ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ሰውን በግርፋት ማሰቃየት ሊቆም እንደሚገባ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መላው ካቶሊካዊ ምዕመናን በጸሎት እንዲተባበሯቸው በጠየቁት የሰኔ ወር የጸሎት ሐሳብ፣ ሰብዓዊ ክብር ከሁሉ በላይ መሆኑን ገልጸው፥ በዓለም ዙሪያ ሰዎችን በግርፋት እና የተለያዩ አካላዊ ጉዳቶችን በማድረስ የመፈጸም የማሰቃየት ተግባር መቆም እንዳለበት አሳስበዋል። ቅዱስነታቸው ይህን ማሳሰቢያ የላኩት በወርሃዊ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዓለም አቀፍ የጸሎት ጥሪ አስተባባሪ አውታረ-መረብ በኩል ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት ነው።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ሰዎችን ማሰቃየት የዛሬ ታሪክም ጭምር ነው

“ሰዎችን ማሰቃየት ያለፈ ታሪክ ሳይሆን ዛሬም የሚፈጸም ተግባር ነው” በማለት የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ካቶሊካዊ ምዕመናን በጸሎት እንዲተባበሯቸው በማለት ባቀረቡት የሰኔ ወር የጸሎት ሐሳብ፣ “ዛሬ በዓለማችን ላይ ከሚፈጸሙ እጅግ ኃይለኛ የማሰቃየት ዓይነቶች በተጨማሪ ሌሎች የተራቀቁ ዘዴዎች ጥቅም ላይ እንደሚውሉ፣ ሰውን ማዋረድ፣ ስሜትን መጉዳት እና የጅምላ እስራት የሰውን ክብር የሚነጠቁ ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች ናቸው” በማለት አስረድተዋል።

ቅዱስነታቸው ድርጊቱን ያወገዙበት እና የጸሎት ሃሳባቸውን ያቀረቡበት ምክንያት በአጋጣሚ እንዳልሆነ ሲታወቅ፣ የፊታችን ሰኔ 19/2015 ዓ. ም. የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለስቃይ ሰለባዎች ድጋፉን የሚገልጽበት ዓለም አቀፍ ቀን እንደሚሆን ታውቋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1987 ዓ. ም. የስቃይ እና ሌሎች የጭካኔ፣ የኢ-ሰብዓዊ ድርጊት፣ የውርደት አያያዝን እና የቅጣት ተግባርን የሚያወግዝ ሕግ የፀደቀበት እና እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ 1984 ዓ. ም. በኋላ በ 162 አገሮች ተግባራዊ ሆኖ መቆየቱ ይታወቃል።

“እነሆ ሰውየውን!”

በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በኢ-ሰብዓዊ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ እስረኞችን፣ ከወንበር ጋር የታሰሩትን፣ እጆቻቸው የጥፊኝ የታሰረባቸውን እና ወቅታዊ የስቃይ ልማድ የሚፈጸምባቸው ሰዎች ምስልን በማሳየት የሚጀምረው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዓለም አቀፍ የጸሎት ጥሪ ቪዲዮ፣ ምንጣፎችን፣ ገመዶችን፣ ባትሪዎችን፣ መዶሻዎችን የያዙ ባልዲዎች በማሳየት፣ አንድን ሰው ወደ ዕቃነት ዝቅ ለማድረግ የሚሞክር ሰው ከሁሉ አስቀድሞ የራሱን ወይም የራሷን ስብዕናን እንደሚያጣ ለማስረዳት የቀረበ ሲሆን፣ ይህ ምናባዊ የማሰቃያ ክፍል ዝርዝር ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የዚህ ወር መልዕክት ጋር የሚመሳሰል እና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሲያሰቃዩት፣ ሲገርፉት እና ሲያላግጡበት ያጋጠመው መከራ ይህ እንደ ነበር ያስታውሰናል።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሕማማቱ ወቅት ስቃይ ደርሶበታል። እነዚያን የስቃይ ምልክቶችን ተሸክሞ ሞቷል። የእሾህ እና የጅራፍ ቁስሎችን፣ የጥፊ ምልክቶችን፣ በወገቡ ላይ የታሰረውን ገምድ ጭምር የሚያሳየው የቪዲዮ ቅንብሩ፣ በጣሊያን ክሮቶኔ ከተማ ውስጥ በሚገኝ የሜሶራካ ቤተ መቅደስ ውስጥ የሚገኘውን “እነሆ ሰውየውን!” የሚል ስያሜ ከተሰጠው ምስል ጋር ቅርበት ያለው ነው። እነዚህ ምስሎች እውነተኛ ታሪክን የሚያሳዩ በመሆናቸው አስደናቂዎች ናቸው።

