ቫቲካን የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የሐምሌ እና የነሐሴ ወራት ሐዋርያዊ መርሃ ግብሮች ይፋ አደረገች
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የቅድስት መንበር መግለጫ ክፍሉ በሚቀጥሉ ሁለት ወራት ቅዱስነታቸው የሚገኙባቸውን የደማቅ መንፈሳዊ በዓላት መርሃ ግብርን ያገኘው ከጳጳሳዊ የአምልኮ ሥነ-ሥርዓት ዝግጅት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት እንደሆነ ታውቋል። ሐምሌ ወር በተለምዶ የቅዱስነታቸው የዕረፍት ወር እንደሆነ ይታወቃል። ይሁንና ሰኔ 27/2015 ዓ. ም. ይፋ የተደረገው መርሃ ግብር እናዳመለከተው፥ በቫቲካን ውስጥ የሚፈጸመው ብቸኛው ኦፊሴላዊ የአምልኮ ሥነ-ሥርዓት እሁድ ሐምሌ 16/2015 ዓ. ም. ለሦስተኛ ጊዜ በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት የሚከበረው ዓለም አቀፍ የአያቶች እና የአረጋውያን ቀን ሲሆን፥ በዚሁ ዕለት ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ ከረፋዱ በአራት ሰዓት የሚጀምረውን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት እንደሚመሩት ታውቋል።
ቤተ ክርስቲያን ዓመታዊውን ዓለም አቀፍ የአያቶች እና የአረጋውያን ቀን ሐምሌ ወር ከገባ በአራተኛው ሳምንት የምታከብረው ሲሆን፣ ይህም የኢየሱስ ክርስቶስ አያቶች፣ ቅዱስ ኢያቄም እና ቅድስት ሐና ዓመታው በዓል በሚከበርበት ዕለት አካባቢ እንደሆነ ይታወቃል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዕለቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተከብሮ እንዲውል የወሰኑት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2021 ዓ. ም. ሲሆን ዓላማውም፥ በትውልዶች መካከል ትስስርን ለመፍጠር ዓይነተኛ መንገድ የሆኑትን፣ የሕይወት እና የእምነት ልምዳቸውን ለወጣቱ ትውልድ የሚያስተላልፉትን፥ ነገር ግን ብዙውን ጊዜ አስታዋሽ የሌላቸውን አያቶች እና አረጋውያን ለማስታወስ እንደሆነ ይታወቃል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለዘንድሮው ዓለም አቀፍ የአያቶች እና የአረጋውያን ቀን የመረጡት መሪ ጥቅስ፥ በሉቃ. 1፡50 ላይ የተጻፈው፥ “ምሕረቱም ከትውልድ እስከ ትውልድ እርሱን በሚፈሩት ላይ ይኖራል” የሚል እንደሆነ ታውቋል። ከዓለም አቀፍ የአያቶች እና የአረጋውያን ቀን በኋላ ብዙም ሳይቆይ ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል በፖርቱጋል መዲና ሊዝበን ውስጥ ከሐምሌ 25-30/2015 ዓ. ም. ድረስ እንደሚከበር እና ይህም በሁለቱ ዓለም አቀፍ በዓላት መካከል ትስስር መኖሩን እንደሚያመላክት ታውቋል። ከእነዚህ ሁለቱ በዓላት በኋላ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ጉብኝት እንደሚያካሂዱ ከጳጳሳዊ የአምልኮ ሥነ-ሥርዓት ዝግጅት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት የወጣው መርሃ ግብር አመልክቷል።
በፖርቱጋል ከወጣቶች ጋር የሚቀርብ መስዋዕተ ቅዳሴ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሐምሌ ወር መጨረሻ አካባቢ ማለትም ከሐምሌ 25-30/2015 ዓ. ም. ድረስ ወደ ፖርቱጋል በመጓዝ በመዲናይቱ ሊዝበን በሚከበረው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል ላይ እንደሚገኙ መርሃ ግብሩ አመልክቷል። ቅዱስነታቸው ወደ ፖርቱጋል መዲና ሊዝበን በሚያደርጉት ጉዞ ወቅት ከዓለም ዳርቻ በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ምዕመናን መንፈሳዊ ጉዞን የሚያደርጉባት የፋጢማ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ መቅደስን እንደሚጎበኙ ታውቋል።
ቅዱስነታቸው ከዚህ በፊት ኮቫ ዳ ኢሪያ በተባለ የፖርቱጋል መንደር እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለሦስት ሕጻንት የተገለጸችበትን መቶኛ ዓመት ለማክበር እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከግንቦት 12-13/2017 ዓ. ም. ድረስ ሐዋርያዊ መጎብኝ ማድረጋቸው ይታወሳል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በወቅቱ ባደረጉት ሐዋርያዊ ንግደታቸው፥ ዓለምን በማስጨነቅ ላይ የሚገኙ ጦርነቶች እንዲያበቁ ጸሎት አቅርበው መመለሳቸውም ይታወሳል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በፖርቱጋል መዲና ሊዝበን በሚከበረው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል ላይ ሲገኙ ይህ ለአራተኛ ጊዜ ሲሆነ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2013 ዓ. ም. በብራዚል ሪዮ ዴ ጄኔሮ ከተማ በተከበረው፣ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2016 ዓ. ም. በፖላንድ መዲና ክራኮቪያ እና እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2019 ዓ. ም. በመካከለኛዋ የላቲን አሜሪካ አገር ፓናማ በተከበረው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል ላይ መገኘታቸው ይታወሳል። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2022 ዓ. ም. በፖርቱጋል መዲና ሊዝበን ሊከበር ታቅዶ የነበረ 37ኛው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ለሌላ ጊዜ መተላለፉ ይታወሳል።
በሞንጎሊያ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት
ጳጳሳዊ የአምልኮ ሥነ-ሥርዓት ዝግጅት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ይፋ ያወጣው መርሃ ግብር እንዳመለከተው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከነሐሴ 25-29/2015 ዓ. ም. ድረስ በሞንግሊያ ሐዋርያዊ ጉብኝት እንደሚያደርጉ ተመልክቷል። ሞንጎሊያ ከ 1,500 የማይበልጡ ካቶሊካዊ ምዕመናን ያሉባት አገር ስትሆን፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይህችን የምሥራቅ እስያ አገርን ሲጎበኙ የመጀመሪያው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ይሆናሉ ተብሏል። ቅዱስነታቸው በሞንጎሊያ የሚያደርጉት የሐዋርያዊ ጉብኝት መርሐ ግብርን እና ሌሎች ተጨማሪ ማብራሪያዎችን በሚቀጥሉት ሳምንታት ውስጥ ይፋ እንደሚያደርግ የቅድስት መንበር መግለጫ ክፍል አስታውቋል። በቅርቡ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በነሐሴ 2022 ዓ. ም. ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አዳዲስ ካርዲናሎችን በሾሙበት ወቅት በሞንጎሊያ ዋና ከተማ ኡላንባታር ሐዋርያዊ አስተዳዳሪ የነበሩትን አቡነ ጆርጆ ማሬንጎን የአገሪቱ የመጀመሪያ ካርዲናል አድርገው መሾማቸው ይታወሳል።