ር.ሊ.ጳ ፍራንችስኮስ ተሳስተን ጠፍተን እንደ ሆነ እንመለስ፣ አፍቃሪ አባታችን ይጠብቃናል አሉ!
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዘወትር ረቡዕ እለት ለምዕመናን በተለያዩ አርእስቶች ላይ ተንተርሰው የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደምያደርጉ ይታወቃል። ቅዱስነታቸው በደረሰባቸው የጤና እክል ምክንያት የሕክምና አገልግሎት ከተሰጣቸው በኋላ በአሁኑ ወቅት በቫቲካን በሚገኘው የቅድስት ማርታ ቤት ውስጥ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ከሕመማቸው እያገገሙ እንደሚገኙ ይታወቃል። በዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው ቀደም ሲል ከመታመማቸው በፊት ያዘጋጁትን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ የቫቲካን የፕሬስ ጽ/ቤት በሚያዝያ 08/2017 ዓ.ም ይፋ አድርጓል። በዚህ መሰረት በወቅቱ ጽ/ቤቱ ያፋ ባደርገው የቅዱስነታቸው የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ አሁን የምንገኝበትን የኢዩቤሊዩ አመት ምክንያት በማድረግ ከዚህ ቀደም "ኢየሱስ ክርስቶስ ተስፋችን ነው፣ የኢየሱስ ሕይወት እና ያደረጋቸው ግንኙነቶች" በሚል ዐብይ አርእስት ጀምረውት ከነበረው አስተምህሮ በመቀጠል “ጠፍቶ ነበር አሁን ግን ተገኘ" (ሉቃስ 15፡32) በሚል ንዑስ አርእስት ምሕረት ስላደርገው ጠፍቶ የተገኘው ልጅ አባት ሁኔታ በሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ ተመርኩዘው ይፋ ባደረጉት የክፍል አምስት አስተምህሮ ተሳስተን ጠፍተን እንደ ሆነ እንመለስ፣ አፍቃሪ አባታችን ይጠብቃናል ማለታቸው ተገልጿል።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን
በእለቱ የተነበበው ምንባብ
እርሱ ግን እንዲህ አለው፦ ‘ልጄ ሆይ! አንተ ሁልጊዜ ከእኔ ጋር ነህ፤ ለእኔም የሆነ ሁሉ የአንተ ነው፤ 32ዳሩ ግን ይህ ወንድምህ ሞቶ ነበረ፤ ሕያው ስለ ሆነ ጠፍቶም ነበር፤ ስለ ተገኘ ደስ እንዲለን ፍሥሐም እንድናደርግ ይገባናል’” (ሉቃስ 15፡31-32)።
ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች የቫቲካን የፕሬስ ጽ/ቤት በወቅቱ ይፋ ያደርገውን የቅዱስነታቸውን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው አሰናድተነዋል፣ ተከታተሉን።
የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ
