ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ከጳጳስዊ የመገናኛ ኮሚሽን ፕሬዚዳንቶች እና ብሔራዊ የመገናኛ ጽ/ቤቶች ዳይሬክተሮች ጋር በቫቲካን ተገናኝተዋል ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ከጳጳስዊ የመገናኛ ኮሚሽን ፕሬዚዳንቶች እና ብሔራዊ የመገናኛ ጽ/ቤቶች ዳይሬክተሮች ጋር በቫቲካን ተገናኝተዋል  (VATICAN MEDIA Divisione Foto)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የካቶሊክ መገናኛ ተቋማት ተስፋን ለማምጣት በኅብረት እንዲሰሩ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ከጳጳስዊ የመገናኛ ኮሚሽን ፕሬዚዳንቶች እና ብሔራዊ የመገናኛ ጽ/ቤቶች ዳይሬክተሮች ጋር በቫቲካን ተገናኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል። ቅዱስነታቸው ለአባላቱ ባስተላለፉት መልዕክት፥ ተስፋን እና መግባባትን በኅበረት ለመገንባ የሚያስችል ልዩ የግንኙነት ሞዴል እንዲያዘጋጁ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ካቶሊካዊ የመገናኛ መሪዎች በቤተ ክርስቲያንም ሆነ በሰፊው ዓለም ተስፋን እና አንድነትን ለመዝራት የሚያስችል ልዩ የመገናኛ ሞዴል በኅብረት እንዲያዘጋጁ አሳስበዋል። “ስለ ወደፊት ጊዜ መጻፍ የኛ ፈንታ ነው” በማለት፥ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ኢዮቤልዩን ለማክበር በቫቲካን ለተሰበሰቡት የካቶሊክ መገናኛ ተቋማት ዳይሬክተሮችን ሰኞ ጥር 19/2017 ዓ. ም. ተናግረዋል።

የተስፋ መልዕክትን እንዴት ማስተላለፍ እንችላለን?
“ጥረታቸው በእውነት ተስፋን የሚያነሳሳ ነው ወይ?” ብለው በመጠየቅ ሃሳባቸውን የጀመሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በቦታው የተገኙት በሙሉ ማኅበረሰቦችን እያዳከመ ያለውን የመከፋፈል በሽታን እንዲመክቱ አሳስበዋል።

“ተስፋ ፈጽሞ አያሳዝንም፤ ነገር ግን ይህን ተስፋ ለሌሎች ማስተላለፍ እንችላለን ወይ?” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ስለ ቤተ ክርስቲያን መናገርር ማለት የተቀመጡትን ሕጎች መከተል ብቻ ሳይሆን ነገር ግን የእግዚአብሔር መንግሥት እንደቀረበ ማሳየት እና በጎነት ያለበትን ተስፋ ማወቅና እና ማስፋፋት እንደ ሆነ አሳስበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ይህም የክፉ መንፈስ መኖርን ተገንዝቦ የመልካምነትን እና የጽናት ታሪኮችን ለሌሎች ለመናገር የተጠራ ክርስቲያን ሁሉ ጥሪ እንደሆነ እና ብዙውን ጊዜ ጋዜጠኝነትን ሊያጋጥም የሚችል አሉታዊ ትኩረትን መቃወም እንደሆነ አስረድተዋል። “ክፋት መኖሩ እርግጥ ነው! መደበቅም የለበትም፤ ነገር ግን ጥያቄን በማቅረብ መልስ ልናገኝለት የሚያነያነሳሳን ሊሆን ይገባል” ብለዋል።

ለዛሬው የባቤል ግንብ አማራጭ መንገድ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “ሁሉም ሰው፥ አዛውንት እና ወጣት፣ ሴትን እና ወንድ የሚተባበርበት፥ ቃላትን፣ ኪነጥበብን፣ ሙዚቃን፣ ስዕልን እና ምስሎችን በመጠቀም እያንዳንዱን ቋንቋ ያገናዘበ የኅብረት ሥራ መሥራት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።


ስለዚህም፥ የካቶሊክ መገናኛ ባለሞያዎች በወንጌል አነሳሽነት ትብብራቸውን እንዲያሳድጉ እና ሁሉም ሰው በሚናገርበት ነገር ግን አንዱ ሌላውን መረዳት በማይችልበት ዓለማችን ውስጥ ተጨባጭ አማራጭ የሚያቀርብ ልዩ የመገናኛ ሞዴል ለመገንባት እንዲተባበሩ አሳስበዋል።

