ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች በኮንጎ እና በአፍሪካ ተስፋን እንደሚዘሩ ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ በማድረግ ላይ በሚገኙት ሐዋርያዊ ጉብኝት ሁለተኛ ቀን፣ በኪንሻሳ ከተለያዩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ተወካዮች ጋር በመገናኘት፣ ድርጅቶቹ ለአደጋ ተጋላጭ ለሆኑት የአገሪቱ ዜጎች ላደረጉት መልካም ሥራ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፓብሊክ መዲና ኪንሻሳ በሚገኘው የቅድስት መንበር እንደራሴ ጽ/ቤት ረቡዕ ጥር 24/2015 ዓ. ም. ለተወሰኑ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ተወካዮች ባደረጉት ንግግር፣ ድርጅቶቹ በእርጋታ ፍሬውን እየሰጥ እንዳለ ደን፣ በዓመፅና በፍትሕ መጓደል መካከል የሚያበረክቱትን አገልግሎት አወድሰዋል።

ስድስቱ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች

በቅድስት መንበር እንደራሴ ጽ/ቤት ውስጥ የተገኙት የስድስት በጎ አድራጎት ድርጅቶች ሠራተኞች እና ዕርዳታ ተጠቃሚዎች ልምዳቸውን ገልጸው፣ በጤና አጠባበቅ፣ በትምህርት እና በሰብዓዊ ልማት ዘርፍ ለድሆች እና ከማኅበረሰቡ ለተገለሉት ወገኖች ያከናወኗቸውን ተግባራት በዝርዝር አቅርበዋል። ተግባራቱ በተለያዩ የአካል ጉዳቶች፣ በሥጋ ደዌ በሽታ እና በሌሎች በሽታዎች የተጎዱን እንደሚያጠቃልል ተገልጿል። ከበጎ አድራጎት ድርጅቶች መካከል በሽታን በታላቅ እና የላቀ ዘዴ የሚያስወግድ “DREAM” የተሰኘ የቅዱስ ኤጂዲዮ ማኅበረሰብ ማዕከል፣ ፋስታ ማኅበር፣ ዓላማው ከማኅበረሰቡ የተገለሉትን በሁለገብ ዘርፍ ከማኅበረሰቡ ጋር ማካተት የሆነው አርጀንቲናዊ ግብረሰናይ ድርጅት፣ “ቴለማ” የተሰኘ የአካል ጉዳተኞች የኑሮ ሁኔታን ለማሻሻል የሚሠራ የአገር ውስጥ ማህበር እና በኪኪዊት ክፍለ ሀገር የሚገኝ የማቫንዳ እመቤታችን ትራፕስት መነኮሳትም ተገኝተዋል።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች የሚረዷቸውን ሰዎች አገኙ
ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች የሚረዷቸውን ሰዎች አገኙ

ድሆችን ከነስማቸው እና መልካቸው ጋር ማቀፍ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን ለሥራቸው አመስግነው፣ ያቀረቧቸው ምስክርነቶች ማኅበራዊ ችግሮችን ወይም አሃዛዊ መረጃዎችን የሚያቀርብ ብቻ ሳይሆን ነገር ግን በይበልጥ ስለ ድሆች በፍቅር መናገር እንደ ነበር ገልጸው፣ “እንደማናችን የግል ስም እና መልክ ላላቸው ክርስቲያኖች ጀርባቸውን መመለስ አይቻልም” ብለዋል። “ዛሬ ብዙዎች ድሆችን ከፊታቸው ሲያስወግዷቸው እናንተ ግን ታቅፏችኋላችሁ፤ ዓለም ሲበዘብዟቸው እናንተ ግን ታበረታታላችሁ” ብለው፣ ብርታትን መስጠት እና ብዝበዛን ያነጻጸሩት ቅዱስነታቸው፣ ጭፍጨፋ የሚካሄድበት ደን እያደገ እና እየሰፋ እንደሚመጣ” ገልጸው፣ የበጎ አድራጎት ድርጅቶቹ በኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ እና በመላው የአፍሪካ አህጉር ዕድገትን እና ተስፋን ለማስፋፋት እየሠሩ ያለውን ሥራ ለሌሎች በሚገባ ማሳወቅ እንደሚፈልጉ ገልጸው፣ “ወደ ኮንጎ የመጣሁት ድምጽ ለሌላቸው ድምጽ ለመሆን ካለኝ ፍላጎት ነው” ብለዋል።

ድህነት በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸም በደል ነው

“ማኅበራዊ መገናኛዎች በኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ እና በመላው የአፍሪካ አህጉር ስለሚገኝ “ታላቅ ተሰጥኦዎች” ብዙ ቦታ አይሰጡም” ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ይህን እውነታ እና የብዙ ወንዶች እና ሴቶች ስቃይ፣ በሀገሪቱ ውስጥ በሚደርሱ ጥቃቶች፣ እንግልቶች፣ አድሎዎች እና መገለል ድምፅ ማሰማት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል። “ድህነት እና ማግለል በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸሙ፣ ክብራቸውንም የሚነጥቁ በደሎች እንደሆኑ  በድጋሚ ተናግረው፣ “የሰው ልጅ ስብዕናን መመለስ የምንችለው ክብሩን ስናስጠብቅ ብቻ ነው” በማለት አስረድተዋል። አክለውም፣ “በኮንጎ ዲሞክራሲያዊት ሪፐብሊክም የእያንዳንዱ ኅብረተሰብ መሠረት እና የወደፊት ዕጣ ፈንታን የሚወክሉ ሕጻናት እና አዛውንቶች መጣላቸው ወይም መረሳታቸው አሳፋሪ ነው” በማለት ማዘናቸውን ገልፀው፣ የወደ  ፊት ትውስታ በሌለበት ማኅበረሰብ ውስጥ እውነተኛ የሰው ልጅ ዕድገት ወይም ልማት ማምጣት አይችልም" ብለዋል።

መልካምነት ይስፋፋል!

