ፈልግ

ምዕመናን በጄሜሊ ሆስፒታል ደጅ በቆመው የቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ሐውልት ፊት ጸሎታቸውን ሲያቀርቡ። ምዕመናን በጄሜሊ ሆስፒታል ደጅ በቆመው የቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ሐውልት ፊት ጸሎታቸውን ሲያቀርቡ። 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ እሁድ በጄሜሊ ሆስፒታል ደጅ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን ሰላምታቸውን ያቀርባሉ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሑድ መጋቢት 14/2017 ዓ. ም. ከቀኑ ስድስት ሰዓት በኋላ ሕክምናቸውን ሲከታተሉ በቆዩበት ጄሚሊ ሆስፒታል ዙሪያ ለሚሰበቡት ምዕመናን እና እንግዶች ሰላምታ እንደሚያቀርቡ የቅድስት መንበር መግለጫ አስታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የቅድስት መንበር መግለጫ ዛሬ ቅዳሜ ጠዋት እንደገለጸው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሕክምናቸውን በመከታተል ላይ ከሚገኙበት ጄሜሊ ሆስፒታል ዙሪያ ለሚሰበሰቡት ምዕመናን ሰላምታ ለመስጠት እና ነገ እሑድ መጋቢት 14/2017 ዓ. ም. ከቀኑ ስድስት ሰዓት በኋላ ቡራኬያቸውን ለመስጠት ማቀዳቸውን አስታውቋል። ቅዱስነታቸው በየሳምንቱ እሑድ ከመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት በኋላ ሲያቀርቡት የነበረው እና ላለፉት ጥቂት ሳምንታት ተቋርጦ የቆየው ሳምንታዊ የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖን ለምዕመናኑ በጽሑፍ እንደሚያጋሯቸው መግለጫው አክሎ አስታውቋል።


ዶክተሮች ቅዱስነታቸው ከሆስፒታል የሚወጡበትን ጊዜ በተመለከተ እስካሁን ምንም ዓይነት ፍንጭ ባይሰጡም ነገ እሁድ ለምዕመናን የሚያቀርቡት ሰላምታ ቅዱስነታቸው የካቲት 7/2017 ዓ. ም. ሆስፒታል ከገቡ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሕዝብ የሚታዩበት እና በቅርቡ የጤናቸው ሁኔታ መሻሻሉ ከተነገረ በኋላ እንደሆነ ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ላለፉት አምስት ሳምንታት ሆስፒታል ውስጥ ሆነው ዕለታዊ ሐዋርያዊ ሥራቸውን በመቀጠል፣ ለነጋዲያን መልዕክቶችን በመላክ፣ መስዋዕተ ቅዳሴን በማሳረግ እና የካቲት 27/2017 ዓ. ም. ባስተላለፉት የድምጽ መልዕክትም ሁሉንም ሰው ላሳየው የፍቅር እና የአብሮነት ምስክርነት ምስጋናቸውን ማቅረባቸው ይታወሳል።

የቫቲካን መገናኛም በበኩሉ የቅዱስነታቸውን ሰላምታ እና ቡራኬበዩቲዩብ ገጹ አማካይነት በቀጥታ ስርጭት ለመላው ዓለም እንደሚያስተላልፍ አስታውቋል።

 

22 Mar 2025, 15:14