“የእርስ በርስ ግንኙነት ዘወትር ፍጹም ሊሆን ይገባል” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ መግባባት ከቻልን የመገናኛ ቋንቋዎችን እና ድልድዮችን መገንባት እንችላለን” ብለው፥ የካቶሊክ መገናኛ ባለሞያዎች የግንኙነት ሞዴል በመሆን በተከፋፈለው ዓለማችን ውስጥ ስምምነትን በመፍጠር ተጨባጭ አማራጮችን የሚያቀርብ መሆን አለበት ብለዋል።

በኅብረት መሥራት
ቅዱስነታቸው የሁለት ቁልፍ ቃላት እነርሱም የ “ኅብረት እና አውታረ መረብን” የማበጀት አስፈላጊነት ሲገልጹ፥ ለክርስቲያኖች የእርስ በርስ ግንኙነት ማለት ተጨባጭ ሐረጎችን፣ መፈክሮችን ወይም መግለጫዎችን መጻፍ ብቻ ሳይሆን ነገር ግን የፍቅር ተግባር መፈጸም መሆኑን አስታውሰው፥ ከፋፋይ የሆኑ የመግባቢያ መንገዶችን ባለመቀበል ማኅበረሰቦችን በየቀኑ የሚያንጹ እና ተስፋን የሚሰጡ የመልካምነት አውታረ መረቦችን ማበጀት እንደሚቻል አስረድተዋል።

የመገናኛ አውታረ መረብ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “አውታረ መረብን” በማስመልከት እንደተናገሩት፥ ይህ ቃል የዓሣ አጥማጆች መረቦችን እና ኢየሱስ ክርስቶስ ለጴጥሮስ ዓሣ አጥማጅ እንዲሆን ያቀረበውን ግብዣ እንደሚያስታውስ ገልጸው፥ “ስለዚህ እኛም ችሎታዎችንን፣ ዕውቀታችንን እና ሃብቶቻችንን በአውታረ መረብ ውስጥ እንድናስገባ በማነሳሳት በቂ መረጃ መስጠት የሚችል፣ ተስፋን ከመቁረጥ እና ከተሳሳተ መረጃ ለማምለጥ የሚያስችል የመገናኛ አውታረ መረብ ሊኖረን ይገባል” ብለዋል።


“አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ” ወይም ሰው ሠራሽ አስተውሎትን ጨምሮ ዘመናዊ የዲጂታል መሣሪያዎች እምቅ አቅም እንዳላቸው በማስገንዘብ፥ ከቴክኖሎጂ ጣኦት በመራቅ ይልቁንም እነዚህ መሣሪያዎች የሰውን የተፈጥሮ እውቀት፣ ጥበብ እና ማስተዋልን ለማዳበር እንደሚግዙ በመግለጽ፥ በመሆኑም ትርጉም ያለውን ግንኙነት እና አውታረ መረቦችን ለመፍጠር ቁርጠኝነት ሊኖር እንደሚገባ አሳስበዋል።

እግዚአብሔር ለሌሎችም እንዲገለጥ ማድረግ አለብን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በተጨማሪም፥ “የካቶሊክ መገናኛ ባለሞያዎች የመነጋገር ችሎታ ምስጢር ራስን ከማስተዋወቅ ወይም ከግለሰብ ስኬቶች ይልቅ በእግዚአብሔር ላይ በጋራ መተማመን ላይ የተመሠረተ መሆኑን አስታውሰው፥ ራሳችንን በማስተዋወቅ እና በራሳችን ተነሳሽነት በምናገኘው ጨዋነት በጎደለው ስሜት ከመታለል ይልቅ የተስፋ መልዕክትን መገንባት የምንችልበትን መንገድ ማሰብ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ኢየሱስ ከስምዖን ጴጥሮስና ከዓሣ አጥማጆች ጋር ያደረገውን ተአምር በማስታወስ፥ የካቶሊክ መገናኛ ባለሞያዎች በተልዕኳቸው ውስጥ በደስታ እና በተስፋ እንዲጸኑ ብርታትትን ተመኝተውላቸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመጨረሻም፥ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን እውነተኛ የእርስ በርስ ግንኙነት እና ምስክርነት እንዲሁም እንግዳ ተቀባይነትን ያማከለ አካሄድ እንደሚያስፈልጋት ገልጸው ከሰፊው ዓለም ጋር በንቃት በመገናኘት እግዚአብሔር ለሌሎች እንዲገለጥ ማድረግ እንደሚገባት በማሳሰብ፥ ካቶሊካዊ የእርስ በርስ ግንኝነት ለካቶሊኮች ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም ጭምር መሆኑን በማስገንዘብ መልዕክታቸውን ደምድመዋል።

 

28 Jan 2025, 16:17