ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ከሰሜን አሜሪካ የመጡ የሰበካ ዘርዓ ክኅነት ማኅበረሰብን በቫቲካን ተቀብለዋል ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ከሰሜን አሜሪካ የመጡ የሰበካ ዘርዓ ክኅነት ማኅበረሰብን በቫቲካን ተቀብለዋል   (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ ካኅናት የመሐሪት ቤተ ክርስቲያን ምልክቶች ሊሆኑ ይገባል አሉ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የካቲት 27/2015 ዓ. ም. ከሰሜን አሜሪካ፣ ክሊቭላንድ የሚገኝ የእመቤታችን ቅድስት ማርያም የሰበካ ዘርዓ ክኅነት ማኅበረሰብን በቫቲካን ተቀብለው ንግግር አድርገውላቸዋል። ቅዱስነታቸው ለእንግዶቹ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ከሲኖዶሳዊነት ሂደት ጎን ለጎን ለክኅነት አገልግሎት እንዴት መዘጋጀት እንደሚገባ ተናግረው፣ ወንድማማችነትንም ማሳደግ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

መደማመጥ፣ አብሮ መጓዝ እና የወንጌል ምስክርነት፣ ቤተ ክርስቲያን እያካሄደች ያለችው የሲኖዶሳዊ ጉዞ ባህሪያት ለክኅነት አገልግሎት ለሚዘጋጁት ወሳኝ መሆናቸውን፣ በቫቲካን ለተቀበሏቸው በሰሜን አሜሪካ የእመቤታችን ቅድስት ማርያም የሰበካ ዘርዓ ክኅነት ማኅበረሰብ አስረድተዋል። ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ የምሥረታውን 175ኛ ዓመት በአል ለማክበር በሰሜን አሜሪካ ከኦሃዮ ግዛት ወደ ሮም ለመጡት ካህናት፣ ዲያቆናት፣ የዘርዓ ክኅነት ተማሪዎች፣ መምህራን እና ሠራተኞች ባደረጉት ንግግር፥ ካህናት በደቀ መዝሙርነት ተልዕኮ ጥሪ በመመራት፣ ለእግዚአብሔር ሕዝብ የሚያቀርቡት የወንጌል አገልግሎት አስፈላጊነት፣ በተለይም መላው ቤተ ክርስቲያን በሚያካሂደው የሲኖዶሳዊ ጉዞ አውድ ውስጥ፣ ለክኅነት ምስጢር እና ለሐዋርያዊ አገልግሎት በመዘጋጀት ላይ ለሚገኙት ጠቃሚ ምክሮችን ለግሠዋል።

የእግዚአብሔርን ቃል ማዳመጥ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የእግዚአብሔርን ቃል ስለ ማዳመጥ በሰጡት ምክራቸው፣ ከምንም ነገር በላይ ለእግዚአብሔር በየቀኑ ቦታን መስጠት፣ ቃሉን ማሰላሰል፣ ለጉዞ የሚሆን ብርሃን መፈለግ እንደሚገባ፣ መንፈሳዊ ድጋፍ ሊኖር እንደሚገባ እና እግዚአብሔርን ወደ መንበረ ታቦቱ ፊት ቀርቦ በጸጥታ እርሱን ማዳመጥ እንደሚገባ አሳስበዋል። “እራስን ወደ እግዚአብሔር ፊት የማቅረብን አስፈላጊነት ፈጽሞ መዘንጋት የለባችሁም” ያሉት ቅዱስነታቸው፣ የእግዚአብሔርን ድምፅ በልባችን ውስጥ መያዝ እና ፈቃዱን ማስተዋል ለመንፈሳዊ ዕድገታችን፣ በተለይም ለአስቸኳይ አገልግሎት ስንዘጋጅ እጅግ አስፈላጊ ናቸው” ብለዋል። “የዘርዓ ክኅነት ሕያወት የጸሎት ልማድን ለማዳበር ዕድል ይሰጣል" በማለት የገለጹት ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ ጸሎት ለክኅነት አገልግሎት አጋዥ እንደሆነ፣ እግዚአብሔርን ማዳመጥ እርሱ ለገለጠው እና ቤተ ክርስቲያን ለምታስተላልፈው ሁሉ የእምነት ምላሽን ለመስጠት እንደሚረዳ ገልጸው፣ ካኅናት በጸሎት በመታገዝ የቅዱስ ወንጌልን እውነት አስደሳች በሆነ መንገድ ለሌሎች ማስተማር እንደሚችሉ አስረድተዋል። 

