ፈልግ

የሩስያ እና የዩክሬይን ጦርነት የሩስያ እና የዩክሬይን ጦርነት 

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ “ጦርነት ምንጊዜም ሽንፈት ነው!” ሲሉ ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎች ከቀደመው ጊዜ እጅግ ወደ ላቀ አረመኔያዊ አደጋ ላይ እንደሚመሩ አስጠነቀቁ። ቅዱስነታቸው ከዚህም ጋር፥ ጦርነት ሁል ጊዜ ሽንፈት እንደሆነ፣ በሰላም የሚጠፋ ነገር እንደሌለ፣ ነገር ግን በጦርነት ሁሉ ሊጠፋ እንደሚችል የዓለም መሪዎችን አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ረቡዕ ሰኔ 11/2017 ዓ. ም. ሳምንታዊ ጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸውን ባቀረቡት ዕለት እንደተናገሩት፥ “ጦርነት ከሚካሄድባቸው አካባቢዎች በተለይም ከዩክሬን፣ ከኢራን፣ ከእስራኤል እና ከጋዛ በሚሰሙ ጩኸቶች ምክንያት የቤተ ክርስቲያን ልብ በሐዘን ቆስሏል” ብለዋል ።

ቅዱስነታቸው በዕለቱ ባስተላለፉት መልዕክት፥ “ጦርነትን መልመድ የለብንም” ብለው፥ ኃይለኛ እና የተራቀቁ የጦር መሣሪያዎችን የመጠቀም ፈተናን መቀበል የለብንም ሲሉ አጽንኦት ሰጥተው፥ ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎች ከቀደመው ጊዜ እጅግ ወደ ላቀ አረመኔያዊ አደጋ ሊሚመሩ እንደሚችሉ አስጠንቅቋል።

“ጦርነት ምንጊዜም ሽንፈት ነው!” በማለት ያስተላለፉትን የነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን መልዕክት በማስተጋባት፥ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ቤተ ክርስቲያንን የመሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛ “ከሰላም ጋር የሚጠፋ ምንም ነገር የለም፣ በጦርነት ሁሉም ነገር ሊጠፋ ይችላል” በማለት የተናገሩትን አስታውሰዋል።

ሩስያ በዩክሬን ላይ የምትፈጽመው ጥቃት ቀጥሏል

ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በዩክሬን በሚገኙ የሲቪል ኢላማዎች ላይ የሩስያ የአየር ድብደባ ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፥ በአንድ ሌሊት ብቻ በሰው አልባ አውሮፕላኖች እና በሚሳኤል ጥቃት ቢያንስ 18 ሰዎች ሲሞቱ 151 ቆስለዋል። የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘሌንስኪ ጥቃቱ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በየካቲት 2022 ዓ. ም. አገራቸው በሩሲያ ሙሉ በሙሉ ከተወረረች በኋላ እጅግ አሰቃቂ ከተባሉት መካከል አንዱ እንደሆነ ተናግረዋል።

የእስራኤል እና የኢራን ግጭት

እስራኤል የኢራንን የኒውክሌር መርሃ ግብር ለማጥፋት ያነጣጠረ ጥቃት እየፈፀመች ባለችበት ወቅት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የኢራን ዋና ከተማ ቴህራንን እየሸሹ እንደሆነ ታውቋል። እስራኤል በመጀመሪያ ዙር በፈጸመችው ጥቃት ከ220 በላይ ሰዎች መሞታቸው ተዘግቧል፤ ከነዚህም መካከል የጦር መሪዎች እና የኒውክሌር ሳይንቲስቶች ይገኙበታል። የእስራኤል ወታደራዊ ምንጮች የአየር ሃይላቸው በቴህራን በአንድ ሌሊት 20 ኢላማዎችን መምታቱን ተናግረዋል።

በምላሹ ኢራን 400 ያህል ሚሳኤሎችን ወደ እስራኤል ያስወነጨፈች ሲሆን በዚህም ወደ 40 የሚጠጉ ሚሳኤሎች በእስራኤል የአየር መከላከያ ማዕከልን ኢላማ አድርገውታል። በጥቃቱ 24 ሰዎች መገደላቸውን የእስራኤል ባለስልጣናት አስታውቀዋል።

የእስራኤል ታንኮች ዕርዳታ የሚሹ ሰዎችን መግደል

በጋዛ የእስራኤል ሃይሎች የሃማስን የፖለቲካ እና ወታደራዊ ድርጅት ለማጥፋት በሚመስል መልኩ ወታደራዊ ዘመቻቸውን ቀጥለዋል።

ማክሰኞ ሰኔ 10/2017 ዓ. ም. የእስራኤል ታንኮች ሰብዓዊ ዕርዳታ የጫኑ መኪኖችን በመጠባበቅ ላይ በነበሩ ሰዎች ላይ ተኩስ መክፈቱ ተዘግቧል። በሥፍራው የተገኙ የሕክምና ባለሙያዎች እንደተናገሩት፥ በጥቃቱ ወደ 60 የሚጠጉ ሰዎች መሞታቸውን እና ከ220 በላይ መቁሰላቸውን አስታውቀው፥ 20 ያህሉ በአስጊ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የጋዛ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንደገለጸው፥ ከግንቦት ወር መጨረሻ ጀምሮ ወደ 400 የሚጠጉ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን፣ ከ3,000 በላይ መቁሰላቸውን እና ዕርዳታን ለማግኘት በሚጠባበቁ ሰላማዊ ሰዎች ላይ በተከፈተው ተኩስ በርካቶች መጎዳታቸውን አስረድቷል። ሚኒስቴሩ እንዳለው እስራኤል በጋዛ ላይ ወረራ ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ ከ55,000 በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን ገልጾ፥ በሁከቱ ከሞላ ጎደል ጠቅላላው የጋዛ ሕዝብ መፈናቀሉን አስታውቋል።

18 Jun 2025, 17:19