ፈልግ

JAPAN-G7-SUMMIT

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከብራዚል ፕሬዚደንት ጋር ስለ ዩክሬይን ሰላም እና ስለ ድኅነት ቅነሳ ተወያዩ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና የብራዚል ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ሉዊስ ኢኛሲዮ ሉላ ግንቦት 23/2015 ዓ. ም. በስልክ የሃሳብ ልውውጥ ማድረጋቸውን የቅድስት መንበር መግለጫ ክፍል እና የብራዚል መንግሥት አስታውቀዋል። ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በላቲን አሜሪካ ውስጥ የሚገኘውን የአማዞን ደንን ከጥፋት ለመከላከል በማድረግ ላይ የሚገኙትን ከፍተኛ ጥረት በማስታወስ ፕሬዚደንቱ አመስግነው፣ ቅዱስነታቸው ብራዚልን ለሁለተኛ ጊዜ እንዲጎበኙት በማለት ግብዣቸውን አቅርበውላቸዋል። በስፋት ከተወያዩባቸው ርዕሠ ጉዳዮች መካከል አንዱ በዩክሬይን ውስጥ ሰላምን ለማስፈን የሚያግዙ ርዕሠ ጉዳይ እንደ ነበር የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል እና የብራዚል መንግሥትም በድረ ገጹ ላይ ባሠፈረው ጽሑፍ አስታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የብራዚል ፕሬዚደንት አቶ ሉዊስ ኢኛሲዮ ሉላ በዩክሬይን ሰላም የሚወርድበትን መንገድ በማስመልከት በቅርቡ በሰጡት አስተያየት፣ በዩክሬን ውስጥ ለሚካሄደው ጦርነት ሰላማዊ መፍትሄን የሚያቀርቡ፣ ብራዚልን ጨምሮ የሌሎች አገራት ተወካዮች የሚገኙበት ቡድን እንዲመሠረት ሃሳብ ማቅረባቸው ሲታወስ፣ በማከልም በዩክሬይን ሰላምን ለማምጣት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እስካሁን ላደረጓቸው እና በማድረግ ላይ ለሚገኙት ጥረቶች ምስጋናቸውን አቅርበው፣ በተጨማሪም በዩክሬይን ሰላም እንዲወርድ ከሚሹ ሌሎች መሪዎች ጋር ያደረጉትን ውይይት አስታውሰዋል።

ድህነትን መዋጋት እና የአማዞን ደንን ከጥፋት መከላከል

የብራዚሉ ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ሉዊስ ኢኛሲዮ ሉላ በማከልም፣ በብራዚል የምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ድህነት በመዋጋት እና የአማዞን ደንን ከአጥፊዎች ለመከላከል ላሳየችው ጥረት ቅዱስነታቸውን አመስግነዋል። በላቲን አሜሪካ አገራት በእነዚህ ጊዜያት የተቀሰቀሱት የተቃውሞ ሰልፎች፣ መሬታችንን ተነጠቅናል የሚሉ የአካባቢው ነዋሪዎች የሚያካሂዱት ወቅታዊ ርዕሠ ጉዳይ እንደ ሆነ ይታወቃል። የአማዞን አካባቢን በተመለከተ ከዚህ በፊት ማለትም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2019 ዓ. ም. የአካባቢው አገራት ሲኖዶሳዊ ጉባኤን ያካሄደበት እና ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስም ዘወትር የሚያስታውሱት የዓለማችን ክፍል እንደሆነ ይታወቃል።

ከብራዚል ጎን መቆም

የብራዚል ፕሬዚደንት አቶ ሉዊስ ኢኛሲዮ ሉላ ግንቦት 23/2015 ዓ. ም. ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር ያደረጉትን የስልክ ውይይት ያስታወሰው መግለጫው፥ በቅርብ ዓመታት ውስጥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከብራዚል ጋር ያላቸውን አንድነት እና ትብብርንም በማስታወስ ምስጋና ማቅረባቸውን ጠቅሷል። በተጨማሪም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስት ፍራንችስኮስ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በመስከረም እና በጥቅምት 2022 ዓ. ም. በቫቲካን ሐዋርያዊ ጉብኝት ያደረግትን የብራዚል ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳትን ተቀብለው ማነጋገራቸውን ጠቅሶ፣ ወቅቱም አገሪቱ ብሔራዊ ምርጫን ለማካሄድ የምዘጋጅበት እና ብዙ ውጥረቶች እና አለመግባባቶች የታዩበት ወቅት እንደነበረም አስታውሷል።

ብራዚልን እንዲጎበኙ ግብዣ ቀርቦላቸዋል

በብራዚል ድህነትን እና ረሃብን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት በተመለከተ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር በተደጋጋሚ የተወያዩት ፕሬዚደንት ሉላ፣ ብራዚል በእነዚህ ችግሮች ከሚታወቁት የዓለም አገሮች መካከል አንዷ መሆኗን በመግለጽ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በብራዚል ሐዋርያዊ ጉብኝት እንዲያደርጉ በማለት ግብዣቸውን አቅርበው፣ ቅዱስነታቸው ግብዣውን ከግምት ውስጥ እንደሚያስገቡ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

የፕሬዚደንት ሉላ የቫቲካን ጉብኝት

ፕሬዚደንት ሉላ በያዝነው ዓመት ሰኔ ወይም ሐምሌ ወር ላይ ቫቲካንን ሊጎበኙ እንደሚችሉ ያስታወቀው የመንግሥት መግለጫው፣ የፕሬዚደንቱ ጉብኝት የመጀመሪያ እንዳልሆነ፣ ከዚህ በፊት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2009 ዓ. ም. እና እንደ ጎሮጎሮሳውያኑ በ2020 ዓ. ም. በድጋሚ ቫቲካንን መጎበኘታቸውን መግለጫው አስታውሷል። ፕሬዚደንት ሉላ ቫቲካንን በጎበኙበት ወቅት ያደረጓቸው ውይይቶች ዴሞክራሲን፣ የአካባቢ ጥበቃን እና ማኅበራዊ እኩልነትን፣ ወጣቶችን እና ድሃውን ማኅበረሰብ በሚያሳትፍ ኤኮኖሚ ላይ ያተኮረ እንደ ነበር ይታወሳል። ፕሬዚዳንቱ ቀጥለውም ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር በትዊተር ማኅበራዊ መገናኛ በኩል ባደረጉት ውይይት ፍትኅን እና ወንድማማችነትን የተመለከቱ ርዕሠ ጉዳዮች በማንሳት መወያየታቸውን መግለጫው አስታውሷል።

01 June 2023, 12:49