ር. ሊ. ጳ. ሌዮ 14ኛ፥ ዲፕሎማቶች ሰላምን በፍትሕ፣ በእውነት እና በተስፋ እንዲገነቡ አሳሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ 14ኛ፥ በሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ መንበር ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያንን እንዲመሩ ከተመረጡ ከአንድ ሳምንት በኋላ በቅድስት መንበር ዕውቅና የተሰጣቸው የዲፕሎማሲ ቡድን አባላትን ዓርብ ግንቦት 8/2017 ዓ. ም. ማለዳ በቫቲካን ተቀብለው ንግግር አድርገዋል።
ቅዱስነታቸው ለዲፕሎማሲ ማኅበረሰብ የመጀመሪያ ንግግር ባደረጉበት ወቅት፥ በቅድስት መንበር ዕውቅና ለተሰጣቸው ዲፕሎማሲያዊ አካላት በሙሉ ተጠሪ የነበሩት ተሰናባቹ የቆጵሮስ አምባሳደር ጆርጅ ፑሊዴስ ለዓመታት ላበረከቱት ጉልበት፣ ላሳዩት ቁርጠኝነት እና ደግነት እንዲሁም ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና ከቀደሙት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ያገኙትን ክብር በማስታወስ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
ቅዱስነታቸው በመቀጠል ለአገራቱ ተወካይ ዲፕሎማቶች ባስተላለፉት መልዕክት፥ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሁሉንም የሰው ዘር ለማገልገል ያላትን ቁርጠኝነት በማረጋገጥ፥ ዲፕሎማሲያዊ ማኅበረሰብ እንደ ቤተሰብ ደስታን እና ሐዘንን የሚካፈል በሰብዓዊ እና መንፈሳዊ እሴቶች ላይ የተመሠረተ እንደሆነ አስገንዝበው፥ በዚህ ቤተሰብ ውስጥ ቤተ ክርስቲያን ልዩ መብቶችን ሳትፈልግ ነገር ግን ልዩ የዲፕሎማሲ መንገድ በሆነው ሐዋርያዊ ጉዳይ ላይ ተመሥርታ የመገናኛ መንገዶችን ለመገንባት ዕድሎችን እንደምትፈልግ ገልጸዋል።
ይህ ተልዕኮ፥ ለድሆች እና ለተገለሉ ሰዎች ያላቸውን ቁርጠኝነት በተግባር የገለጹ፥ እንዲሁም ለፍጥረት ጥበቃ እና ለሰው ሠራሽ አስተውሎት “አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ” ማደግ ትኩረት የሰጡ የነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ትሩፋት የሚያንጸባርቅ ዘላቂ ተነሳሽነት ሆኖ እንደሚቀጥል አስረድተዋል።
በሰሜን እና በደቡብ አሜሪካ እንዲሁም በአውሮፓ የነበራቸውን የሐዋርያነት ሕይወታቸውን የስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ 14ኛ፥ ቤተ ክርስቲያን በዓለም ዙሪያ ካሉ ሕዝቦች እና መንግሥታት ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር ድንበሮችን የሚያቋርጡ ግንኙነቶችን ለማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል።
ሰላም፣ ፍትህ እና እውነት የተባሉ ሦስት ምሰሶዎች
ሰላም፣ ፍትህ እና እውነት የሚሉ ሦስት አስፈላጊ ቃላትን የጠቀሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ 14ኛ፥እነዚህ ሦስቱ ለቤተ ክርስቲያን የሚስዮናዊነት አገልግሎቶች ዋና ምሰሶዎች እና የቅድስት መንበር ዲፕሎማሲ መሠረት መሆናቸውን አስረድተዋል።
ሰላም