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች ባደረጉት ንግግር፣ ችግር ቢያጋጥማቸውም ታሪካቸው እንደሚያረጋግጠው ሁሉ፣ መልካምነት ሳይደናቀፍ ከጊዜ ወደ ጊዜ እንደሚሰፋ፣ “በነጻ የተቀበልነውን ለሌሎች በነጻ እንድንሰጥ ይገፋፋናል” በማለት ለተሰብሳቢዎቹ አስረድተው፣ “በተለይ ወጣቶች ይህንን ማየት ይኖርባቸውል" ሲሉ አፅንዖት ሰጥቷል። ወጣቶች ግድየለሽነትን የሚያሸንፉ፣ የጦር መሣሪያን የማይዙ እና ገንዘብን ያላግባብ የማይጠቀሙ እጆች ማየት እንዳለባቸው፣ “መሬት ላይ ወድቀው የቀሩትን ከወደቁበት አንስተው ወደ ክብራቸው የሚመልሱ የእግዚአብሔርን ልጆች ማየት አለባቸው” ብለዋል።  አክለውም፣ "እውነተኛ ልግስና ከእግዚአብሔር ጋር በማስተባበር፣ እርሱ በሚወዳቸው ሰዎች አማካኝነት ያልተጠበቁ ድንቅ ነገሮች እንድናይ ያስችለናል” ብለዋል።

ክርስቲያኖች የበጎነት ምስክርነት ማጥላላት የለባቸውም

የጤና አገልግሎትን ማዳረስ፣ የትምህርት ዕድልን ማስፋፋት እና ተጋላጭ የሆኑትን የመንከባከብ ሃላፊነት በዋናነት በመንግሥት ላይ ቢሆንም፣ "በኢየሱስ ክርስቶስ የሚያምኑት በሙሉ የበጎነት ምስክርነትን ፈጽሞ ማጥላላት እንደሌለባቸው፣ ያላቸውን አውጥተው ከሌላቸው ጋር መካፈል አለባቸው" ብለው፣ ድህነት የሚመጣው በንብረት ማጣት እና ዕድሎችን በመነፈግ ሳይሆን እኩል የሃብት ክፍፍል ባለመኖሩ ነው በማለት ገልጸዋል። “ይህም በጎ አድራጎት ሳይሆን እምነት ነው” ሲሉ አጽንዖት ሰጥተው፣ ቅዱሳት መጻሕፍትም “እምነት ያለ ሥራ የሞተ ነው” እንደሚሉ አስታውሰዋል። የክርስቲያን በጎ አድራጎት ድርጅቶች፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ለድሆች ያለውን ፍቅር ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በመመስከር፣ የካቶሊክ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ፍሬያማ ለመሆን የሚከተሏቸው ሦስት መስፈርቶች መኖራቸውን፣ የመጀመሪያው፥ ታማኝ በመሆን አብነትን ማሳየት፣ በፋይናንስ አስተዳደር ግልጽነት እንዲኖር እና ለሥራው ብቁ ሆኖ መገኘት የሚል መሆኑን ገልጸዋል።

ድሆችን በራስ እንዲተማመኑ ማድረግ

ሁለተኛው መስፈርት፣ የድሆችን የዛሬን ፍላጎት ማሟላት ብቻ ሳይሆን፣ ቤተ ክርስቲያን በኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ እና በብዙ የዓለም ክፍሎች እንደምታደርገው፣ ረጅም ጊዜን በማቀድ ወደፊት  ራሳቸውን እንዲችሉ የሚያግዙ የልማት ውጥኖችን በማስተዋወቅ ረገድ “አርቆ አስተዋይነት” የሚለው እንደሆነ ገልጸው፣ ሁልጊዜም ቢሆን እጥረት የሚታይባቸውን ዕርዳታዎችን ከማከፋፈል ይልቅ እውቀት እና ልማት ራስ ገዝ እና ቀጣይነት ያለው እንዲሆን የሚረዱ መሣሪያዎችን ማስተላለፍ የተሻለ እንደሚሆን አስረድተዋል።

ድሆችን ለመርዳት መተባበር

በመጨረሻም፣ ለክርስቲያናዊ በጎ አድራጎት ድርጅት ፍሬያማ እና ውጤታማ እንዲሆን የሚያግዝ ሦስተኛው መስፈርት፣ የካቶሊክ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ተባብረው ከክርስቲያን ማኅበረሰቦች እና ሌሎች ሃይማኖታዊ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር ድሆችን ለመርዳት መተባበር እንደሆነ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ገልጸው፣ በንግግራቸው ማጠቃለያ፣ በኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ውስጥ ለሚገኙት የካቶሊክ በጎ አድራጎት ድርጅቶች በሙሉ ቡራኬያቸውን በመላክ፣ ትልቅ የቤተ ክርስቲያን ሃብት መሆናቸውን ገልጸው፣ ለውድ ሥራቸው በድጋሚ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።

02 February 2023, 16:24