ፈልግ

የባሕር ውስጥ ብዝሃ ሕይወት የባሕር ውስጥ ብዝሃ ሕይወት 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ ውቅያኖሶች የሕዝቦች መገናኛ እንጂ የአደጋ ሥፍራ መሆን የለባቸውም አሉ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በቅርቡ በፓናማ ከተማ ተካሂዶ ለተጠናቀቀው የውቅያኖስ ውሃ ደኅንነት ጥበቃ ጉባኤ መልዕክት አስተላልፈዋል። በቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ በሆኑት በብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን ተፈርሞ በተላከው መልዕክታቸው ቅዱስነታቸው፣ የውቅያኖስ ውሃ የሰው ልጆች በሙሉ የሚመኩበት የግንኙነት መድረክ መሆኑን በማስገንዘብ፣ ይህን ሰፊ የምድራችን ክፍል በተመለከተ ሁሉ አቀፍ የልማት እና የስነ-ምህዳር ዕይታን ማጎልበት እንደሚያፈልግ፣ የምድራችን ውሃን ከብክለት ለመጠበቅ እና ብዝሃ ሕይወትን ከጉዳት ለመጠበቅ ስምምነት ለተደረሰበት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኒውዮርክ ጉባኤ በላኩት መልዕክት አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው ለጉባኤው ተሳተፊዎች በላኩት መልዕክት፣ ውቅያኖሶች በሕዝቦች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጎልበት የጋራ መንስኤ ሊሆን እንደሚችል ገልጸው፣ ይህን ትስስር በሚገባ ለመረዳት፣ የድሆችን ጩኸት እና የምድራችን ዋይታ ማዳመጥ እንደሚገባ፣ በአባካይኝነት እና በፍጆታ ላይ የተመሠረቱ የዕድገት ስልቶችን፣ ኢ-ፍትሃዊ እና ዘላቂነት የሌላቸው የምርት፣ የትራንስፖርት፣ የስርጭት እና የፍጆታ ሞዴሎችን መገምገም እንደሚያስፈልግ፣ በፓናማ ከተማ ከየካቲት 23-24/2015 ዓ. ም. በተካሄደው ስምንተኛ ዙር የውቅያኖስ ውሃ ድህንነት ጉባኤ በላኩት መልእክት አሳስበዋል።

የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ መልዕክት ጉባኤውን የደረሰው፣ አሥር ከመቶ በላይ የሚሆኑ ብርቅዬ ዝርያዎች ለመጥፋት አደጋ በተጋለጡበት ወቅት፣ በባሕር ላይ የሚደረጉ ጥናታዊ እንቅስቃሴዎች፣ እንደ ማዕድን ፍለጋ፣ በአሳ ማጥመድ እና በመርከብ ጉዞ ላይ ገደቦችን የሚያወጣ ስምምነት በኒውዮርክ በተፈረመ ማግስት እንደሆነ ታውቋል። ከአሥር ዓመታት በላይ ውይይት ከተደረገ በኋላ የተደረሰው ስምምነቱ፣ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2030 ዓ. ም.  30 በመቶው ለባሕር ውሃ የሚደረገውን ጥበቃ የሚመለከት ሲሆን፣ ዓላማውም የውሃ ውስጥ ተፈጥሮን ከጉዳት ለመጠበቅ እና እንደገና እንዲያገግም ለማድረግ ነው ተብሏል።

መተባበር ያስፈልጋል

በብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን በተፈረመው መልዕክት ውስጥ ሌሎች ሁለት መሠረታዊ ነጥቦች የተዘርዘሩ ሲሆን፣ ከአስተዳደር እስከ ግሉ ሴክተር፣ ከምርምር ዓለም እስከ ፖለቲካ እና ባሕል፣ ከሃይማኖት እና ከወጣቶች ድርጅቶች እስከ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ድረስ ያለውን የግንኙነት እውነታዎችን የሚመለከት እንደሆነ ታውቋል። ከነጥቦቹ መካከል አንዱ "በባሕር ውስጥ፣ በባሕር ዳርቻዎች እና በወንዞች ውስጥ የሚገኙ ስነ-ምህዳሮችን ከጉዳት ለመጠበቅ እና ወደነበሩበት ለመመለስ ተባብሮ መሥራት እንደሚያስፈልግ የተገለጸ ሲሆን፣ ሌላኛው እና ሁለተኛው ነጥብ፣ "ለውቅያኖስ ውሃ ከሚደርግ ጥበቃ መጠን እና ውስብስብነት ጋር የተያያዘውን ውጤታማ አስተዳደር እና ተቋማዊ ቅንጅት ማመቻቸት አስፈላጊነት እንደሆነ ታውቋል።

ጤናማ ውቅያኖስ ለወደፊት ትውልዶች

የሰው ልጅ በሙሉ በውቅያኖስ ውሃ ላይ እንደሚደገፍ ያመላከተው የቅዱስነታቸው መልዕክት፣ የውቅያኖስ ውሃ ለሰው ልጅ ከፈጣሪ የተሰጠው ስጦታ በመሆኑ፣ ፍትሃዊ እና ቀጣይነት ባለው መንገድ በመጠቀም በመልካም ሁኔታ ለወደፊት ትውልድ እንዲተላለፍ ማድረግን አስታውሷል። በመሆኑም መላው የሰው ልጅ ቤተሰብ፣ “ውዳሴ ላንተ  ይሁን” በሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን እንደተገለጸው፣ የልማት እና የሥነ-ምህዳር ዋነኛ ራዕይን እንዲቀበል መጠራቱን መልዕክቱ አስገንዝቧል። እንደ አለመታደል ሆኖ፣ የውቅያኖስ ውሃ ብክለት፣ የአሲድነት፣ ሕገ-ወጥ እና ከመጠን በላይ ዓሣ የማጥመድ አሳሳቢነት አሁንም መኖሩ፣ የባሕር ውስጥ ኢንዱስትሪ ልማት እና የስደተኞች አስጨናቂ የባሕር ላይ ጉዞ እና አሳዛኝ ክስተቶች ጎን ለጎን፣ በባሕር ላይ የሚፈጸመው ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ አስቸጋሪ የመርከብ ተጓዦች፣ አንዳንዴም ሕገወጥ የሥራ ሁኔታ እና በባሕር ላይ የሚታዩ ጂኦፖለቲካዊ ውጥረቶች መኖራቸውን የቅዱስነታቸው መልዕክት አስታውሷል።

ውሃ ሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት አስፈላጊ ነው

“የውቅያኖስ ውሃ አመላካች፣ ተያያዥነት ያለው እና ምንም ዓይነት የፖለቲካ እና የባሕል ድንበር የለውም" ያለው መልዕክቱ፣ “የውቅያኖስ ውሃ በማኅበረሰቦች እና በአገሮች መካከል ያለውን ግንኙነት እና ጥገኝነት የሚያጎላ፣ ምድራችንን የሚያቋርጥ ጅረት እንደሆነ በመግለጽ፣ የአንድ ቤተሰብ አባላት በመሆናችን፣ የማይጠፋውን ሰብዓዊ ክብርን ለመጋራት እና ለመንከባከብ በተጠራንበት የጋራ መኖሪያ ምድራችን ውስጥ እንኖራለን" በማለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በፓናማ ከተማ ከየካቲት 23-24/2015 ዓ. ም. ለተካሄደው ስምንተኛ ዙር የውቅያኖስ ውሃ ድህንነት ጉባኤ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።  

07 March 2023, 16:19