በዓለም አቀፍ ሕግ ጥላ ስር የሚገኝ የተከለከለ አሠራር

በግርፋት ማሰቃየት ከጥንት ጀምሮ የነበረ ተግባር ነው። በ18ኛው እና በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ምዕራባውያን አገራት ድርጊቱን በፍትህ ሥርዓት በይፋዊ አስቀርተውታል። ዛሬ በዓለም አቀፍ ሕግም ሙሉ በሙሉ የተከለከለ ተግባር ነው። ያም ሆኖ ግን በብዙ አገሮች ተግባሩ ቀጥሏል። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ1981 ዓ. ም. ጀምሮ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሁሉም የዓለማችን ክፍሎች የሚገኙ በአማካይ 50,000 የሚደርሱ የስቃዩ ሰለባዎችን በየዓመቱ እየረዳቸው ይገኛል።

በእርግጥ የማሰቃየቱ ተግባር በግጭት ቀጠናዎች ውስጥ በሚገኙ አገራት ውስጥ ይከሰታል። የሩስያ ወታደሮች በዩክሬ ላይ ጥቃት በፈጸመችበት ወቅት በሰላማዊ ሰዎች ላይ ያደረሱትን የማሰቃየት ተግባር የሚገልጹ ዘገባዎች ይፋ ሆነዋል። በተጨማሪም በከፊል አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች በመጡ ቁጥር ሥነ-ልቦናዊ ማሰቃየት የመሳሰሉ አንዳንድ አካላዊ ያልሆኑ የስቃይ ዘዴዎች ጨምረዋል። ከዚህም በላይ ጉዳዩን የሚያባብሰው በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሚደርስ ሰቆቃ እና እንግልት ተጠያቂነት አለመኖሩ፣ ሥርዓቱን በግድ የለሽነት መያዝ እና መካድ፣ የመንግሥት ባለስልጣናት መሰናክል በመሆን ሆን ብለው ከሃላፊነት መሸሻቸው ድርጊቱ የተጎጂዎች ቁጥር የመመዝገብ እና የመገመት ሂደቱን አስቸጋሪ አድርጎታል።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አቤቱታ

የድርጊቱን አስከፊነት ተመልክተው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ባቀረቡት አቤቱታ፥ ለተጎጂዎች እና ቤተሰቦቻቸው ድጋፍ በማድረግ እና ዋስትና በመስጠት የማሰቃየት ድርጊትን ለማስወገድ ተጨባጭ ቆራጥነትን እንዲያሳይ ጠይቀዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ቀደም ሲል እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2014 ዓ. ም. ባደረጉት ንግግር፥ እነዚህን በደል ማስቆም የሚቻለው ከምንም ነገር በላይ ለሰው ልጅ ክብር እውቅናን ለመስጠት የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጽኑ ቁርጠኝነት ሲኖረው እንደሆነ ጠቁመዋል።

ኢየሱስ ክርስቶስ ተገርፏል፣ ተሰቅሎአልም

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዓለም አቀፍ የጸሎት ጥሪ አውታረ-መረብ አስተባባሪ፣ አባ ፍሬደሪክ ፎርኖስ በበኩላቸው፣በጸሎት ጥሪ ዓላማ ላይ ብሰጡት አስተያየት፥ በምንም ምክንያት ቢሆን ሰውን ማሰቃየት ፈጽሞ ትክክል ሊሆን እንደማይችል ገልጸው፥ ሰውን ማሰቃየት ከባድ ኃጢአት እንደሆነ፣ ክርስቲያን ማኅበረሰቦች የስቃይ ሰለባዎችን መርዳት እንደሚገባ እና ለክርስቲያኖች በሙሉ ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ገጽታ እንደሆነ በቲውተር ማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ሰኔ ወር 2018 ዓ. ም. በመጻፍ መግለጻቸውን አባ ፍሬደሪክ አስታውሰዋል።

“በታሪክ ዘመናት በሙሉ ኢየሱስ ክርስቶስ በሕማማቱ በኩል ወደ ሁሉም የስቃይ ሰለባዎች ዘንድ ቀርቧል” ያሉት አባ ፍሬዴሪክ፥ በዚህም ምክንያት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” ባሉት ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ቁ. 227 ላይ፥ “በሰው ልጅ ላይ የሚፈጸመው የአመጽ ድርጊት በሙሉ በሰው ልጅ ሥጋ ላይ የሚፈጠር ቁስል ነው' ማለታቸውን አስታውሰው፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ምዕመናን በሰኔ ወር ውስጥ እንዲተባበሯቸው ያቀረቡት የጸሎት ሃሳብ፥ በታገቱት፣ በታሰሩት ላይ እና ታፍነው በተወሰዱት ሰዎች ላይ የሚፈጸም ማንኛውም ዓይነት ስቃይ እንዲወገድ ጥያቄን ያቀረቡበት እና ለተጎጂዎች እና ቤተሰቦቻቸው የድጋፍ ዋስትና እንዲኖራቸው አቤቱታቸውን ያቀረቡበት ሃሳብ መሆኑን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዓለም አቀፍ የጸሎት ጥሪ አውታረ-መረብ አስተባባሪ፣ አባ ፍሬደሪክ ፎርኖስ አስረድተዋል።

08 June 2023, 16:50