ር. ሊ. ጳ. ሌዮ 14ኛ፥ እርስ በርሳችን በመዋደድ ወደ እግዚአብሔር እንጓዝ ማለታቸው ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ አሥራ አራተኛ፥ የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ መሪነት አገልግሎታቸውን ከዓለም ዙሪያ ከ200,000 በላይ ምዕመናን፣ የልዩ ልዩ አገራት መሪዎች እና የቤተ እምነት ተወካዮች በተገኙት እሑድ ግንቦት 10/2017 ዓ. ም. በመሩት መስዋዕተ ቅዳሴ በደስታ ጀምረዋል። ክቡራት እና ክቡራን የዝግጅታችን ተከታታዮች ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ 14ኛ በዕለቱ ያሰሙት ንግግር ትርጉም ሙሉ ይዘት እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን፥
“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ! የሮም ጳጳስ እና የቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ በመሆን ሐዋርያዊ አገልግሎቴን በይፋ በምጀምርበት በዛሬው በዓል ላይ ለተገኛችሁት የልዩ ልዩ አብያተ ክርስቲያናት፣ የቤተ ክርስቲያን ማኅበረሰብ እና የቤተ እምነት ተወካዮች በሙሉ በታላቅ ደስታ ሰላምታዬን አቀርባለሁ። ለብፁዕ ወቅዱስ በርተሎሜዎስ፣ ለብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ሦስተኛ እና ለብፁዕ አቡነ ማር አዋ ሦስተኛ ወንድማዊ ፍቅርን እየገለጽኩ፥ እያንዳንዳችሁንም ከልብ አመሰግናለሁ። የእናንተ እዚህ መገኘት እና መጸለይ ለእኔ ታላቅ መጽናኛ እና መበረታቻ ሆኖኛል።
የነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ መሪነት አንዱ ጠንካራ ጎን ዓለም አቀፋዊ ወንድማማችነት ነው። በዚህ ነጥብ ላይ መንፈስ ቅዱስ በቀደሙት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በተለይም ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ 23ኛ ጀምሮ የተጀመሩትን ጅምሮች በታላቅ እመርታ ወደ ፊት እንዲያራምዱ ገፋፍተዋቸዋል። ‘ሁላችንም ወንድማማቾች ነን!’ የሚለው የነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ መልዕክት የክርስቲያኖች የአንድነት ጉዞን እና የሃይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይቶችን አስተዋውቋል። ከሁሉም በላይ የእርስ በርስ ግንኙነቶችን በማጎልበት፣ በአብያተ ክርስቲያን መካከል ያለውን ትስስር ሳያጓድል፣ በሰዎች መካከል የሚደረገው ግንኝነት ሁልጊዜም ዋጋ ያለው እንዲሆን አድርጎታል። ለእርሱ የምንሰጠውን ምስክርነት ውጤታማ እንዲሆን እግዚአብሔር ይርዳን!
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳስነት ምርጫዬ የተካሄደው ቤተ ክርስቲያን የመጀመሪያው የኒቂያ ጉባኤ 1700ኛ ዓመት ለማክበር በምትዘጋጅበት ወቅት ነው። ያ ጉባኤ ሁሉም አብያተ ክርስቲያናት እና የቤተ ክርስቲያን ማኅበረሰቦች የሚጋሩትን የእምነት መግለጫ መሠረታዊ ደረጃን ይወክላል። ሁሉም ክርስቲያኖች ወደ ሙሉ ኅብረት ዳግም ለመመለስ በምንጓዝበት ወቅት፥ ይህ አንድነት በእምነት አንድ መሆን እንዳልሆነ እንገነዘባለን። እንደ ሮም ጳጳስ ቀዳሚ ተግባሬ በእግዚአብሔር አብ፣ በወልድ እና በመንፈስ ቅዱስ ላይ ተመሳሳይ እምነት ባላቸው ክርስቲያኖች መካከል ሙሉ እና ተጨባጭ ኅብረት እንደገና የሚመሠረትበትን መንገድ መፈለግ እንደሆነ እረዳለሁ።
እንደ እውነቱ ከሆነ የክርስቲያኖች አንድነት ዘወትር የምመኘው ጉዳይ ሲሆን፥ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳስነት አገልግሎቴ የመረጥኩት፥ ‘በእርሱ እኛ አንድ ነን’ የሚለው መሪ ቃል፥ ‘ምንም እንኳን ብዙዎች ብንሆንም በኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ነን’ የሚለውን የኢፖናው ቅዱስ አጎስጢኖስ ስብከት የሚያስታውሰን ነው።
አንድነታችን እውን የሚሆነው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ባለን ኅብረት ነው። ለእርሱ የበለጠ ታማኝ እና ታዛዥ በሆንን ቁጥር እርስ በርስ ይበልጥ እንተባበራለን። እንደ ክርስቲያኖች በኅብረት በመጸለይ እና በመሥራት ደረጃ በደረጃ የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ወደ ሆነው ግብ ለመድረስ ተጠርተናል።
