ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ “እግዚአብሔር የማይሰማው ጩኸት የለም!”
ክቡራት ክቡራን፥ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛን አስተምህሮ ትርጉም ከማቅረባችን አስቀድመን፥ ያስተነተኑበትን የቅዱስ ወንጌል ጥቅስ እናነብላችኋለን፥
“ኢየሱስም ቆም ብሎ ‘ጥሩት’ አላቸው። እነርሱም ዓይነ ስውሩን፥ አይዞህ፤ ተነስ፤ ይጠራሃል’ አሉት። እርሱም ልብሱን ጥሎ ብድግ በማለት፥ ተነስቶ ወደ ኢየሱስ መጣ።ኢየሱስም ‘ምን እንዳደርግልህ ትፈልጋለህ’ አለው። ዓይነ ስውሩም፥ ‘መምህር ሆይ፤ እንዳይ እፈልጋለሁ’ አለው። ኢየሱስም፥ ‘ሂድ፥ እምነትህ አድኖሃል’ አለው። ወዲያውም ዓይኑ በራለት፤ በመንገድም ኢየሱስን ተከትሎ ሄደ” (ማር. 10: 49-52)።
ክቡራት እና ክቡራን፥ ከዚህ ቀጥሎ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በዕለቱ ያቀረቡትን የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ትርጉም ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን፥
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ! በዚህ በዛሬው የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ አስፈላጊ በሆነው በሌላው የኢየሱስ ሕይወት ገጽታ ማለትም በፈውሶቹ ላይ ትኩረት ማድረግ እፈልጋለሁ። ስለዚህ በሕይወታችሁ ውስጥ የተቆለፉ እና የታገዱ የሚመስላችሁን እንዲሁም እጅግ የሚያማችሁ እና ደካማ የሆኑ ክፍሎቻችሁን በኢየሱስ ክርስቶስ ልብ ፊት እንድታቀርቡ እጋብዛችኋለሁ። ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅሶአችንን ሰምቶን እንዲፈውሰን በእምነት እንጠይቀው!
በዛሬው አስተንትኖአችን ውስጥ የምናገኘው ሰው፥ የጠፋን መስሎ ቢሰማን እንኳ ተስፋ መቁረጥ እንደሌለብን እንድንገነዘብ ያግዘናል። ይህ ሰው ኢየሱስ በኢያሪኮ ያገኘው ዓይነ ስውር እና ለማኝ በርጤሜዎስ ነው (ማር. 10፡46)። ቦታው ትልቅ ሥፍራ የሚሰጠው ነው። ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ ሲነሳ ጉዞውን የጀመረው ከባሕር ወለል በታች በምትገኝ በኢያሪኮ ከተማ ነበር። በእርግጥም ኢየሱስ ክርስቶስ በሞቱ ወደ ገደል የወደቀውን እና እያንዳንዳችንን የሚወክለውን አዳምን ከወደቀበት ሊያነሳ ሄደ።
በርጤሜዎስ ማለት የጤሜዎስ ልጅ ማለት ነው። ሰውየው ከብዙ ሰዎች ጋር ባለው ግንኙነት ይታወቃል። ያም ሆኖ ግን ብቸኛ ሰው ነው። ይህ ስም ግን ‘የክብር ልጅ’ ወይም ‘አስደናቂ’ ማለት ሊሆን ይችላል። እርሱ ራሱን ካየበት ሁኔታ ፈጽሞ ተቃራኒ ነው። ስሙ በአይሁድ ባሕል ውስጥ እጅግ አስፈላጊ ስለሆነ በርጤሜዎስ በሚጠራበት አኳኋን መኖር ተስኖታል።
ኢየሱስን ተከትለው ከሚራመዱ ሰዎች እንቅስቃሴ በተለየ ሁኔታ በርጤሜዎስ በአንድ ቦታ ቆሞ ነበር። ወንጌላዊው እንደሚለን በርጤሜዎስ በመንገድ ዳር ተቀምጦ ስለነበር ከነበረበት አስነስቶ ጉዞውን እንዲቀጥል የሚረዳው ሰው ያስፈልገው ነበር ይለናል።
መውጫ የጠፋ በሚመስል ሁኔታ ውስጥ ስንገኝ ምን ማድረግ እንችላለን? በርጤሜዎስ በውስጣችን ያሉትን እና የእኛ የሆኑትን ሃብቶች እንዴት ጥቅም ላይ ማዋል እንደምንችል ያስተምረናል። በርጤሜዎስ ለማኝ ነው። ዕርዳታን እንዴት መጠየቅ እንዳለበት ያውቃል። በእርግጥም ድምጹን ከፍ አድርጎ መለመን ይችላል! አንድን ነገር ከልብ ከፈለጋችሁት፥ ያንን ነገር ለማግኘት የምትችሉትን ሁሉ ታደርጋላችሁ። ሌሎች ሲነቅፏችሁ፣ ሲያዋርዷችሁ እና እንድትተውት ሲነግሯችሁ፥ በእውነት የምትመኙት ከሆነ ጥረታችሁን ትቀጥላላችሁ።