ኢየሱስ በተወሰኑ የወንጌል ምሳሌዎች ውስጥ ከተጠቀሱ ሰዎች ጋር ስላደረገው ግንኙነት ላይ ካስተነተንን በኋላ፣ ከዚህ የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ጀምሮ ደግሞ በአንዳንድ ምሳሌዎች ላይ ቆም ማለት እፈልጋለሁ። እንደምናውቀው ከዕለት ተዕለት እውነታ ምስሎችን እና ሁኔታዎችን የሚስቡ ታሪኮች ናቸው። ለዛም ነው ሕይወታችንን የሚነኩት። ይቀሰቅሱናል። እናም አንድ ቦታ እንድንይዝ ይጠይቁናል፡ በዚህ ታሪክ ውስጥ የት ነው ያለሁት? ብለን እንድንጠይቅ ያነሳሱናል።
በጣም ዝነኛ ከሆነው ምሳሌ እንጀምር፣ ምናልባትም ሁላችንም ከልጅነታችን ጀምሮ የምናስታውሰው፡ የአባትና የሁለቱ ልጆች ምሳሌ (ሉቃስ 15፡1-3፣ 11-32)። በዚህ የወንጌል ክፍል ውስጥ የኢየሱስን ልብ ማለትም የእግዚአብሔርን ምሕረት እናገኛለን።
ወንጌላዊው ሉቃስ ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ለፈሪሳውያንና ለጻፎች የተናገረው ከኃጢአተኞች ጋር መብላቱን ባዩ ጊዜ በእርሱ ላይ ስላዘኑ መሆኑን ተናግሯል። ለዚህም ነው ለጠፉት ሰዎች የተነገረ ምሳሌ ነው ይሚባለው፣ ነገር ግን ሳያውቁ በሌሎችም ላይ ስለሚፈርዱ ሰዎች የተነገረ ምሳሌ ነው።
ወንጌሉ የተስፋ መልእክት ሊሰጠን ነው የፈለገው፣ ምክንያቱም በምንጠፋበት ጊዜ ሁሉ እግዚአብሔር ሁል ጊዜ እኛን ሊፈልገን እንደሚመጣ ስለሚነግረን ነው! ምናልባት እንደ በግ ተቅበዝብዘን ጠፋን፣ ከግጦሽ ስፍራ ተቅበዝብዞ ከመንገድ ስንጠፋ ወይም በድካም ወደ ኋላ ስንቀር እርሱ ይፈልገናል (ሉቃ. 15፡4-7)። ወይም እንደ ሳንቲም ጠፋን፣ ምናልባት መሬት ላይ ወድቆ ሊገኝ የማይችል፣ ወይም አንድ ሰው የሆነ ቦታ ያስቀመጠው እና የት እንደሆነ የማያስታውሰው ዓይነት ዕቃ ልንሆን እንችል ይሆናል። ወይም ደግሞ እንደ እኚህ አባት ሁለት ልጆች ጠፍተናል፡ ታናሹ በጣም የሚጠይቅ ሆኖ በሚሰማው ግንኙነት ስለሰለቸ ነው። ነገር ግን ትልቁም እንዲሁ ጠፍቷል፣ ምክንያቱም በልቡ ውስጥ ኩራት እና ቂም ካለ በቤት ውስጥ መቆየት በቂ አይደለም።
ፍቅር ሁል ጊዜ ቁርጠኝነትን የሚጠይቅ ነው ፣ ወደ ሌላው ለመሄድ ሁል ጊዜ ማጣት ያለብን አንድ ነገር አለ። ነገር ግን በምሳሌው ውስጥ ያለው ታናሽ ልጅ በአንዳንድ የልጅነት እና የጉርምስና ደረጃዎች ውስጥ እንደሚታየው ስለ ራሱ ብቻ ያስባል። እንደ እውነቱ ከሆነ፣ ራስ ወዳድ ስለሆኑ ግንኙነታቸውን መቀጠል የማይችሉ ብዙ ጎልማሶችን በዙሪያችን እናያለን። እራሳቸውን አገኛለሁ ብለው እራሳቸውን ያታልላሉ እና ይልቁንም እራሳቸውን ያጣሉ ፣ ምክንያቱም ለአንድ ሰው ስንኖር ብቻ ነው በእውነት የምንኖረው።