በተጨማሪም ሲኖዶሳዊነት እና የክርስቲያኖች አንድነት በቅርበት የተሳሰሩ መሆናቸውን በመገንዘብ፥ ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶሳዊነትን ለማስተዋወቅ የጀመሩትን ጥረት አዲስ እና ተጨባጭ በሆኑ መንገዶች በማዘጋጀት በክርስቲያኖች መካከል ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ለማድረግ ያለኝን ፍላጎት ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ።
ከላይ እንደጠቀስኩት የሰው ልጆች የወንድማማችነት መንፈስ ሁሉንም በማሳተፍ የጋራ ጉዟችንን ሰፋ ባለ መልኩ ለመጓዝ የሚረዳ መሆን አለበት። ጊዜው ተወያይተን እርስ በርስ የምንገናኝባቸውን ድልድዮች የምንገነባበት ነው። ስለዚህ ለወንዶች እና ለሴቶች እንዲሁም ለፍጥረታት በሙሉ የፍቅር እና የሕይወት ባለቤት በሆነው በእግዚአብሔር ፈቃድ ፍለጋ ላይ የሚካፈሉ የሌሎች ሃይማኖታዊ ወጎች ተወካዮችን በማግኘቴ እጅግ ደስተኛ እና አመስጋኝ ነኝ።
ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሃይማኖቶች መካከል ውይይት ለማድረግ ያደረጉትን አስደናቂ ጥረት አይታችኋል። በቃሎቻቸው እና በድርጊቶቻቸው አዳዲስ የግንኙነቶች ዕይታዎችን ከፍተዋል። የውይይት ባህልን እንደ መንገድ፤ የጋራ ትብብርን እንደ ምግባር፣ የጋራ ዕውቀት እንደ ዘዴ እና መስፈርት በማድረግ፥ ለሰብዓዊ ወንድማማችነት፣ ለዓለም ሰላም እና አብሮ መኖር የሚያግዝ ሠነድ በአቡ ዳቢ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በየካቲት 4/2019 ዓ. ም. ይፋ አድርገዋል።
በሰብዓዊ ወንድማማችነት ላይ የተመሠረተ ግንኙነትን ለመፍጠር ያለመ ስብሰባዎችን በማካሄድ እና ተጨባጭ የሃሳብ ልውውጦችን በማበረታታት ለሚጫወተው አስፈላጊ ሚና፥ በጳጳሳዊ ምክር ቤት የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤትን አመሰግናለሁ።
ለአይሁድ እና ለሙስሊም ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ልዩ ሰላምታ ማቅረብ እፈልጋለሁ። የክርስትና እምነት ባለው የአይሁድ መሠረቶች ምክንያት ሁሉም ክርስቲያኖች ከአይሁድ እምነት ጋር ልዩ ግንኙነት አላቸው። ‘ኖስትራ አቴቴ’ ወይም ‘የእኛ ዘመን’ የተሰኘው የጉባኤው መግለጫ በቁ. 4 ላይ ለክርስቲያኖች እና ለአይሁዶች የጋራ ለሆነው የመንፈሳዊ አባትነት ታላቅነት አጽንኦት ይሰጣል። ይህም የጋራ እውቀትን እና ፍላጎትን ያበረታታል። በክርስቲያኖች እና በአይሁዶች መካከል ያለው ሥነ-መለኮታዊ ውይይት አስፈላጊ እና ልቤ ውስጥ የሚገኝ ነው። ግጭቶች እና አለመግባባቶች በሚታዩበት በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ይህን እጅግ ውድ የሆነው የውይይት ጥረት በጉጉት መቀጠል ያስፈልጋል።
በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን እና በሙስሊሞች መካከል ያለው ግንኙነት፥ ሕያው፣ መሐሪ እና ሁሉን ቻይ፣ የሰማይ እና የምድር ፈጣሪ የሆነው አንድ አምላክ ለእነዚህ ወንድሞች እና እህቶች የተናገረው አንድነት በውይይት እና በወንድማማችነት ጥረት እያደገ መጥቷል። በመከባበር እና በህሊና ነፃነት ላይ የተመሠረተ ይህ አካሄድ በማኅበረሰባችን መካከል ለሚገነባው የመገናኛ ድልድይ ጠንካራ መሠረት ይሆናል።
የሌሎች ቤተ እምነቶች ተወካዮች፣ በዚህ ሥነ-ሥርዓት ላይ የተሳተፋችሁት በሙሉ ለሰላም ላደረጋችሁት አስተዋፅኦ ምስጋናዬን አቀርባለሁ። በአመጽ እና በግጭት በቆሰለ ዓለም ውስጥ እያንዳንዱን ማኅበረሰብ በመወከል የራሳቸውን የጥበብ እና የርህራሄ ቁርጠኝነትን ለሰው ልጅ ጥቅም እና ለጋራ መኖሪያ ምድራችን ጥበቃ ያበረክታሉ። ከርዕዮተ ዓለም እና ከፖለቲካዊ ዓላማ ነፃ ሆነን የምንስማማ ከሆነ ጦርነት በመቃወም ሰላምን መፍጠር፣ ለጦር መሣሪያ ከመሽቀዳደም ይልቅ ትጥቅ ለማስፈታት የምንጥር ከሆነ፥ ሕዝቦችን እና ምድርን ለድህነት የሚዳርግ የኢኮኖሚ ሥርዓትን ከማራመድ ይልቅ የሁሉ አቀፍ የልማት ውጥኖችን በመዘርጋት ውጤታማ መሆን እንደምንችል እርግጠኛ ነኝ።
የወንድማማችነት ምስክርነታችን መልካም የሆኑ ወንዶች እና ሴቶች በልባቸው ውስጥ እንደሚመኙት፥ የበለጠ ሰላማዊ ዓለም ለመገንባት አስተዋፅዖ በማድረግ ውጤታማ ምልክቶችን ማሳየት እንደምንችል ተስፋ አደርጋለሁ።
ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ! ከእኔ ጋር በመሆናችሁ ሁላችሁንም በድጋሚ አመሰግናለሁ። በልባችን የእግዚአብሔርን በረከት እንለምነው። የእርሱ ወሰን የሌለው ቸርነቱ እና ጥበቡ ዘወትር ይርዳን። እግዚአብሔር የሰጠን ተስፋ በመላው ዓለም እንዲያድግ እንደ እርሱ ልጆች በወንድማማችነት እና በእህትማማችነት እንድንኖር። አመሰግናለሁ!"