የበርጤሜዎስ ጩኸት፥ በማርቆስ ወንጌል ምዕ. 10:47 ላይ እንደተገለጸው፥ ‘የዳዊት ልጅ፥ ኢየሱስ ሆይ፤ ማረኝ! (ቁ. 47) የሚል ነው። በምሥራቃውያን ወግ ውስጥ በጣም የታወቀ ጸሎት ሆኗል። እኛም፥ ‘የእግዚአብሔር ልጅ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ፥ እኔን ኃጢአተኛውን ማረኝ’ ብለን መለመን እንችላለን።
በርጤሜዎስ ዓይነ ስውር ነው። ነበር ግን በሚገርም ሁኔታ እርሱ ከሌሎቹ በተሻለ ሁኔታ ‘ይመለከታል’። ኢየሱስ ክርስቶስ ማን እንደሆነ ያውቃል! ወደ ኢየሱስ ከመጮሁ በፊት ኢየሱስ ቆሞ ብሎ እንዲጠራው አደረገው (ማር. 11.49)። ምክንያቱም ምንም እንኳን እኛ እርሱን እንደምንጠራው ባናስተውልም እግዚአብሔር የማይሰማው ጩኸት የለም (ዘጸ. 2፡23)። ኢየሱስ ወደ ዓይነ ስውሩ ሰው ዘንድ ወዲያው አለመሄዱ እንግዳ ይመስላል። ነገር ግን ካሰብነው የበርጤሜዎስን ሕይወት እንደገና ለማነቃቃት የተጠቀመበት መንገድ ነው። እንደገና እንዲነሳ አደረገው፤ በእግሩ መራመድ እንደሚችልም ያምናል። ያ ሰው እንደገና በእግሩ ሊቆም ይችላል። ከሞት አፋፍ ጭንቀት ሊወጣ ይችላል። ነገር ግን ይህን ለማድረግ ትርጉም ያለውን ምልክት ማሳየት ነበረበት። ልብሱንም አውልቆ መጣል ነበረበት (ማር. 11:50)።
ለአንድ ለማኝ ልብስ ሁሉ ነገር ነው፤ ደኅንነቱ ነው፣ ቤቱ ነው፣ መከላከያው ነው። ሕግ እንኳን የለማኙን መጎናጸፊያ ያስጠብቃል። በመያዣነት የተወሰደ ከሆነም ማታ ላይ እንዲመለስ ይደነግጋል (ዘፀ. 22፡25)። ነገር ግን ብዙውን ጊዜ በመንገዳችን ላይ የሚቆሙ ነገሮች የእኛ ግልጽ ደህንነቶች ናቸው። እራሳችንን ለመከላከል የምናደርጋቸው ቢሆንም ነገር ግን በምትኩ እንዳንራመድ የሚከለክሉን ናቸው። በርጤሜዎስ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ሄዶ ራሱን ለመፈወስ ሁሉንም ማድረግ ነበረበት። ይህ በማንኛውም የፈውስ ጉዞ ውስጥ መሠረታዊ እርምጃ ነው።
ኢየሱስ ‘ምን እንዳደርግልህ ትፈልጋለህ?’ (ማር. 11:51) ሲል የጠየቀው ጥያቄ እንግዳ ይመስላል። ነገር ግን እንደ እውነቱ ከሆነ ከሕመማችን መፈወስ እንደምንፈልግ አያረጋግጥም። አንዳንዴ ሃላፊነት ላለመውሰድ ብለን ዝም ማለትን እንመርጣለን። የበርጤሜዎስ ምላሽ ጥልቅ ነው፥ ‘አናብለፔይን’ የሚለውን የዕብራይስጥ ግስ ተጠቀመ። ትርጉሙም፥ ‘እንደገና ማየት’ ማለት ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ‘ቀና ብሎ ወደ ላይ መመልከት’ ማለት ብለን መተርጎም እንችላለን። በእርግጥ በርጤሜዎስ እንደገና ማየት ብቻ አልፈለም። ክብሩንም ጭምር መልሶ ማግኘት ይፈልጋል! ቀና ብለን ለማየት አንገታችንን ቀና ማድረግ አለብን። አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ሕይወት ስላዋረዳቸው ክብራቸውን እንደገና ማግኘት ይፈልጋሉ።
በርጤሜዎስን እና እያንዳንዳችንን የሚያድነን እምነት ነው። ኢየሱስ የሚፈውሰን ነፃ እንድንሆን ነው። ኢየሱስ በርጤሜዎስን እንዲከተለው አልጠራውም። ነገር ግን እንዲሄድ እና መንገዱ እንዲቀጥ ነገረው (ማር. 11:52)። ሆኖም ግን ወንጌላውይው በርጤሜዎስ ኢየሱስን መከተል እንደጀመረ በመናገር ታሪኩን ያጠናቅቃል። በርጤሜዎስም መንገዱ የሆነውን ኢየሱስን መከተልን በነጻነት መረጠ!
ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፥ ሕመማችንን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ እና ወደምንወዳቸው ሰዎች ፊት በእምነት እናቅርብ። የጠፉ እና መውጫ ያጡ መስሎ የሚሰማቸውን ሰዎች ስቃይ ወደ ኢየሱስ ፊት እናቅርብ። ስለ እነርሱ እንጩህ! ኢየሱስ ቆም ብሎ እንደሚሰማን እርግጠኞች እንሆናለን።”