ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ ከፍተኛ የሳይንስ ጠበብት እና የባለሙያዎች ቡድንን በቫቲካን ተቀብለው ንግግር ሲያደርጉ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ ከፍተኛ የሳይንስ ጠበብት እና የባለሙያዎች ቡድንን በቫቲካን ተቀብለው ንግግር ሲያደርጉ   (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ ሰው ሠራሽ አዕምሮ በሥነ-ምግባር የተመራ አጠቃቀም እንዲኖረው አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ከፍተኛ የሳይንስ ጠበብት እና የባለሙያዎች ቡድንን መጋቢት 18/2015 ዓ. ም. በቫቲካን ተቀብለው ንግግር አድርገውላቸዋል። ቅዱስነታቸው ለቡድኑ አባላት ባደረጉት ንግግር፣ ባሁኑ ጊዜ የቴክኖሎጂ ውጤቶች እና ሰው ሠራሽ አዕምሮ ለሚሰጡት ጥቅሞችን አድናቆታቸውን ገልጸው፣ ሰው ሠራሽ አዕምሮ ከባድ ጥያቄዎችን እያስነሳ ስለሚገኝ በሥነ ምግባር እና ኃላፊነት በተሞላው መንገድ የሰውን ክብር ለማስጠበቅ እና የጋራ ጥቅምን ለማሳደግ መዋል እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የቴክኖሎጂ ውጤቶች እና ሰው ሠራሽ አዕምሮ ለጋራ ጥቅም መዋላቸውን በደስታ የተቀበሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ነገር ግን ሰው ሠራሽ አዕምሮን ከሥነ-ምግባር ውጭ ወይም ኃላፊነት በጎደለው መንገድ ከመጠቀም አስጠንቅቀዋል። ቅዱስነታቸው ይህን የተናገሩት፣ በቅድስት መንበር የትምህርት እና የባሕል ጉዳዮች ጳጳሳዊ ምክር ቤት ባዘጋጀው ከፍተኛ የሳይንስ ሊቃውንት እና የባለሙያዎች ዓመታዊ ስብሰባ የተካፈሉትን ሰኞ መጋቢት 18/2015 ዓ. ም. በቫቲካን ተቀብለው ንግግር ባደረጉበት ወቅት ነው።

ስብሰባው ከቴክኖሎጂው ዓለም የተውጣጡ ባለሙያዎችን፣ የሳይንስ ሊቃውንቶችን፣ መሐንዲሶችን፣ የንግድ ተቋማት መሪዎችን ፣ የሕግ ባለሙያዎችን እና ፈላስፋዎችን፣  እንዲሁም የቤተ ክርስቲያን ተወካዮችን፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለሥልጣናትን፣ የነገረ መለኮት ሊቃውንት እና የሥነ-ምግባር ባለሙያዎችን ያሳተፈ ሲሆን ዓላማውም ዲጂታል ቴክኖሎጂዎች በተለይም ሰው ሠራሽ አዕምሮ በማኅበራዊ እና ባሕላዊ ሕይወት ላይ የሚያሳድሩትን ተጽዕኖ በማጥናት ግንዛቤን የበለጠ ለማሳደግ እንደሆነ ታውቋል።  

ኃላፊነት ያለው የቴክኖሎጂ አጠቃቀም

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለዚህ ቀጣይነት ላለው የውይይት መድረክ ከፍተኛ ዋጋን እንደሚሰጡት ተናግረው፣ በተለይም የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን የተመለከተ ውይይትን የሚያካትት በመሆኑ፣ “ለሃይማኖታዊ እሴቶችም ክፍት ነው" ሲሉ ገልጸዋል።

"በአማኞች እና በማያምኑት መካከል በመሠረታዊ የሥነ-ምግባር፣ የሳይንስ እና የሥነ-ጥበብ ጥያቄዎች እና የሕይወት ትርጉም ፍለጋ ላይ የሚደረግ ውይይት ለሰላም እና ለሰው ልጅ ዕድገት ዋና መንገድ እንደሆነ እርግጠኛ ነኝ።" ብለዋል።

“ቴክኖሎጂ ለሰብዓዊ አገልግሎት በተለይም በሕክምና፣ በምህንድስና እና በመገናኛ ዘርፎች እጅግ ጠቃሚ ነው” ያሉት ር ዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የቴክኖሎጂ ውጤት በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ለሚሰጠው ተግባራዊ ጠቀሜታዎች አመስግነው፣ “የሰው ልጆች የፈጠራ ችሎታ እና በእግዚአብሔር የፍጥረት ተግባር ውስጥ በኃላፊነት ለመሳተፍ የተጠራበት ልዕልና ማሳያ አድርገን እናያቸዋለን” ብለዋል።

በሥነ-ምግባር መንገድ መተግበር

"ከዚህ አንፃር የሰው ሠራሽ አዕምሮ እና በመሣሪያዎች በመታገዝ የመማር ዕድገት ለሰው ልጅ የወደፊት ሕይወት በአዎንታዊ መልኩ አስተዋፅኦ እንደሚያደርግ እርግጠኛ ነኝ" ብለዋል። "በተመሳሳይም "ይህ እምቅ አቅም እውን የሚሆነው እነዚህን ቴክኖሎጂዎች በማዳበር በሥነ-ምግባር እና በኃላፊነት እንዲገለገሉባቸው የሚያደርግ የማያቋርጥ እና የማይለዋወጥ ቁርጠኝነት ሲኖር እንደሆነ እርግጠኛ ነኝ" በማለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስጠንቅቀዋል።

