ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የብራዚል ፕሬዚደንት አቶ ኢናሲዮ ሉላን በቫቲካን ተቀብለው አነጋገሩ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
በቫቲካን ውስጥ ለፕሬዚደንት ሉላ የተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል አስቀድሞ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር የነበራቸውን የበርካታ ዓመታት ወዳጅነት የሚገልጽ ሲሆን፥ አቶ ኢናሲዮ ሉላ ብራዚልን ለሦስተኛ ጊዜ ለመምራት በኅዳር ወር 2022 (እ.አ.አ) በድጋሚ ከተመረጡ በኋላ ቫቲካንን ሲጎበኙ ይህ የመጀመሪያቸው ነው።
መልካም ድባብ የታየበት አቀባበል ነበር
ፕሬዚደንት ሉላ ከጣሊያኑ ፕሬዝደንት አቶ ሴርጆ ማታሬላ ጋር ያደረጉትን ውይይት ከፈጸሙ በኋላ ወደ ቫቲካን ደርሰው ከር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ጋር ተገናኝተው ለ45 ደቂቃ ያህል የዝግ ውይይት አድርገዋል። በውይይታቸው ማጠቃለያው ላይ ከልዑካን ቡድኑ ጋር የኅብረት ፎቶግራፍ እና የስጦታ ልውውጥ ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለፕሬዚደንት ሉላ ባቀረቡላቸው ስጦታዎች መካከል ለ2023 (እ.አ.አ) የጻፉት የዓለም የሰላም ቀን መልዕክት፣ በአረብ ኤምሬቶች አቡ ዳቢ ከተማ የተፈረመው የሰብዓዊ ወንድማማችነት ሠነድ፣ “ለሰው ልጅ በሙሉ የተስፋ መልዕክት የማድረስ ተልዕኮ” በሚል አርዕስት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ መጋቢት 27/2020 ዓ. ም. የጻፉት መጽሐፍ እና “ሰላም እንክብካቤን የሚሻ ተሰባሪ አበባ ነው” የሚል የተጻፈበት ከነሐስ የተሠራ ሐውልት ይገኙባቸዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ስጦታዎቻቸውን ባቀረቡበት ወቅት ባስተላለፉት አጭር መልዕክት፥ “ሰላም አደጋ ውስጥ በወደቀበት የጦርነት ጊዜ ላይ እንገኛለን!” ብለዋል። የብራዚል ቀዳማዊት እመቤት በበኩላቸው ከብራዚል ቤሌም ግዛት ያመጡትን የናዝሬቷ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ምስል በስጦታነት ለቅዱስነታቸው አበርክተዋል።
ወደ ቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤት ያደረጉት ጉብኝት
ፕሬዚደንት ኢናሲዮ ሉላ ከቅዱስነታቸው ጋር ከነበራቸው ቆይታ በኋላ ወደ ቫቲካን አስተዳደር ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት አምርተው፥ የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን ለመጽሐፍ ምረቃ ተጋብዘው ወደ ኡድኔ ክፍለ ሀገር በሄዱበት፥ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ግንኙነት ክፍል ምክትል ዋና ጸሐፊ ከሆኑት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኤጅጋር ፔኛ ፓራ ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል። በሁለቱ ወገኖች መካከል የተካሄደውን ውይይት በማስመልከት ከቅድስት መንበር የወጣው መግለጫ፥ በብራዚል እና በቅድስት መንበር መካከል ባለው መልካም ግንኙነት ሁለቱም ወገኖች እርካታቸውን መግለጻቸውን፥ ይህም በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን እና በብራዚል መንግሥት መካከል ያለውን መልካም ትብብር በማጉላት የሞራል እሴቶችን እና የጋራ ጥቅሞችን እንደሚያሳድግ መናገራቸውን መግለጫው አስታውቋል። በክልሉ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ሁኔታ ላይ አዎንታዊ የሃሳብ ልውውጥ መደረጉን እና የጋራ ጥቅምን በሚመለከት፥ ሰላምና እርቅን ማጎልበት፣ ድህነትንና የኑሮ አለመመጣጠንን መዋጋት፣ በአገሪቱ ውስ|ጥ የሚኖሩ ነባር ተወላጆችን ማክበር እና አካባቢን ከውድመት ማዳን በሚሉ መሪ ሃሳቦች ላይ ውይይት መካሄዱን የቅድስት መንበር መግለጫ በማከል አስታውቋል።
ብራዚልን እንዲጎበኙ ግብዣ ቀረበ
ፕሬዚደንት ሉላ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር ለመወያየት ከፈለጓቸው ርዕሠ ጉዳዮች መካከል፥ "ድህነትን አስወግዶ እኩልነት ማምጣት፣ ለሁሉም በቂ ምግብ ማፍራት በምትችል ምድራችን ላይ ያለውን ረሃብ መዋጋት” እንደሆነ በይፋ ገልጸዋል። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በሐምሌ ወር 2013 ዓ. ም. በብራዚል ሪዮ ዲ ጄኔሮ በተከበረው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫ ላይ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ መገኘታቸውን ፕሬዚደንት ሉላ አስታውሰው፣ ቅዱስነታቸው በብራዚል ለሁለተኛ ጊዜ ሐዋርያዊ ጉብኝት እንዲያደርጉ በማለት አዲስ ግብዣ አቅርበውላቸዋል። ፕሬዚዳንቱ ለብዙኃን በመገናኛ እንደተናገሩት፥ በብራዚል ውስጥ በሚከበሩ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በዓላት መካከል አንዱ በሆነው ቤሌም ግዛት ውስጥ በድምቀት በሚከበሩ የናዝሬቷ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዓመታዊ ክብረ በዓል ላይ ቅዱስነታቸው እንዲገኙ ከፍተኛ ምኞት ያላቸው መሆኑን ገልጸዋል።