ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ የማዳጋስካር ጳጳሳትን በቫቲካን ተቀብለው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ የማዳጋስካር ጳጳሳትን በቫቲካን ተቀብለው   (@Vatican Media)

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ጳጳሳት ዓይኖቻቸውን ከድሆች ላይ እንዳያነሱ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ለኢዮቤልዩ በዓል መንፈሳዊ ንግደት በማድረግ ወደ ሮም ከመጡት የማዳጋስካር ብጹዓን ጳጳሳት ጋር በቫቲካን ተገናኝተዋል። ቅዱስነታቸው ለብጹዓን ጳጳሳቱ ባስተላለፉት መልዕክት፥ ድሆች የወንጌል ማዕከል መሆናቸውን እንዲያስታውሱ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ዘንድሮ በ2025 ዓ. ም. እየተከበረ በሚገኝ የኢዮቤልዩ በዓል ተካፋይ ለመሆን ወደ ሮም መንፈሳዊ ንግደት ያደረጉት የማዳጋስካር ካቶሊክ ጳጳሳት ሰኞ ሰኔ 9/2017 ዓ. ም ቫቲካንን ጎብኝተው ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ጋር ተገናኝተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ የማዳጋስካር ካቶሊካዊ ጳጳሳትን በቫቲካን ተቀብለው ባደረጉት ንግግር፥ ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2019 ዓ. ም. በማዳጋስካር ካደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት እና ጳጳሳቱ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2022 ዓ. ም. ወደ ሮም ካደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት በኋላ ወደ ቫቲካን በኅብረት መጥተው የቅዱስ ጴጥሮስን መካነ መቃብር ለመሳለም መወሰናቸውን አድንቀዋል።

“የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ቅዱስ በሮችን በየቀኑ ከሚሻገሩ በሺዎች ከሚቆጠሩ ምዕመናን ጋር የተስፋ ተጓዦች መሆናቸው መልካም መሆኑን የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ አክለውም፥ ሁሉም ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ ተስፋ የመመላለስ ጸጋን እንዲያገኝ፥ በቅድሚያ ለራሳቸው ቀጥሎም በማዳጋስካር ላሉ ሰዎች የተስፋ ተጓዦች እንዲሆኑ መጠራታቸውን አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የማዳጋስካር ብጹዓን ጳጳሳት ሐዋርያዊ ደስታችውን እና ፈተናዎቻቸውን ካዳመጡ በኋላ ባስተላለፉት መልዕክት፥ ሕያው የወንጌል ምልክት በመሆን ከምእመናን ጋር መጓዝን እንዲቀጥሉ አበረታተዋቸዋል።

እያንዳንዳችሁ በአገልግሎታችሁ የመጀመሪያ ተባባሪዎች እና የቅርብ ወንድሞቻችሁ ለሆኑት ካኅናት እንዲሁም ራሳቸውን ለአገልግሎት ለሰጡ ገዳማውያን እና ገዳማውያት ልዩ እንክብካቤ አድርጉ” በማለት ጳጳሳትን አበረታትተዋል።

የማዳጋስካር ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የሚስዮናዊነት ሕይወትን ያደነቁት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ከእነርሱ በፊት የነበሩ በተለይም የሚስዮናዊው የሄንሪ ደ ሶላዥ እና የአገሪቱ የመጀመሪያው ሰማዕት ቅዱስ ዣክ በርቲዩ ፈለግ እንዲከተሉ አደራ ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ጳጳሳቱ ዓይኖቻቸውን ከድሆች ላይ እንዳያነሱ በማሳሰብ፥ “ድሆች የወንጌል ማዕከል እና የምሥራቹን ቃል እንዲቀበሉ የተጠሩ ናቸው” ሲሉ ገልጸዋቸዋል።

ሁሉም ጳጳሳት በድሆች ላይ የሚታየውን የኢየሱስ ክርስቶስ መልክ እንዲመለከቱ ጋብዘው፥ በኅብረተሰቡ ለተናቁት ዘወትር በመጨነቅ እንክብካቤን እንዲያደርጉላቸው አደራ ብለዋል።

ቅዱስነታቸው ለማዳጋስካር ብጹዓን ጳጳሳት ያደረጉትን ንግግር ሲያጠቃልሉ፥ ጳጳሳቱ የማዳጋስካርን የተፈጥሮ ውበት በመጠበቅ፥ ሁሉም ሰው የጋራ መኖሪያ ምድራችንን እንዲንከባከብ በመጋበዝ፥ ፍጥረትን መንከባከብ የትንቢታዊ ተልዕኳቸው ዋና አካል እንደ ሆነ አስረድተዋል።

“ጉዳት ደርሶበት የሚያቃስተውን ፍጥረት ተንከባከቡት” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ፍጥረትን በፍትህና በሰላም የመጠበቅ ጥበብን ምዕመናኖቻችሁን አስተምሯቸው” ብለዋል።

 

17 Jun 2025, 17:29