“ሰላም የጦርነት አለመኖሩን ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ጥረትን የሚጠይቅ የኢየሱስ ክርስቶስ የመጀመሪያ ስጦታ ነው” በማለት ገልጸዋል። እውነተኛ ሰላም ኩራትን እና በቀልን በመቃወም በትህትና እና ጥንቃቄ በተመላበት ንግግር ከሰው ልብ ውስጥ የሚጀምር መሆን አለበት ብለው፥ ሰውን የሚያቆስሉ እና የሚገድሉ የጦር መሣሪያዎች ብቻ ሳይሆኑ ቃላትም ጭምር መሆናቸውን አስገንዝበዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ አሥራ አራተኛ ይዚህ መነሻ በማድረግ፥ የሃይማኖት ነፃነት እና በሃይማኖቶች መካከል የሚደርግ ውይይት ሰላምን በማጎልበት ረገድ የማይተካ ሚና እንዳለው አጽንኦት ሰጥተዋል። ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለመላው ዓለም እና ለሮም ከተማ ነዋሪዎች ባስተላለፉት የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ መልዕክታቸው፥ “እውነተኛ የጦር መሣሪያ ትጥቅ መፍታት ካልተካሄደ ሰላምን ማምጣት አይቻልም” ያሉትን በመድገም፥ የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እና የጦር መሣሪያ እሽቅድድም እንዲቆም ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
ፍትህ
ፍትህ የሚለውን ሁለተኛ ነጥብ በማስመልከት፥ በቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ 13ኛ አስተምህሮ እና በቤተ ክርስቲያን ጥልቅ የማኅበራዊ አስተምህሮ ባህል ላይ በማስተንተን እንደተናገሩት፥ በዓለማችን ውስጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን እኩልነት ማጣት ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ 14ኛ፥ የአገራት መሪዎች መዋዕለ ንዋያቸውን በቤተሰብ እንክብካቤ ላይ እንዲያፈሱ እና የእያንዳንዱ ሰው ልጅ ክብርን እንዲያስጠብቁ አሳስበዋል። ከስደተኛ ቤተሰብ መወለዳቸውን በማስታወስ በሰጡት አጠር ያለ አስተያየትም፥ ዜግነት ሳይገድበው በሁሉም ሕዝቦች የጋራ ሰብዓዊ ክብር ላይ የተመሠረተ አንድነት ሊኖር እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።
እውነት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ አሥራ አራተኛ፥ ሦስተኛ እና የመጨረሻው ነጥብ የሆነውን “እውነት” በማስመልከት ሲናገሩ፥ እውነት ለትክክለኛ እና ሰላማዊ ግንኙነት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው፥ እውነታ በተዛባበት ዓለም ውስጥ በተለይም በአዲሱ የማኅበራዊ መገናኛ ዘመን መግባባት አስቸጋሪ ቢሆንም ቤተ ክርስቲያን እውነትን በበጎ አድራጎት የመናገር ግዴታ እንዳለባት አሳስበዋል።
“እውነት፥ ረቂቅ መርህ ሳይሆን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር መገናኘት ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ “የሰው ልጅ እንደ ስደት፣ ቴክኖሎጂ ወይም አካባቢያዊ ቀውስ የመሳሰሉ አስቸኳይ መፍትሄ የሚጠይቁ ተግዳሮቶችን በአንድነት እና በጋራ ዓላማ እንዲጋፈጣቸው የሚያስችለው ይህ እውነት ነው” ሲሉ አስረድተዋል።
አዲስ መንገድ የሚገኝበት ተስፋ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ አሥራ አራተኛ በንግግራቸውን ማጠቃለያ፥ አገልግሎታቸውን በኢዮቤልዩ የተስፋ ዓመት አውድ ውስጥ በማስቀመጥ፥ ይህም የመለወጥ፣ የመታደስ እና ከሁሉም በላይ ግጭትን ወደ ኋላ የሚተውበት ጊዜ እንደሆነ አስረድተዋል።
በመጨረሻም፣ ቅድስት መንበር ከእያንዳንዱ አገር ጋር በኅብረት በመጓዝ፥ ሁሉም ሰው በክብር እና በሰላም የሚኖርበትን ዓለም ለመገንባት ያላትን ቁርጠኝነት በማደስ፥ እንደ ዩክሬን እና ቅድስት አገር ያሉ አስከፊ መከራ በሚደርስባቸው ቦታዎችም ቁርጠኝነቷን እንደምትቀጥል ያላቸውን ተስፋ በመግለጽ፥ ዓርብ ግንቦት 8/2017 ዓ. ም. ማለዳ በቫቲካን ለተቀበሏቸው ዲፕሎማሲያዊ አካላት ያደረጉትን ንግግር ደምድመዋል።