ር. ሊ. ጳ. ሌዮ 14ኛ፥ በጦርነት ምክንያት የሚሠቃዩትን መርሳት እንደማይገባ አሳሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ አሥራ አራተኛ፥ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን እና በዓሉ ላይ ለተገኙት እንግዶች በመሩት የሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪነት የአገልግሎት መጀመሪያ መስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ማጠቃለያ ላይ ባሰሙት ንግግር፥ በጦርነት ምክንያት ለሚሰቃዩ ሰዎች ሰላም እንዲወርድ ተማጽነዋል።
በመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙትን ከ200,000 በላይ ምዕመናንን እና በርካታ ልኡካን አመስግነው፣ ለልዩ ልዩ አገራት፣ ለአብያተ ክርስቲያናት እና ለቤተ እምነት ተወካዮች ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ 14ኛ በመስዋዕተ ቅዳሴው ማጠቃለያ ላይ ባሰሙት ንግግር፥ “ከእምነት እና ከኅብረት በምናገኘው ደስታ በጦርነት ምክንያት የሚሠቃዩ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ፈጽሞ መርሳት አንችልም” ብለዋል።
በእስራኤል እና በሐማስ መካከል ጦርነት በቀጠለበት ወቅት በጋዛ ውስጥ ከጦርነት አደጋ የተረፉት ህጻናት፣ ቤተሰቦች እና አረጋውያን ለረሃብ መዳረጋቸውን አስታውሰዋል። ቅዱስነታቸው በተጨማሪም በምያንማር የተከሰቱ አዳዲስ ግጭቶች የንጹሐን ወጣቶች ሕይወት ማጥፋቱን ገልጸዋል።
በጦርነት የተሰቃየው የዩክሬን ሕዝብ ፍትሃዊ እና ዘላቂ ሰላምን የሚያመጣ ድርድር እንዲካሄድ መጠበቁንም የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ አሥራ አራተኛ ከሐዋርያዊ የአገልግሎት መጀመሪያ መስዋዕተ ቅዳሴን ሥነ-ሥርዓት በኋላ ከዩክሬኑ ፕሬዚዳንት አቶ ቮሎዲሚር ዘለንስኪ እና ከባለቤታቸው ጋር በግል ተገኝተዋል።
በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት በርካታ ምዕመናን ጋር ወደ እመቤታችን ማርያም የሰማይ ንግሥት ዘንድ ጸሎት ባቀረቡበት ወቅት ባሰሙት ንግግር፥ “ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመንፈስ አብረውን መሆናቸው እጅግ ተሰምቶናል” ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ አሥራ አራተኛ፥ የሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ ሆነው ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን በይፋ ሲጀምሩ፥ ካቶሊካዊ ምዕመናን የመልካም ምክር እናት የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዕርዳታን በጸሎት እንዲጠይቁ አደራ ብለዋል።
ቅዱስነታቸው በመጨረሻም፥ “በጦርነት የሚሰቃዩት ሰላምን በማግኘት የሚጽናኑበት እና ከሙታን ለተነሳው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምስክሮች የምንሆንበትን ጸጋ ትሰጠን ዘንድ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት እንማጸናለን” ሲሉ ንግግራቸውን ደምድመዋል።