ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ሌዮ 14ኛ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልዑካን የቀረበላቸውን ስጦታ ሲቀበሉ ር. ሊ. ጳ. ሌዮ 14ኛ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልዑካን የቀረበላቸውን ስጦታ ሲቀበሉ  (@Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ሌዮ አሥራ አራተኛ፥ “ጊዜው የውይይት እና የግንኙነት መንገድ ማመቻችያ ነው” ሲሉ ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ አሥራ አራተኛ፥ የቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ ሆነው ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን በጀመሩበት ማግሥት፣ ካቶሊካዊ ያልሆኑ የአብያተ ክርስቲያናት፣ የክርስቲያን ማኅበረሰቦች እና የሌሎች ቤተ እምነት ተወካዮችን በቫቲካን ተቀብለው ሰላምታ የተለዋወጡ ሲሆን፥ ይህም የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለክርስቲያኖች አንድነት እና በልዩ ልዩ የሃይማኖት ተቋማት መካከል ውይይት ለማካሄድ ያላቸውን ቁርጠኝነት በማስታወስ እንደሆነ ተገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ የቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ ሆነው ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን በይፋ በጀመሩበት እሑድ ግንቦት 10/2017 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በመሩት መስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ላይ ከተገኙት የአብያተ ክርስቲያናት እና የሌሎች ሃይማኖቶች ተወካዮች ጋር ዛሬ ሰኞ በቫቲካን ተገናኝተዋል።

ቅዱስነታቸው ለተወካዮቹ ባደረጉት ንግግር፥ ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዓለም አቀፍ ወንድማማችነት ላይ ማትኮራቸውን እና የቀደሙት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በተለይም የቅዱስ ዮሐንስ 23ኛ ትኩረትን በንግግራቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።

ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወንድማማችነትን በክርስቲያኖች የአንድነት እንቅስቃሴ እና በሌሎች የእምነት ተቋማት መካከል ውይይቶች እንዲበረታቱ ማድረጋቸውን፣ ከሁሉም በላይ የእርስ በርስ ግንኙነትን በማጎልበት፣ በአብያተ ክርስቲያን መካከል ያለው ትስስር ሳይቋረጥ ለሰብዓዊ ግንኙነት ዘወትር ዋጋ ይሰጡ እንደ ነበር ገልጸው፥ ለምስክርነታቸውም ዋጋን መስጠት እንድንችል የእግዚአብሔርን ዕርዳታ ለምነዋል።

እውነተኛ አንድነት የእምነት አንድነት ነው!

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ አሥራ አራተኛ፥ ለሌሎች አብያተ ክርስቲያናት እና የቤተ ክርስቲያን ማኅበረሰቦች ለመጀመሪያ ጊዜ ባደረጉት ንግግር፥ የኒቂያ ጉባኤ 1,700 ኛ ዓመት መታሰቢያን በማስታወስ፥ በክርስቲያኖች መካከል ያለው አንድነት በእምነት ውስጥ ያለው አንድነት ብቻ ሊሆን እንደማይችል አጽንዖት ሰጥተዋል።

የሮም ጳጳስ እንደመሆናቸው በሁሉንም ክርስቲያኖች መካከል ያለውን ሙሉ እና የሚታይ ኅብረትን ማሳደግ ቅድሚያ የሚሰጡት አንዱ ጉዳይ እንደሆነም አክለዋል።

ከዚሁም ጋር በክርስቲያኖች አንድነት እና በሲኖዶሳዊነት መካከል ያለውን የጠበቀ ግንኙነት በማስታወስ፣ “የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶሳዊነትን በማስተዋወቅ ረገድ ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ለመከተል ያላቸውን ቁርጠኝነት ለልዑካኑ አረጋግጠዋል።

በሰብዓዊ ወንድማማችነት መንፈስ ውስጥ ያለው የጋራ መንገድ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ አሥራ አራተኛ፥ ክርስቲያን ያልሆኑ የቤተ እምነት ተወካዮችን በመጥቀስ እንደተናገሩት፥ ሰብዓዊ የወንድማማችነት መንፈስ የጋራ መንገዳችን በመሆኑ ሁሉንም ሰው የሚያሳትፍ መሆኑን መረዳት ይቻላል  ብለዋል።

