ፈልግ

አስደሳችና አጽናኝ የስብከተ ወንጌል ደስታ አስደሳችና አጽናኝ የስብከተ ወንጌል ደስታ  (ANSA)

አስደሳችና አጽናኝ የስብከተ ወንጌል ደስታ

ደግነት ሁልጊዜ የመስፋፋት ዝንባሌ አለው፡፡ ማንኛውም የእውነትና የደግነት ተሞክሮ በባህርዩ በውስጣችን ማደግ ይፈልጋል፤ መሠረታዊ ነጻነት ያገኘ ሰው ሁሉ ለሌሎች ሰዎች ፍላጎት ይበልጥ ተጨናቂ ይሆናል፡፡ ደግነት እየሰፋ ሲሄድ ጥልቀት ይኖረዋል፣ ይዳብራል፡፡ የተከበረና የተሳካ ሕይወት ለመምራት ከፈለግን ለሌሎች መድረስና የእነርሱን በጎ መሻት አለብን፡፡ በዚህ ረገድ፣ ቅዱስ ጳውሎስ የተናገራቸው ብዙ ነገሮች አሉ፤ ለምሳሌ ‹‹የክርስቶስ ፍቅር ግድ ይለናል›› (2 ቆሮ.5፡14)፤ ‹‹ወንጌልን ባልሰብክ ውዮልኝ›› (1ቆሮ.9፡16) ማለቱ ሊያስገርመን አይገባም፡፡

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ወንጌል ከፍ ያለ፣ ኃይሉ ያልቀነሰ ሕይወት እንድንኖር ዕድል ይሰጠናል፡፡ ‹‹ሕይወት የሚያድገው ለሌሎች ሲሰጡት ነው፣ በብቸኝነትና በምቾት ጊዜ ግን ይቀንሳል፡፡ በእውነቱ፣ ኑሮአቸው እጅግ የሚደሰቱ ሰዎች የራሳቸውን ደኅንነት ወደ ጎን ትተው ሕይወትን ለሌሎች በማስተላለፍ ተልእኮ የሚተጉ ናቸው›› (አምስተኛ የላቲን አሜሪካና ካሪቢያን አገሮች ጳጳሳት ጠቅላላ ጉባኤ፣አፓሬሲዳ ሰነድ፣እ.አ.አ. ሰኔ 29 ቀን 2007፣360) ፡፡ ቤተ ክርስቲያን ክርስቲያኖችን ለስብከተ ወንጌል ሥራ ስትጠራ፣ ወደ እውነተኛ ግለሰብአዊ የስኬት ምንጭ ማመልከትዋ ነው፡፡ ምክንያቱም ‹‹እዚህ ላይ ጥልቅ የሆነ የእውነታን ሕግ እናገኛለን፡፡ ይኸውም ሕይወት የሚገኘውና የሚዳብረው ለሌሎች ሕይወት ለመስጠት  በተሰጠው ልክ ነውና፡፡ ተልእኮ ማለት በእርግጥ ይህ ነው››፡፡ ስለሆነም የወንጌል ሰባኪ ገና ለገና ከቀብር የተመለሰ ሰው ሊመስል አይገባም፡፡ መንፈሳዊ ግለታችንን፣ ‹‹መዝራት ያለብን በእንባ ቢሆንም እንኳ ያን አስደሳችና አጽናኝ የወንጌል ደስታን›› መልሰን እናግኝ፣ እናዳብረውም፡፡ ‹‹አንዳንዴ በጭንቀት፣ አንዳንዴ በተስፋ ውስጥ ሆኖ ፍለጋ ላይ የሚገኘው የዛሬው ዓለማችንም የምስራቹን ቃል መቀበል ያለበት ካዘኑ፣ ተስፋ ከቆረጡ፣ ትዕግሥት ከሌላቸው ወይም ከሚሰጉ ሰባኪዎች ሳይሆን፣ ሕይወታቸው በጋለ መንፈሳዊ ስሜት ከደመቀና፣ አስቀድመው የክርስቶስን ደስታ ከተቀበሉ የወንጌል አገልጋዮች ነው››፡፡

