ፈልግ

በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተመቅደስ አጠገብ የተገነባ የሕክምና ማዕከል  በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተመቅደስ አጠገብ የተገነባ የሕክምና ማዕከል  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ እያንዳንዱ ታማሚ ሕጻን በወላጆቹ ርኅራኄ ሊታገዝ ይገባል አሉ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በሰሜን ጣሊያን፣ ሚላን ከተማ ለተፈጸመ የሆስፒታል ምረቃ ሥነ-ሥርዓት መልዕክት ልከዋል። ቅዱስነታቸው ዓርብ መጋቢት 15/2015 ዓ. ም. በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ ለተገኙት አባላት በላኩት መልዕክታቸው፣ ባለባቸው ሕመም ምክንያት ለተለያዩ የሕክምና ዕርዳታ ወደ ሆስፒታል ለሚገቡ ሕጻናት ልጆቻቸው ወላጆች ርኅራሄን በመግለጽ ከጎናቸው መሆን እንዳለባቸው አደራ ብለዋል። ቅዱስነታቸው አክለውም፣ ሆፒታሉ በሽታውን ለመቋቋም፣ በተለይም ከሕጻናት ልጆቻቸው ጋር ጥረት የሚያደርጉ ወላጆችን በደስታ ተቀብሎ ሕልሙን እውን ያደርገዋል ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በሕመም ላይ ለሚገኝ እያንዳንዱ ሕጻን እንክብካቤን ከሚያደርጉ ዶክተሮች እና ነርሶች በተጨማሪ፣ የእናት እና የአባት ፍቅር፣ ርኅራሄ እና ቅርበት መሠረታዊ እንደሆነ ቅዱስነታቸው አስረድተው፣ "አንዲት ሕጻን ወይም አንድ ሕጻን በጠና ሲታመም ልዩ የባለሙያ ዕርዳታ ያስፈልጋል” ብለው፣ ብዙውን ጊዜ ይህ ዕርዳታ ወይም እንክብካቤ ከቤት ርቀው በሚገኙ ሆስፒታሎች ውስጥ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ወላጆች በሕመም ከሚሰቃዩ ልጆቻቸው ጎን የመሆን ዕድል መኖር አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው፣ በሰሜን ጣሊያን ሚላን ከተማ ውስጥ ለሕጻናት የሕክምና ዕርዳታን ለመስጠት የተገነባው እና "ካዛ ፋብሪሲዮ ፍሪዚ" ተብሎ ለሚጠራ የሕክምና ማዕከል የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ባስተላለፉት መልዕክት፣ የሆስፒታሉ ተነሳሽነት እና ዋና ዓላማ እውን የሚሆነው፣ በሕመም የሚሰቃዩ ሕጻናት ቤተሰቦችን በተለይም እናቶችን እና አባቶችን በደስታ ተቀብሎ ማስተናገድ እንደሆነ ገልጸዋል።

እውን የሚሆን ህልም

ከአምስት ዓመት በፊት በሕመም ምክንያት በሞተው ፋብሪሲዮ ፍሪዚ በተባለ ሕጻን ስም ለተገነባው ሆስፒታል ድጋፍ ማድረጋቸውን የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ወደ ሃያ ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ “ዩኒታልሲ” ከተሰኘ ፕሮጄክት ጋር ታላቅ ወዳጅነት እንዳላቸው አስታውሰዋል። ለሕክምና ማዕከሉ ግንባታ አስተዋፅዖ ላደረጉት በሙሉ ምስጋናቸውን ያቀረቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ከሁሉም በላይ የ“ዩኒታልሲ” ፕሮጄክት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ቪቶሬ ዴ ካርሊን በመጥቀስ ለቆራጥነታቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙት መንፈሳዊ አባቶች እና መንግሥታዊ ሃላፊዎች
በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙት መንፈሳዊ አባቶች እና መንግሥታዊ ሃላፊዎች

ቅድስት ድንግል ማርያም የቤተሰብ ደጋፊ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለሆስፒታሉ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት የላኩትን መልዕክት ሲያጠቃሉ፣ ሆስፒታሉ በአካባቢው በምትገኝ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የጸጋዎች ሁሉ እናት ቤተመቅደስ አጠገብ መገንባቱን ገልጸው፣ “ውድ ሕዝብ!” ላሏቸው የሚላን ከተማ ነዋርዎች ባስተላለፉት መልዕክትም፣ ነዋሪዎቹ ከሰማይ የሚመጡላቸውን ስጦታዎች ለመጠየቅ፣ ሕይወትን እና የኅብረተሰቡን ቁስሎች እንድትፈውስ ፊታቸውን በጸሎት ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ማዞራቸውን በማስታወስ፣ በሕክምና መስጫ ማዕከሉ ውስጥ ለሚቆዩ ወላጆች በሙሉ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የርኅራኄ እና የመጽናናት ድጋፍን በመለመን መልዕክታቸውን ደምድመዋል።

በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙት መንፈሳዊ እና መንግሥታዊ ሃላፊዎች
በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙት መንፈሳዊ እና መንግሥታዊ ሃላፊዎች
25 March 2023, 15:49