ፈልግ

 ከቀኝ ወደ ግራ፥ ሊቀ ጳጳስ ጀስቲን ዌልቢ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር እና ቄስ ኢየን ግሪንሺልድስ ከቀኝ ወደ ግራ፥ ሊቀ ጳጳስ ጀስቲን ዌልቢ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር እና ቄስ ኢየን ግሪንሺልድስ   (VATICAN MEDIA Divisione Foto)

“በደቡብ ሱዳን የሰላም እና የዕርቅ ምላሽ ያለው በፖለቲከኞች እጅ ነው!”

በእንግሊዝ የካንተርበሪው ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጀስቲን ዌልቢ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2019 በቫቲካን ከደቡብ ሱዳን እና ተቃዋሚ ቡድኖች ጋር የተካሄደውን ስብሰባ በማስታወስ፣ በሰላም ሂደት ላይ መሻሻል ባለመታየቱ የተሰማቸውን ቅሬታ ገልጸዋል። የስኮትላንድ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላላ ጉባኤ መሪ ቄስ ግሪንሺልድስም በበኩላቸው፣ የፖለቲካ መሪዎች እምነታቸውን በተግባር በመግለጽ ተጋላጭ እና ከማኅበረሰቡ የተገለሉ ሰዎችን እንዲያገለግሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ቀጥለው የተናገሩት የካንተርበሪው ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጀስቲን፣ “ከአምስት ዓመት ገደማ በኋላም ወደ ደቡብ ሱዳን የመጣነው፣ ታርቃችሁ ሰላምን እንድታደርጉ ዛሬም በእግራችሁ ሥር ወድቀን ልንለምናችሁ፣ ልናዳምጣችሁ፣ ልናገለግላችሁ እና አብረናችሁ ልንጸልይ ነው” ብለዋል። የደቡብ ሱዳን ፖለቲከኞች እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2019 ዓ. ም. ያካሄዱትን ታሪካዊ ስብሰባ በማስታወስ፣ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር እና በምክትል ፕሬዚደንት ሪክ ማሻር ፊት ተንበርክከው ሰላምን መማጠናቸውን አስታውሰዋል።

ዌልቢ፥ "የበለጠ ጠብቀን ነበር!"

“መንፈስ ቅዱስ እንዲሠራ ቦታ ከተገኘ ብለን ጸለይን ነበር፤ በዚያ ስብሰባ ላይ ተስፋ መኖሩንም አይተን ነበር” ያሉት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጀስቲን፣ ሆኖም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ባዩት እና በሰሙት ነገር ማዘናቸውን ተናግረዋል።“ተጨማሪ ተስፋ አድርገን ጸለይን ነበር፣ የበለጠ ጠብቀን ነበር፣ እናንተም ቃል ገብታችሁልን ነበር” ያሉት ሊቀ ጳጳሱ፣ የሰላም ስምምነት የሚደረገው የተወሰኑ ክፍሎችን ብቻ በመምረጥ እንዳልሆነ ነገር ግን እያንዳንዱ ክፍል በእያንዳንዱ ሰው በኩል ሰላምን ተግባራዊ ማድረግ እንዳለበት እና ይህም ብዙ ወጪን እንደሚጠይቅ አስረድተዋል።

ሰላም በእግዚአብሔር ዕርዳታ ይመጣል

“የሰላም እና የዕርቅ ምላሽ ያለው በዚህ ዓይነት ጉብኝት ላይ ሳይሆን ነገር ግን በእጃችሁ ነው" ያሉት ያሉት ሊቀ ጳጳስ ጀስቲን ዌልቢ፣ "በእጃችሁ ላይ ያለውን ሰላም በእግዚአብሔር ዕርዳታ ትደርሱበታላችሁ" ብለው፣ ለነጻነቱ ሲል ረጅም ጊዜ ሲታገል እና ሲያሸንፍ የቆየው የደቡብ ሱዳን ሕዝብ ምኞቱ ሊሳካለት የሚችለው እና በእርግጠኝነት አሁንም ለሰላም እና ለእርቅ ለመታገል ድፍረቱ ያለው በፖለቲከኞች እጅ እንደሆነ በማስረዳት የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች “ሙስና ተወግዶ በደቡብ ሱዳን ሰላም እንፈልጋለን!” ማለታቸውን አስታውሰዋል።

እሴቶች እና እምነት ያላቸው መሪዎች ያስፈልጉናል

የስኮትላንድ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላላ ጉባኤ መሪ ቄስ ግሪንሺልድስም በበኩላቸው፣ ደቡብ ሱዳን እሴቶች እና እምነት ያሏቸው፣ ለሰዎች የኑሮ ሁኔታ የሚጨነቁ፣ በተጋላጭ እና የተገለሉ ሰዎች መካከል የሚሠሩ እና እምነታቸውን በተግባር የሚያሳዩ የፖለቲካ መሪዎች ያስፈልጓታል” ብለዋል።

መጭውን ጊዜ ለማሳመር መሥራት ይገባል

የፖለቲካ፣ የሲቪል እና የዓለም አቀፍ መሪዎች፣ ለሁሉም ሕዝቦች ሙሉ ሕይወት የሚገኝበትን የእግዚአብሔር ሁለንተናዊ ተስፋን በኅብረት መፈለግ እንደሚገባ፣ ደቡብ ሱዳን ገና ወጣት እና ብሩህ ተስፋ ያለባት ሀገር፣ ወደ አንድነት ጎዳና ለመሥራት ዝግጁ የሆኑ ሰዎች ያሏት አገር መሆኗን አክለው ተናግረዋል።

04 February 2023, 18:19