ፈልግ

የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛ የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛ  

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ታሪካዊውን የሰላም ጥሪ በድጋሚ አቀረቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበስቡት ምዕመናን ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ክፍል ባቀረቡበት ወቅት የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 1939 ዓ. ም. ዓለም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት አፋፍ ላይ በነበረችበት ወቅት በሬዲዮ ያስተላለፉትን የሰላም ጥሪ በድጋሚ አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ረቡዕ ሰኔ 11/2017 ዓ. ም. ባቀረቡት ሳምንታዊ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ማጠቃለያ ላይ፥ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከመጀመሩ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛ የተናገሯቸውን አስደናቂ ቃላት በማስታወስ አሁን የሚታየው ውጥረት እና ሁከት ተወግዶ ሰላም እንዲሰፍን በማለት ጥሪ አቅርበዋል።

ቅዱስነታቸው በሰላም ጥሪያቸው መልዕክታቸው፥ የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ነሐሴ 24/1939 ዓ. ም. ያስተላለፉትን ታሪካዊ የሬዲዮ መልዕክት በመጥቀስ፥ ዓለም አቀፋዊ ግጭት እንዲወገድ ፈልገው ያቀረቡትን ተመሳሳይ የሰላም ጥሪ ደግመዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 11ኛን ተከትለው መላዋ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያንን የመሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛ ወደ መንበረ ጴጥሮስ ከመምጣታቸው በፊት ለዘጠኝ ዓመታት ያህል የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ሆነው ማገልገላቸው ይታወሳል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛ የሰላም ጥሪያቸውን ያስተላለፉት፥ ጦርነት የማይቀር መሆኑን የሚገልጸው የናዚ-የሶቪየት ስምምነት ዜና ወደ ቫቲካን ከደረሰ በኋላ እንደ ነበር ይታወሳል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛ በሰላም ጥሪያቸው ላይ “ፍትህ የሚመጣው በጦር መሣሪያ ሳይሆን በምክንያታዊነት ነው” ብለው፥ “በፍትህ ላይ ያልተመሠረቱ መንግሥታት እግዚአብሔር ያልፈቀዳቸው እና ሥነ-ምግባር የሌለው ፖለቲካ ተመልሶ አራማጆችን ይከዳቸዋል” ሲሉ ተናግረዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛ አክለውም፥ “አደጋው ቅርብ ቢሆንም የማስቀረት ዕድል እና ጊዜ አሁንም አለ” ብለው፥ የሰላም ጎዳናን በመከተል የሚጠፋ ምንም ነገር እንደሌለ፣ ነገር ግን ጦርነት ውድመትን እንደሚያስከት፥ በመሆኑም ሰዎች ወደ መግባባት ለመድረስ የሚያስችላቸውን ድርድር እንደገና መቀጠል እንዳለባቸው አሳስበዋል። በበጎ ፈቃድ አንዳቸው የሌላውን መብት አክብሮ በመደራደር ቅን ስምምነቶች ሊገኙ እንደሚችሉ እና ወደ ስኬት እንደሚመሩ አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛ ያሰሙትን የሰላም ጥሪ ንግግር ያዘጋጁት፥ በወቅቱ የቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤት ተተኪ ጸሐፊ የነበሩት እና በኋላም ለኩላዊ ቤተ ክርስቲያን መሪነት የተመረጡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ ስድስተኛ እንደ ነበሩ ይታወሳል።

ያልተሰማ ማስጠንቀቂያ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛ ምንም እንኳን የሰላም ተማጽኖ ጥሪያቸውን ቢያቀርቡም ድምጻቸው ሳይሰማ ቅረቶ፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ መስከረም 1/1939 የጀርመን ወታደሮች ፖላንድን በመውረራቸው ሁለተኛው የዓለም ጦርነት መቀስቀሱ ይታወሳል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ እነዚያን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛ ቃላት ዛሬ በማስታወስ፥ ዓለም ከጥፋት ይልቅ ውይይትን፣ ካለፈው የጨለማ ጊዜ ይልቅ ዛሬ ብርሃንን በመፈለግ፥ ዓለም ከጦርነት ይልቅ ሰላምን እንዲመርጥ በድጋሚ ጋብዘዋል።

ከጊዜ ወደ ጊዜ ውጥረቶች እና ብጥብጦች እየጨመሩ በመጡበት በዚህ ጊዜ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን የሰላም ጥሪን፥ አሁንም ለሰላም መንገዱ ክፍት ቢሆንም ነገር ግን ድፍረትን፣ ህሊናን እና ቁርጠኝነትን ይጠይቃል በማለት ከአጣዳፊነቱ ጋር አስተጋብተዋል።

 

19 Jun 2025, 16:41