ፈልግ

የኤኳዶር እና የፔሩ ሕዝቦችን የጎዳው የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ የኤኳዶር እና የፔሩ ሕዝቦችን የጎዳው የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ   (ANSA)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ በመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ የተጎዳውን የኤኳዶር ሕዝብ በጸሎት አስታወሱ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በኃይለኛ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ጉዳት የደረሰበትን የኤኳዶር ሕዝብ በጸሎት አስታውሰዋል። እሁድ መጋቢት 10/2015 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለእኩለ ቀኑ የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ለተሰበሰቡት ምዕመናን ባቀረቡት ጥሪ፣ ምዕመናኑ ጦርነት ያሰቃየውን የዩክሬን ሕዝብ በጸሎት እንዲያስታውሱት አደራ ብለው፣ እሁድ ዕለት ተከብሮ የዋለውን የአባቶች ቀን በማስታወስ ለአባቶች መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በደቡባዊ ኤኳዶር እና በሰሜናዊ የፔሩ ግዛት ቅዳሜ መጋቢት 9/2015 ዓ. ም. ሌሊት ላይ በተከሰተው ኃይለኛ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ የተጎዱትን በጸሎት ማስታወሳቸውን ቅዱስነታቸው ገልጸዋል። በሪክተር መለኪያ መጠኑ 6.8 በሆነው የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ የሞቱት ሰዎች ቁጥር ቢያንስ 16፣ በርካቶችን በፍርስራሹ ውስጥ እንዳስቀራቸው እና በግምት 381 የሚሆኑ ሰዎችን ለመቁሰል አደጋ ዳርጓቸዋል።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ እሁድ መጋቢት 10/2015 ዓ. ም. ባቀረቡት የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ላይ እንደተናገሩት፣ ከኤኳዶር ሕዝብ ጋር በጸሎት እንደሚተባበሩ እና በአደጋው የሞቱትን እና የተጎዱትን በሙሉ በጸሎት እንደሚያስታውሷቸው አረጋግጠዋል።

የአደጋውን አስከፊነት ተዘዋውረው የተመለከቱት፣  የግንባታ ደረጃዎችን ያላሟሉ ሕንፃዎች መፍረሳቸውን እና ድሃው ማኅበረሰብ በብዛት የሚገኙባቸው አካባቢዎች ለአደጋው ይበልጥ መጋለጣቸውን ገልጸዋል። በፓስፊክ ውቅያኖስ ዳርቻ ላይ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ የኤኳዶር ሁለተኛ ሰፊ ከተማ ከሆነችው ከጓያኪል በስተደቡብ 80 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እንደ ነበር እና በርካታ ሰዎችም በፍርስራሹ ውስጥ ተቀብረው እንደሚገኙ የአገሪቱ የአደጋ መከላከያ እና ዝግጁነት ኤጀንሲ አስታውቋል።

በተለይ ኤኳዶር ለመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ የተጋለጠች መሆኗ ሲነገር፣ ከዚህ በፊትም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2016 ዓ. ም. ብዙ ሰዎች በማይኖሩበት የፓስፊክ ውቅያኖስ ዳርቻ በመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ከ600 በላይ ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል። ቅዳሜ መጋቢት 9/2015 ዓ. ም. ሌሊት ላይ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ፣ ከኤኳዶር ጋር በሚዋሰኑ የሰሜን ፔሩ ግዛቶችም ጉዳትን አስከትሏል። ከዚህ ጋር በተያያዘ የፔሩ ባለስልጣናትም አደጋው በተከሰተበት አካባቢ የአንድ ሰው ሕይወት መጥፋቱን ገልፀው፣ ቤቶች መውደማቸውን እና በጦር ሠፈር በሚገኙ አሮጌ ቤቶች መውደማቸውን አስታውቀዋል።

ለዩክሬን ሰላም የቀረበ ጸሎት

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ ከዚህ በፊት በመሯቸው የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት እና ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸው ወቅት በተደጋጋሚ እንዳሳሰቡት፣ መላው ምዕመናን እና በጎ ፈቃድ ያላቸው ሰዎች ጦርነት ያጎሳቆላት ዩክሬንን በጸሎት እንዲያስታውሷት አሳስበው፣ በማከልም “በጦርነት ወንጀሎች እየተሰቃየ ለሚገኝ የዩክሬን ሕዝብ መጸለይን አንርሳ" ብለዋል።

የአባቶች ቀን

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በንግግራቸው ማጠቃለያ ላይ፣ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ወደ ቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የመጡ ምዕመናን እና አገር ጎብኝዎች የያዟቸውን የተለያዩ አገራት ሰንደቅ ዓላማዎችን ተመልክተው፣ እሑድ መጋቢት 10/2015 ዓ. ም. የተከበረውን የአባቶች ቀን በማስታወስ፣ “ዛሬ ለአባቶች በሙሉ መልካም ምኞታችንን እንገልጻለን” ካሉ በኋላ፣ “አባቶች ከቅዱስ ዮሴፍ አብነት ድጋፍን እና መፅናናትን በማግኘት የአባትነት አደራቸውን በመልካም እንዲወጡ” በማለት መልካም ምኞታቸውን ገልጸውላቸዋል።

20 March 2023, 14:35