ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ወደ ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ የመማጸኛ ጸሎት ባቀረቡበት ወቅት ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ወደ ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ የመማጸኛ ጸሎት ባቀረቡበት ወቅት   (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ለሩሲያ እና ዩክሬን ሰላም ጸሎት ማድረግ የጀመሩበትን አንደኛ ዓመት አስታወሱ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በጦርነት ውስጥ በሚገኙት ሩስያ እና ዩክሬን ሰላም እንዲወርድ ወደ እመቤታችን ቅድስት ማርያም ጸሎት ያቀረቡበትን አንደኛ ዓመት በማስታወስ፣ ምእመናን እና የጸሎት ማኅበራት በሙሉ በየዓመቱ መጋቢት 16 ቀን በሚቀርብ የሰላም ጸሎት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበው፣ “እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከልጇ ከኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምን በመለመን ሕዝቦች በአንድነት እንዲኖሩ ልታደርግ ትችላለች” ብለዋል። ቅዱስነታቸው ጥሪያቸውን ያቀረቡት ረቡዕ መጋቢት 13/2015 ዓ. ም. ባቀረቡት ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ማጠቃለያ ሲሆን፣ በጦርነት ስቃይ ውስጥ የሚገኘውን የዩክሬን ሕዝብ ባስታወሱበት ንግግራቸው፣ እያንዳንዱ ሕይወት የተቀደሰ እና ክብሩም የማይጣስ መሆኑን አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከአንድ ዓመት በፊት፣ ዓርብ መጋቢት 16/2014 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ በተዘጋጀው የሰላም ጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ ተገኝተው ወደ እመቤታችን ቅድስት ማርያም ፊት ቀርበው በመላው ዓለም ለሚገኙ የሰው ልጆች በተለይም በጦርነት አደጋ ውስጥ በሚገኙት ሩሲያ እና ዩክሬን መካከል ሰላም እንዲወርድ የእመቤታችን ማርያም አማላጅነት በጸሎት መማጸናቸው ይታወሳል። ከቅዱስነታቸው ጋር በጸሎት በመተባበር፣ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ እና በአደባባዩ ከተሰበሰቡት በርካታ ምዕመናን በተጨማሪ በዓለም ዙሪያ የሚገኙት ካቶሊካዊ ቁምስናዎች ምዕመናንም፣ በሩሲያ እና ዩክሬን መካከል ጥላቻ እና ቂም በቀል ቀርቶ ሰላም እንዲወርድ በማለት ወደ ንጽሕት እመቤታችን ማርያም ዘንድ መማጸናቸው ይታወሳል።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ረቡዕ መጋቢት 13/2015 ዓ. ም. ባቀረቡት ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸው ማጠቃለያ ላይ ለምዕመናኑ ባቀረቡት ጥሪ፣ ከአንድ ዓመት በፊት በመላው ካቶሊካዊ ምዕመናን ዘንድ የነበረውን ጥልቅ የሰላም ተማጽኖ ጸሎትን አስታውሰው፣ በሩስያ እና ዩክሬን መካከል የሚካሄደው ጦርነት በቀጠለበት በዚህ ጊዜም የሰላም ተስፋ እውን ሊሆን እንደሚችል ገልጸው፣ "ለሃያ አራት ሰዓት ወደ እግዚአብሔር ዘንድ በጸሎት እንቅረብ" የሚለው ተነሳሽነት ሳይቆርጥ እንዲቀጥል አደራ ብለዋል። 

ወደ ሰላም ንግሥት የሚቀርብ የሰላም ልመና

የላቲን ሥርዓተ አምልኮን በምትከተል ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ዘንድ መጭው ቅዳሜ መጋቢት 16/2015 ዓ. ም. መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሰላምታ ያቀረበበት መታሰቢያ ቀን በጸሎት እንደሚከበር የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ያለፈው ዓመት በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት በሙሉ በአንድንት ለሰው ልጆች በተለይም በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል ሰላም እና እርቅ እንዲወርድ ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ንጹሕ ልብ ጸሎት ያቀረቡበት ዕለት እንደነበር አስታውሰው፣ “ዘንድሮም ሳንታክት ወደ ሰላም ንግሥት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ልመናችንን እናቅርብ” ብለዋል።

የዩክሬን ሕዝብን በጸሎት እናስታውስ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ረቡዕ መጋቢት 13/2015 ዓ. ም. ባቀረቡት ጥሪ "እያንዳንዱ ክርስቲያን እና ክርስቲያን ማኅበረሰብ በተለይም የጸሎት ማኅበራት፣ በየዓመቱ መጋቢት 16 ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የሚያቀርቡትን የሰላም ተማጽኖ ጸሎት እንዲያድሱ በማለት ይጠይቀዋል። “እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከልጇ ከኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምን በመለመን ሕዝቦች በአንድነት እንዲኖሩ ልታደርግ ትችላለች” ብለው፣ “በዚህን ጊዜ በመከራ ውስጥ የሚገኝ የዩክሪን ሕዝብ ሳንዘነጋ በጸሎት እናስታውስ” ብለዋል።

በመልአኩ ላይ ያለው ትውስታ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ ያለፈው መጋቢት 3/2015 ዓ. ም. ከምዕመናን ጋር ባቀረቡት የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ፣ "ለሃያ አራት ሰዓት ወደ እግዚአብሔር ዘንድ በጸሎት እንቅረብ" በማለት ያቀረቡትን ተነሳሽነት በማስታወስ፣ ተነሳሽነቱ ከእግዚአብሔር ዘንድ “የሰላም ስጦታን” ለመጠየቅ የቀረበ መሆኑን አስረድተዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም፣ እግዚአብሔር በእናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት የሚቀርብ የሕዝቡ ልመናን ሁል ጊዜ እንደሚሰማ፣ ወደ እርሱ የምናቀርበው የአደራ ጸሎት ከንቱ ሆኖ ስለማይቀር ተስፋችንን መቁረጥ እንደሌለብን አደራ ብለዋል።

የሰውን ሕይወት ከጥፋት በመከላከል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ረቡዕ መጋቢት 13/2015 ዓ. ም. ባቀረቡት ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸው ማጠቃለያ፣ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙት የፖላንድ ካቶሊካዊ ምዕመናንም ሰላምታቸውን አቅርበው፣ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሰላምታ ያቀረበበት መታሰቢያ ቀን መጋቢት 16፣ በፖላንድ “የሕይወት ቅድስና” የሚከበርበት ቀን መሆኑንም አስታውሰዋል።

ይህም የሰውን ሕይወት ከተጸነሰበት ዕለት እስከ ተፈጥሯዊ ሞት ድረስ የመጠበቅ እና የመንከባከብ አስፈላጊነት" እንደሚያመላክት የገለጹት ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ ዛምቢያ ውስጥ ለሚገኝ አንድ የሕይወት ተንከባካቢ ፋውንዴሽን የሚላክ ግዙፍ ደወል ባርከው፣ "በማህፀን ውስጥ የሚገኝ ሕጻን ድምጽ" የሚል ስም የተሰጠው ይህ ደወል እያንዳንዱ ሕይወት የተቀደሰ እና ክብሩም የማይጣስ ነው የሚል መልዕክት የሚያስተላልፍ  መሆኑን ተናግረዋል።

23 March 2023, 16:17