ር. ሊ. ጳ. ሌዮ 14ኛ፥ “መቶኛ ዓመት” ጳጳሳዊ ፋውንዴሽን፥ ድሆችን እንዲያግዝ አሳሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
“ቼንቴዚመስ አኑስ” ወይም “የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ መቶኛ ዓመት” የተሰኘ ጳጳሳዊ ፋውንዴሽን፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከግንቦት 15-17/ 2025 ዓ. ም. ድረስ የሚቆየውን ጠቅላላ እና ዓለም አቀፍ ጉባኤን ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳስ ሌዮ 14ኛ ጋር ከተገናኘ በኋላ መጀመሩ ይታወሳል።
የጉባኤው መሪ ርዕሥ፥ “መለያየትን ማሸነፍ፣ ዓለም አቀፋዊ አስተዳደርን እንደገና ለመገንባት የሚያግዙ የሥነ-ምግባር መሠረቶች” የሚል ሲሆን፥ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ 14ኛ መልዕክትም ከቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ ጋር ግንኙነት ባለው የሥነ-ምግባር መሠረት ላይ ያተኮረ እንደ ነበር ተመልክቷል።
የውይይት ድልድዮችን መገንባት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ 14ኛ በተመረጡበት ምሽት፥ “ሁሉም ሰው አንድ ላይ ዘወትር በሰላም እንዲኖር የሚያስችል የውይይት እና የእርስ በርስ መገናኛ ድልድይ መገንባት ያስፈልጋል” በማለት በተናገሩት የተልዕኮ መልዕክት ላይ የፋውንዴሽኑ አባላት ለመተባበር ጥረት አድርገዋል። ቅዱስነታቸው በዚህ መልዕክታቸው፥ ይህም በድንገት የሚሆን ሳይሆን ነገር ግን የጸጋ እና የነፃነት ጥምረት የሚጠይቅ መሆኑን አስታውሰዋል።
የክፍፍል ጊዜ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ 14ኛ ከእርሳቸው በፊት የነበሩትን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 13ኛን በማስታወስ ባደረጉት ንግግር፥ “በዘመናቸው ባደረጉት ትግል ማኅበራዊ ውይይትን በማስተዋወቅ ለሰላም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማድረግ ጥረት አድርገዋል፥ ዘመናችንም ከዚህ የተለየ አይደለም” ሲሉ ተናግረዋል።
ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “በጦርነት፣ በአየር ንብረት ለውጥ ቀውስ፣ በእኩልነት ማጣት፣ በግዳጅ ስደት፣ በድህነት እና በመብት መጓደል የተሞላ የበርካታ ቀውሶች ዘመን” በማለት መግለጻቸውን ቅዱስ አባታችን አስታውሰዋል።
በእነዚህ ማኅበረሰባዊ፣ አካባቢያዊ እና ማኅበራዊ ተግዳሮቶች መካከል የቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ፥ ሳይንስን እና ህሊናን ወደ ውይይት የሚያመጡ መንገዶችን ያሳያል” ብለው፥ የፋውንዴሽኑ አባላት ከችግሮቹ የበለጠ አስፈላጊው ነገር፥ ሰዎች ለእነርሱ የሚሰጡት ሥነ ምግባራዊ መርሆች፣ ትክክለኛ የግምገማ መመዘኛዎች እና ለእግዚአብሔር ጸጋ ግልጽነት የሚሰጡት ምላሽ እንደ ሆነ አስገንዝበዋል።
ማኅበራዊ አስተምህሮ በዛሬው ዓለም ውስጥ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ አሥራ አራተኛ በመልዕክታቸው፥ “በሂሳዊ አስተሳሰብ ውስጥ የማስተማር ተልዕኮን እንደገና ማግኘት፣ መግለጽ እና ማጎልበት” አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው፥ ምክንያታዊ ያልሆኑ ድምፆች፣ የውሸት ዜናዎች እና ሕገ ቀኖናዊ የይገባኛል ጥያቄዎችን እንዲሰራጩ ከመፍቀድ መጠንቀቅ እንደሚገባ አስጠንቅቀዋል።
ይህን ለማድረግ፥ የፋውንዴሽኑ አባላት ከድሆች ጋር የሚገናኙ እና የሚያዳምጧቸው በመሆኑ ማጥናት እና በጥንቃቄ ማሰላሰል አስፈላጊ እንደሆነ አሳስበዋል።
“ድሆች የቤተ ክርስቲያን እና የሰው ልጅ ውድ ሃብት ናቸው” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ 14ኛ፥ ምክንያቱም አመለካከቶችን የሚገልጹ፥ ብዙውን ጊዜ የሚገለሉ ቢሆንም ነገር ግን ዓለምን በእግዚአብሔር ዓይን ለማየት ወሳኝ ናቸው” ሲሉ ገልጸዋቸዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ አሥራ አራተኛ፥ “ለድሆች ድምጽ መስጠት ይገባል” ሲሉ አፅንዖት ሰጥተው፥ “የቼንቴዚሙስ አኑስ” ፋውንዴሽን አባላት በንቃት በመሳተፍ፥ በዚህ ታላቅ ማኅበራዊ ቀውስ ወቅት ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር በመሆን ሌሎችን በትኩረት ማዳመጥ እና ከሁሉም ጋር ግልጽ ውይይት እንዲያደርጉ አሳስበዋል።