ዘላለማዊ መታደስ

የስብከት ተሐድሶ ለአማንያን እንዲሁም ለለዘብተኞችና ተሳትፎ ለሌላቸው ሰዎች ከስብከተ ወንጌል ሥራ የሚገኝ አዲስ የእምነትና የፍሬያማነት ደስታን ይሰጣቸዋል፡፡ የመልእክቱ ፍሬ ነገር ሁልጊዜ ያው ነው፤ ይኸውም፣ ጥልቅ ፍቅሩን በተሰቀለውና ከሞት በተነሣው ክርስቶስ የገለጠው እግዚአብሔር መሆኑን የሚያመለክት ነው፡፡ እግዚአብሔር የዕድሜ ልዩነት ሳያደርግ ምእመናኑን ያለማቋረጥ ያድሳል፡፡ እነርሱም ‹‹እንደ ንስር በክንፍ ይወጣሉ፣ ይሮጣሉ፣ ይበራሉ፣ አይታክቱም፤ ይሄዳሉ፣ አይደክሙም›› (ኢሳ.40፡31)፡፡ ክርስቶስ ‹‹የዘላለም ወንጌል›› ነው (ራእይ.14፡6)፡፡ እርሱ ‹‹ትናንት፣ ዛሬም ለዘላለምም ያው ነው›› (ዕብ.13፡8)፤ ሀብቱና ውበቱም አያልቅም፡፡ እርሱ ምን ጊዜም ወጣትና የተሃድሶ ምንጭ ነው፡፡ ስለሆነም ቤተክርስቲያን ‹‹ጥልቅ የሆነውን የእግዚአብሔርን የጥበብና የዕውቀት ባለጠግነት›› (ሮሜ.11፡33) ከማድነቅ ከቶ አትታክትም፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ዘመስቀል እንዳለው›› የእግዚአብሔር ጥበብና ዕውቀት እጅግ ጥልቅና ሰፊ ከመሆኑ የተነሣ፣ ነፍስ ምንም ያህል  ስለዚህ ነገር ብታውቅ፣ ሁልጊዜ ወደ እርሱ መሰረፅ ትችላለች››፡፡ እንዲሁም ቅዱስ ኤሬኔዎስ እንደ ጻፈው፡- ‹‹ክርስቶስ በመምጣቱ ከራሱ ጋር አዲስነትን አመጣ››፡፡ በዚህ አዲስነትም ሁልጊዜ ሕይወታችንን  ያድሳል፡፡ የክርስትና መልእክት፣ የጨለማ ጊዜያትና የቤተክርስቲያን ድክመት ቢያጋጥሙትም እንኳ፣ ፈጽሞ አያረጅም፡፡ ከዚህ ሌላ ኢየሱስን  የምንሸፋፍንባቸውን ከንቱ ሙከራዎች ያፈራርሳቸዋል፣ በመለኮታዊ ጥበቡም ዘወትር ያስደንቀናል፡፡ ወደ ምንጩ ለመመለስና የወንጌልን መሠረታዊ አዲስነት መልሰን ለማግኘት ጥረት ባደረግን ቁጥር አዳዲስ ጎዳናዎችና አዲስ የጥበብ መንገዶች ይከፈታሉ፡፡ እነርሱም የተለያዩ መገለጫዎች ያሉአቸው፣ ለዛሬው ዓለም አዲስ ትርጉም የሚሰጡና ይበልጥ ልብ የሚነኩ ምልክቶችና ቃላት ናቸው፡፡ ማንኛውም እውነተኛ ስብከተ ወንጌል  ምን ጊዜም ‹‹አዲስ›› ነው፡፡