የኅብረት መንፈስ ማጠናከር

አብሮ መጓዝ  ሌላው የሲኖዶሳዊነት ጉዞ ባህሪ እንደሆነ የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ የዘርዓ ክኅነት ተማሪዎች ለክህነት በሚዘጋጁበት ወቅት የቤተ ክርስቲያንን አንድነት በተግባር እንዴት መኖር እንደሚችሉ ሲመክሩ፥ “በዘርዓ ክህነት ትምህርት ቤት ሕይወት በመካከላቸው ብቻ ሳይሆን ከጳጳሳት፣ ከካኅናት፣ ከገዳማውያን እና ገዳማውያት፣ እንዲሁም ከምእመናን ጋር ያለውን የወንድማማችነት መንፈስ የሚያጎለብቱበት አጋጣሚ፣ ራሳችንን የእግዚአብሔርን የተስፋ ቃል የተቀበልን የትልቅ ሕዝብ አካል መሆናችንን ማወቅ አለብን” ብለዋል። “የክህነት ሕይወትን የሚመርጡ ሰዎች ጥሪም ታላቅ ስጦታ ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው፣ የክርስቶስን አካል ማነጽን በአገልግሎት ላይ ማዋል፣ “ከመንጋው ጋር በመራመድ፣ መንገዱን ለማሳየት አንዳንዴ ወደፊት እየቀደሙ፣  ለማበረታታት አንዳንዴ በመካከላቸው እየሆኑ፣ ብዙ የሚለፉትን ለማጀብ አንዳንዴም ከኋላቸው እየሆኑ፣ በኅብረት መጓዝ ይገባል” ብለዋል።

ካኅናት የወንጌል መስካሪ ቤተ ክርስቲያን ምልክቶች ናቸው

ምስክርነት "በዓለም ላይ የኢየሱስ ክርስቶስ ሕያው ምልክቶች" መሆን እንደሆነ የገለጹት ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ ምስክርነት እግዚአብሔርን የመስማት እና አብረው የመጓዝ ፍሬ እንደሆነ አስረድተው፣ በዘርዓ ክኅነት ቤት የሚያሳልፏቸው ዓመታት፣ ለእግዚአብሔር እና ለምዕመናን የተሰጠውን ጠቅላላ ስጦታ በፍቅር እና በአንድ ልብ እንዲዘጋጁበት በማለት ምኞታቸውን ገልጸውላቸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ንግግራቸውን ሲያጠቃልሉ፣ የዘርዓ ክኅነት ተማሪዎችን በጸሎታቸው እንደሚያስታውሷቸው አረጋግጠው፣ በሐዋርያዊነታቸው የወንጌል ምስክርነት ጥሪዋን በመወጣት ላይ የምትገኝ ቤተ ክርስቲያን ምልክት እንዲሆኑ፣ የኢየሱስ ክርስቶስን መሐሪ ፍቅር ለመላው የሰብዓዊ ቤተሰብ በተለይም ለድሆች እና ችግረኞች እንዲመሰክሩ እና እንዲያካፍሉ አደራ ብለው፣ ከዘርዓ ክኅነት ትምህርት ቤት የሚቀስሟቸው መንፈሳዊ ዕውቀቶች፣ ለእግዚአብሔር ያላቸውን ታማኝ ፍቅር እና ለባለ እንጀራዎቻቸው የሚያቀርቡትን የትህትና አገልግሎት እንዲያሳድግላቸው በመመኘት ንግግራቸውን ደምድመዋል።

07 March 2023, 16:15