ቅዱስነታቸው በማከልም፣ "በቴክኖሎጂ እና ሰው ሠራሽ አዕምሮ መስኮች ዙሪያ የሚሠሩ በርካታ ሰዎች፣ ቴክኖሎጂ ሰውን ያማከለ፣ በሥነ-ምግባር ላይ የተመሠረተ እና ወደ መልካም አቅጣጫ የሚመራ መሆኑን ለማረጋገጥ እየሰሩ መሆናቸውን ማወቁ አበረታች ነው።" ብለዋል።

በልማት ሂደት አስፈላጊነት ላይ ለተፈጠረው መግባባት አድናቆታቸውን የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ቴክኖሎጂን ሥነ-ምግባር ባለው መንገድ መጠቀሙ ማካተትን፣ ግልጽነትን፣ ደኅንነትን፣ እኩልነትን፣ ግላዊነትን እና አስተማማኝነት ያላቸው እሴቶችን ለማክበር እንደሆነ አስረድተዋል። በተጨማሪም ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እነዚህን ቴክኖሎጂዎች አገልግሎት ለማሻሻል የሚያደርጉትን ጥረት በደስታ ተቀብለው፣ በዚህ መንገድ እውነተኛ ዕድገትን እንደሚያበረታቱ እና ለተሻለ ዓለም እና በአጠቃላይ ለላቀ የሕይወት ጥራት አስተዋፅዖን የሚያበረክቱ መሆኑንም አስረድተዋል።

የእያንዳንዱ ወንድ እና ሴት ተፈጥሮአዊ ክብር

በቴክኖሎጂ ዘርፎች የተሰማሩት ባለሙያዎች ሰብዓዊ ክብርን ለማስጠበቅ እስከረዱ ድረስ፣ በሁሉም የሰው ልጅ የሕይወት ደረጃ ላይ ያለውን አገላለጽ ከፍ ለማድረግ እስከረዱ ድረስ ከሥነ-ምግባራዊ ሁኔታ ጋር የሚጣጣሙ መሆናቸውን ገልጸው፣ የእያንዳንዱ ወንድ እና ሴት ተፈጥሮአዊ ክብር፣ በማደግ ላይ የሚገኙ ቴክኖሎጂዎች የሚገመገሙበት ዋና መስፈርት ለማድረግ ለሚጥሩት በሙሉ ብርታትን ተመኝተውላቸዋል።

"በአሁኑ ጊዜ መረጃዎች እንደሚያመላክቱት የዲጂታል ቴክኖሎጂዎች በዓለማችን ውስጥ የኑሮ አለመመጣጠንን መጨመራቸው አሳስቦኛል” በማለት በቅሬታ የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ "ሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ተቋሞቻችን የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች በምርቶቻቸው አማካይነት ለሚፈጥሩት ማኅበራዊ እና ባሕላዊ ተፅእኖ ተጠያቂ ማድረግ ይችላሉ? የቴክኖሎጂ ውጤቶች የኑሮ አለመመጣጠንን በመጨመር የሰውን እና የኅብረተሰብን የአብሮነት ስሜት ሊያዳክሙ እንደሚችሉ ስጋት አለ? ለጋራ እጣ ፈንታ ያለንን ስሜት ልናጣው እንችላለን? በማለት ጥይቀው፣ እውነተኛ ግባችን የሳይንስ እና የቴክኖሎጂ ፈጠራ ዕድገት በላቀ የሰው ልጅ እኩልነት እና በማኅበራዊ አንድነት እንዲታጀብ መሆን አለበት ብለዋል።

የሰው ክብር በአኃዝ መረጃ ሊለካ አይችልም

“ተፈጥሯዊ የሰው ልጅ ክብር ፅንሰ-ሃሳብ የአንድን ሰው መሠረታዊ እሴት በመረጃ ብቻ ሊለካው እንደማይችል እንገነዘባለን” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በማኅበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ ውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ፍርዶችን ወደ ቀመሮች ለመለወጥ በሚደረግ አካሄድ ላይ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናግረው፣ ግለሰብን በመቅረጽ እና የቀድሞ ባህሪዎችን በመግለጽ ላይ ብዙውን ጊዜ በድብቅ የሚሰበሰቡ መረጃዎች መኖራቸውን ቅዱስነታቸው ገልጸዋል።

"እንዲህ ያሉ መረጃዎች በኅብረተሰቡ ጭፍን ጥላቻ እና የቅድሚያ ግምቶች ሊበከሉ እንደሚችሉ አስጠንቅቀው፣ የአንድ ሰው ያለፈ ባህሪ፥ ለመለወጥ፣ ለማደግ እና ለኅብረተሰቡ አስተዋፅኦን ለማበርከት ዕድል እንዳለው መዘንጋት የለብንም” ያሉት ቅዱስነታቸው፣ "ቀመሮች የሰዎችን ክብር እንዲገድቡ ወይም እንዲከለክል ርህራሄን፣ ምህረትን፣ ይቅርታን እና ከሁሉም በላይ ሰዎች ሊለወጡ ይችላሉ የሚለውን ተስፋ እንዲያስወግዱ መፍቀድ አንችልም” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በቅድስት መንበር የትምህርት እና የባሕል ጉዳዮች ጳጳሳዊ ምክር ቤት ባዘጋጀው ከፍተኛ የሳይንስ ሊቃውንት እና የባለሙያዎች ዓመታዊ ስብሰባ ለተካፈሉት ያደረጉትን ንግግር ከመደምደማቸው በፊት በጸሎት የታገዘ መልካም ምኞታቸውን ገልጸው፣ የስብሰባው ተካፋዮች እርስ በርስ ለመደማመጥ እና በኅብረት ለማሰላሰል ላደረጉት ጥረት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

28 March 2023, 16:46