“የምንገኝበት ጊዜ ውይይት የሚደረግበት እና እርስ በርስ የምንገናኝበትን ድልድይን የምንገነባበት ነው” ሲሉ አስገንዝበው፥ ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሃይማኖቶች መካከል ውይይት ለማድረግ ያደረጉትን አስደናቂ ጥረት በድጋሚ አስታውሰዋል።

ስለ ሰብዓዊ የወንድማማችነት ሠነድ የጠቀሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ 14ኛ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቃላቸው እና በተግባራቸው አዳዲስ የመገናኛ መንገዶችን መክፈታቸውን በመግለጽ፥  የውይይት ባህልን እንደ መንገድ፣ የጋራ ትብብር እንደ የሥነ ምግባር ደንብ፣ እርስ በርስ መግባባትን እንደ ዘዴ እና ደረጃ መጠቀማቸውን አስረድተዋል።

ከአይሁድ እምነት፣ ከእስልምና እና ከሌሎች ሃይማኖታዊ ወጎች ጋር ያለው ግንኙነት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ 14ኛ፥ ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ በሃይማኖቶች መካከል ያለውን ግንኙነት በማስመልከት ይፋ ያደረገውን “የእኛ ዘመን” የተሰኘ ሠነድ በመከተል፥ “ክርስቲያኖች እና የአይሁድ እምነት ተከታዮች በጋራ የሚካፈሏቸውን መንፈሳዊ ቅርሶች በማጉላት፥ ግጭቶች እና አለመግባባቶች በሚፈጠሩበት ጊዜ በማኅበረሰቦች መካከል ለሚካሄድ የሥነ-መለኮታዊ ውይይት አስፈላጊነት አጽንኦት ሰጥተዋል።

ቅዱስነታቸው በመቀጠልም፥ በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን እና በሙስሊሞች መካከል ያለውን ግንኙነት የሚመለከት የንግግር እና የወንድማማችነት ጥረት እያደገ መምጣቱን በመግለጽ፥ “በጋራ መከባበር እና በኅሊና ነፃነት ላይ የተመሠረተ አካሄድ በማኅበረሰቦቻችን መካከል ድልድይ ለመገንባት የሚያስችል ጠንካራ መሠረት ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ 14ኛ በመጨረሻም፥ የሂንዱ፣ የቡዳ፣ የጄኒ እና የሌሎች እምነቶች ተወካዮችን ባነጋገሩበት ወቅት፥ በዓመፅ እና በግጭት በቆሰለው ዓለም ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን ላደረጉት አስተዋጽኦ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

የሃይማኖት ተቋማት በጋራ መሥራት ጦርነትን፣ የጦር መሣሪያ እሽቅድምድም እና ኢ-ፍትሐዊ የሆነ የኢኮኖሚ ክፍፍልን ለመቃወም እንደሚረዳ እና ሰላምን በማምጣት፣ የጦር መሣሪያ ትጥቅ በመፍታት ወደ አጠቃላይ ልማት እንደሚያደርስ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

የበለጠ ሰላማዊ ዓለምን መገንባት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ አሥራ አራተኛ፥ ወንድማማችነትን በመመስከር የበለጠ ሰላም የሰፈነባት ዓለምን ለመገንባት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ እና ይህም በጎ የሆኑ ወንዶች እና ሴቶች በልባቸው የሚመኙት መሆኑን በማመን ንግግራቸውን ደምድመዋል።

በመጨረሻም ልዑካኑ የእግዚአብሔርን በረከቶች በልባቸው እንዲለምኑ በመጠየቅ፥ የእርሱ ​​ማለቂያ የሌለው ቸርነቱ እና ጥበቡ እንዲረዳን፥ እንደ ልጆቹ እርስ በርሳችን በወንድማማችነት እና በእህትማማችነት በመኖር ተስፋው በዓለም ላይ ሊያድግ ይገባል በማለት ንግግራቸውን ደምድመዋል።

 

19 May 2025, 17:26