ይህ ተልእኮ ከእኛ ትልቅ ልግስናን መጠየቁ እውነት ቢሆንም፣ እንደ ግለሰብ ጀብዱ ማየት ስሕተት ነው፡፡ ምክንያቱም፣ ይህ ከሁሉ አስቀድሞ እኛ ከምናየውና ከምንረዳው በላይ የሆነ የጌታ ሥራ ነውና፡፡ ኢየሱስ ‹‹የመጀመሪያውና ትልቁ ሰባኪ ነው››:: በማንኛውም የስብከተ ወንጌል ተግባር ውስጥ ቀዳሚው ምን ጊዜም ከእርሱ ጋር እንድንተባበር የጠራንና በመንፈሱ ኃይል የሚመራን እግዚአብሔር ነው፡፡ እውነተኛ ተሃድሶ እግዚአብሔር ራሱ ምሥጢራዊ በሆነ መንገድ የሚፈጽመው፣ የሚቀሰቅሰው፣ የሚያነሣሣው፣ በሺህ በሚቆጠሩ መንገዶች የሚመራውና አብሮት የሚጓዘው ተሃድሶ ነው፡፡ ስለዚህ፣ የቤተክርስቲያን ሕይወት ምን ጊዜም ቢሆን እግዚአብሔር ቅድሚያውን እንደሚወስድ፣ ማለትም ‹‹እርሱ አስቀድሞ እንደ ወደደን›› (1ዮሐ. 4፡19) እና እርሱ ብቻ ‹‹ማደግን እንደሚሰጥ›› (1ቆሮ. 3፡7) በግልጽ ማሳየት ይኖርበታል፡፡ ይህ እምነት ዕድሜ ልካችንን አብሮ የሚቆይ ከባድና ቀዳሚ በሆነ ተግባር ውስጥ ሆነን የደስታ መንፈስ እንዲኖረን ይረዳናል፡፡ እግዚአብሔር ከእኛ ሁሉን ነገር ይፈልጋል፣ ከዚሁ ጋር ለእኛ መልሶ ሁሉን ነገር ይሰጠናል፡፡

የዚህን ተልእኮ አዲስነት በአካባቢያችን ያለውንና ወደ ፊት የሚያራምደንን ሕያው ታሪክ እንደ መተካት ወይም እንደ መርሳት ልናየው አይገባም፡፡ ዳግም ትዝታ ‹‹deutronmic ›› ብለን የምንጠራው የእምነታችን ገጽታና  የእስራኤልን ዳግም ትዝታ የሚመስል ነው፡፡ ኢየሱስ የቤተክርስቲያን ዕለታዊ መታሰቢያ እና በእርሱ ፋሲካ በጥልቀት የመካፈል እውነት ይሆን ዘንድ ቅዱስ ቁርባንን ሰጠን (ንጽ.ሉቃ.22፡19)፡፡ የስብከተ ወንጌል ደስታ ሁልጊዜ የሚመነጨው ከምስጋና መታሰቢያ ነው፡፡ እኛም ያለማቋረጥ መለመን የሚገባን ጸጋ ነው፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ ልባቸውን የነካበትን ወቅት ከቶ አልረሱም፤ ጊዜው ‹‹ከቀኑ አሥር ሰዓት ያህል ነበር›› (ዮሐ.1፡39)፡፡ ከኢየሱስ ጋር ሆኖ ይህ መታሰቢያ ‹‹እንደ ደመና በዙሪያችን ያሉ ብዙ ምስክሮችን›› (ዕብ.12፡1) ያስታውሰናል፡፡ ከእነዚህም አንዳንዶቹን፣ እንደ ምእመናን፣ በታላቅ ደስታ የምናስታውሳቸው ናቸው፡- ‹‹የእግዚአብሔርን ቃል የነገሩአችሁን መሪዎቻችሁን አስቡ›› (ዕብ.13፡7) ተብለናልና፡፡ አንዳንዶቹም ለእኛ የሚቀርቡና የእምነትን ሕይወት ያስተማሩን ተራ ሰዎች ነበሩ፡፡ ‹‹ግብዝነት የሌለበት እምነትህን አስታውሳለሁ፤ ይህ እምነት ቀድሞ በአያትህ በሎይድ እንዲሁም በእናትህ በኤውንቄ ዘንድ ነበረ›› (2ጢሞ.1፡5)፡፡ ስለዚህ፣ አማኝ በመሠረቱ ‹‹አስታዋሽ›› ነው፡፡

ምንጭ፤ የወንጌል ደስታ ከተሰኘ የቅዱስ አባታችን ፍራንቸስኮስ በዛሬው ዓለም ወንጌልን ስለ መስበክ ለጳጳሳት፣ ለካህናት፣ ለደናግልና ለምእመናን ያስተላለፉት ሐዋርያዊ  ምክር ከአንቀጽ 9-13 ላይ የተወሰደ!

 

 

 

07 June 2023, 13:09