዶ ሬይና፥ አብሮ የመኖር ልምድን በማስታወስ ሲናገሩ፥ ከውስብስብ የባሕል ለውጥ ነፃ አለመሆናቸውን እና ይህንንም አምነው ተቀብለው ብዙ ጊዜ ከየቦታው ለሚደርሱባቸው ጫናዎች ምላሽ የሚሰጡበትን መንገድ በመፈለግ ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል።
ብፁዕ ካርዲናል ባልዶ ሬይና በመጨረሻም፥ በቅዱስነታቸው የእረኝነት አገልግሎት ተባባሪዎች በመሆናቸው የተሰማቸውን ክብር እና ፍቅር ገልጸው፥ ለእግዚአብሔር እቅድ ባላቸው ታዛዥነት የሚወዱትን ሀገረ ስብከታቸውን ይበልጥ ውብ እና ቅዱስ ለማድረግ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማድረግ ቃል መግባታቸውን አረጋግጠዋል።