ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪርን ንግግር አድምጠዋል ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪርን ንግግር አድምጠዋል  (VATICAN MEDIA Divisione Foto)

ፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር፣ አገራቸው የሮሙን የሰላም ድርድር ለመቀጠል ዝግጁ መሆኗን ገለጹ

የደቡብ ሱዳን ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ሳልቫ ኪር፣ በደቡብ ሱዳን ሐዋርያዊ ጉብኝት ለማካሄድ ወደ ጁባ ለገቡት ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ባደረጉት የሰላምታ ንግግር፣ ቅዱስነታቸው በደቡብ ሱዳን የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት “ታሪካዊ ጉብኝት” ሲሉ ገልጸው፣ ቅዱስነታቸው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2019 ዓ. ም. ያዘጋጁትን የጸሎት እና የሱባኤ ሥነ ሥርዓት በማስታወስ፣ በቅዱስ ኤጂዲዮ ማኅበረሰብ ሸምጋይነት አንዳንድ ተቃዋሚ ቡድኖች ሳይፈርሙ የቀሩትን የሮሙን የሰላም ድርድር ለመቀጠል አገራቸው ዝግጁ መሆኗን ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር ከደቡብ ሱዳን ተቃዋሚዎች ጋር በሮም የሚደረገውን የሰላም ድርድር ለመቀጠል ያላቸውን ፍላጎት በይፋ መግለጻቸው፣ ውጥረት አስወግደው አገሪቱን ወደ መደበኛ ሁኔታ ለመመለስ ያላቸውን ምልክት ይገልጻል ተብሏል። ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ደቡብ ሱዳንን ለጎበኙት የመጀመሪያው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ባደረጉት የእንኳን ደህና መጡ ንግግር፣ "የእርስዎ በመካከላችን መገኘት ታሪካዊ ምዕራፍ ነው" ብለዋል።

በቅዱስ ኤጂዲዮ ማኅበረሰብ ሸምጋይነት የተጀመረው የሰላም ድርድር የተቋረጠው በአገሪቱ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ቡድኖች ባሳዩት "ቁርጠኝነት ማጣት" መሆኑን ገልጸው፣ በበኩላቸው ለዚህ ምላሽ እንደሚሰጡ እና በአገራችን ሁሉን አቀፍ ሰላም ለማምጣት በቅንነት ቁርጠኞች እንደሚሆኑ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

ወደ ሰላም የሚደረግ ጉዞ

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2019 ዓ. ም. ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ በቫቲካን ያዘጋጁትን የጸሎት እና የሱባኤ ሥነ-ሥርዓትን ያስታወሱት ፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር፣ ምክትላቸው ከሆኑት ከዶ/ር ሪክ ማሻር ጋር በጎርጎሮሳውያኑ 2018 ዓ. ም. የተፈረመውን የተሻሻለ የሰላም ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ አብረው መገኘታቸውን አስታውሰዋል።

የጋራ ውይይት እና ተግዳሮቶቹ

የደቡብ ሱዳን ፕሬዝደንቱ ከላይ በተጠቀሰው ስምምነት አፈፃፀም ላይ ሁሉም ሰው አለመርካቱን እንደሚገነዘቡት ተናግረው፣ “የስምምነቱ አካል የሆኑት ወገኖች የሚያጋጥሟቸውን ፈተናዎች ለመቅረፍ በውይይት መንፈስ አብረን እየሠራን እንገኛለን” ብለው፣ በደቡብ ሱዳን ሰላም እስኪሰፍን ድረስ መሥራታቸውን እንደሚቀጥሉ፣ አሳታፊ የፖለቲካ ሂደትን ለመከተል ካለው ጥልቅ ፍላጎት መሆኑንም አስታውሰዋል። የዜጎች ድምጽ የሚሰማበት ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ሂደት ለማካሄድ፣ ግልጽ እና ተአማኒ ምርጫን የሚፈቅዱ ተቋማትን ለመፍጠር የሚያስችል፣ የሽግግር ጊዜን በ24 ወራት የሚያራዝም መመሪያ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

የክርስቲያኖች አንድነት የሰላም ንግደት አስፈላጊነት

የፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር ተስፋ፣ ሰላምና ዕርቅን ፍለጋ የካንተርበሪ ሊቀ ጳጳስ ጀስቲን ዌልቢ እና የስኮትላንድ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላላ ጉባኤ ተወካይ የቄስ ኢያን ግሪንሺልድስ ወደ ደቡብ ሱዳን ያደረጉት ታሪካዊ ጉብኝት፣ በተለይም ሰላምን በማጠናከር ተግባር እና በሕዝባቸው መካከል ያለውን የእርቅ እና የይቅር ባይነት ፍላጎትን በማገናዘብ የቅርብ ጊዜ ታሪካቸውን በጥልቅ እንዲያስቡ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል።

04 February 2023, 16:53