ይህ ታናሽ ልጅ ልክ እንደ ሁላችንም የፍቅር ረሃብ አለው፣ መወደድ ይፈልጋል። ፍቅር ግን ውድ ስጦታ ነው፣ በጥንቃቄ መያዝ አለበት። ይልቁንም እርሱ ያባክናል፣ ይንቀዋል፣ ራሱን አያከብርም። ይህን የሚገነዘበው በረሃብ ጊዜ ማንም የማይጨነቅለት ጊዜ ሲመጣ ነው። አደጋው በእነዚያ ጊዜያት ፍቅርን እንለምናለን እና እራሳችንን ከአጋጣሚ ካገኘነው የመጀመሪያ ጌታ ጋር ማያያዝ ነው የምንፈልገው።
ለጥፋተኝነት ማስተሰረያ ወይም እውነተኛ ፍቅር ሊኖር እንደማይችል እንደ አገልጋይ ብቻ ግንኙነት ውስጥ ልንሆን የምንችለው ወደሚለው የተዛባ እምነት በውስጣችን የፈጠሩት እነዚህ ገጠመኞች ናቸው። በእርግጥ፣ ታናሹ ልጅ፣ ከሰው ሁሉ በታች ሲሆን በመሬት ላይ ተበታትነው የሚገኙ ጥቂት የፍቅር ፍርፋሪዎችን ለመውሰድ ወደ አባቱ ቤት ለመመለስ ያስባል።
ከዚህ የውሸት የፍቅር አመለካከት ነፃ የሚያወጡን በእውነት የሚወዱን ብቻ ናቸው። ከእግዚአብሔር ጋር ባለን ግንኙነት፣ በትክክል ይህ ልምድ አለን። ታላቁ ሰዓሊ ሬምብራንት በታዋቂው ሥዕል ላይ የአባካኙን ልጅ መመለስ በሚያምር ሁኔታ አሳይቷል። በተለይ የስዕሉ ሁለት ዝርዝሮች እኔን ነክተውኛል፣ የወጣቱ ራስ ተላጭቷል፣ ልክ እንደ ንስሃ፣ ነገር ግን ጭንቅላቱ የልጅ ራስ ይመስላል፣ ምክንያቱም ይህ ልጅ እንደገና በመወለዱ ነው። ከእዚያም በመቀጠል የገረመኝ ነገር የአባቱ እጆች ናቸው፣ አንድ ወንድ እና አንድ ሌላ ሴት፣ በይቅርታ እቅፍ ውስጥ ያለውን ጥንካሬ እና ርህራሄ ለመግለጽ ታስቦ የተደርገ ነው።
ነገር ግን ምሳሌው የተነገረለትን የሚወክለው የበኩር ልጅ ነው፡ እርሱ ሁልጊዜ ከአባቱ ጋር በቤት ውስጥ የሚኖር በልቡ ግን የራቀ ልጅ ነው። ይህ ልጅም መልቀቅ ፈልጎ ሊሆን ይችላል፣ ነገር ግን በፍርሃት ወይም በግዴታ በዚያ ግንኙነት ውስጥ እዚያው ቆየ። ሳይወዱ በግድ ሲላመዱ ግን ቁጣን በውስጣችሁ መያዝ እንድንጀምር ያደርገናል እናም ይዋል ይደር እንጂ ይህ ቁጣ ይፈነዳል። አያዎ ወይም ተጻራሪ (ፓራዶክስ) የሚመስል ሐሳብ ነው ፣ እሱ የአባቱን ደስታ ስለማይጋራ ፣ በመጨረሻው ላይ የመተውን አደጋ የሚጋፈጠው የበኩር ልጅ ነው።
አባትየውም ወደ እሱ ይሄዳል። አይነቅፈውም ወይም ስለሥራው ብቃት ጥርጣሬ የለውም። የሚፈልገው ፍቅሩ እንዲሰማው ብቻ ነው። እንዲገባና በሩን ክፍት እንዲተው ጋበዘው። ያ በር ለእኛም ክፍት ነው። በእርግጥ ይህ የተስፋችን ምክንያት ነው፣ እኛ ተስፋ ማድረግ እንችላለን፣ ምክንያቱም አባታችን ተዘግጅቶ ስለሚጠብቀን ነው፥ እርሱ ከእሩቅ ይመለከተናል፣ እናም እርሱ ሁሌም በሩን ለእኛ ክፍት ያደርጋል።
ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ እራሳችንን እንጠይቅ፣ ታዲያ በዚህ አስደናቂ ታሪክ ውስጥ የት እንዳለን እንጠይቅ። እኛም ወደ ቤት የምንመለስበትን መንገድ ልናገኝ የምንችለውን ጸጋ እግዚአብሔርን አብን እንለምነው።