ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ የጦር መሣሪያ ከትክሻችሁ ላይ አውርዱ፣ ምሕረትን ተቀበሉ ማለታቸው ተገለጸ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ ወደ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉዞ በሁለተኛው ቀን ከአንድ ሚሊዮን ለሚበልጡ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን በኪንሻሳ በሚገኘው “ንዶሎ” አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ ላይ በጊዜያዊነት በተሰራው ስፍራ ላይ ሥርዓተ ቅዳሴ ማድረጋቸው የተገለጸ ሲሆን ቅዱስነታቸው በወቅቱ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት እንደገለጹት በአገሪቷ የሚታዩ ግጭቶች እንዲያበቁ ጦረኞች የጦር መሳሪያዎችን ከትክሻቸው ላይ እንዲያወርዱ እና ምሕረትን እንዲቀበሉ፣ የቅዱስ ወንጌል እና የሰላም ሰባኪዎች እንዲሆኑ አሳስበዋል

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

የጦር መሣሪያን ከትክሻችሁ ላይ አውርዱ፤ ምሕረትን ተቀበሉ፣ እናም የሰላም ሚስዮናውያን ሁኑ በማለት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በዲሞክራቲክ ሪፖብሊክ ኮንጎ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው በሁለተኛው ቀን ረቡዕ እለት በኪንሻሳ ርዕሰ መዲና ለሚገኙት ለአገሪቱ ምእመናን መስዋዕተ ቅዳሴ ባሳረጉት ወቅት ባደረጉት ስብከት ይህን ማበረታቻ ሰጥተዋል።

በ"ንዶሎ" አየር ማረፊያ ለተሰበሰቡ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ንግግር ያደረጉት የቅዱስ አባታችን ቃለ ምእዳን በኮንጎ እና በኮንጎ ሕዝብ መካከል በመሆናቸው የተሰማቸውን ደስታ በመግለጽ ጀመሩ።

"ኢሴንጎ (በኮንጎ ቋንቋ ደስታ ማለት ነው) ደስታ፡ እናንተን ማየት እና መገናኘት ለእኔ ትልቅ ደስታ ነው" በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው "ይህን ጊዜ በጣም በጉጉት ጠብቄአለሁ:: እዚህ በመሆኔ አመሰግናለሁ!" በማለት ተግረዋል።

ቅዱስ አባታችን ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ በፋሲካ ምሽት "ሰላም ለእናንተ ይሁን!" በማለት የተናገራቸውን ቃላት የሚጠቅሰውን የቅዱስ ወንጌል ክፍል አስታውሰዋል። እነዚህ ቃላት ያለፈውን ትተው እንደገና እንዲጀምሩ ለሐዋርያቱ ያስቻላቸው “ስጦታ” መሆናቸውን ጳጳሱ አክለው ገልጸዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በቦታው የተገኙት ምዕመናን በኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ቦታ እንዲቀመጡ የጋበዙ ሲሆን "በዚያን ቀን በመስቀሉ ላይ ባዩት ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ተሠቃዩ፣ ኢየሱስን ሸሽተው ጥለው በመውጣታቸው ቁስለኛ ሆነው፣ ሕይወቱ ያለፈበት መንገድ ያሳዘናቸውና ሕይወታቸውም በተመሳሳይ መንገድ ይጠፋል ብለው ፈሩ” ሲሉ አክለው የገለጹ ሲህን "የበደለኛ ስሜት፣ ብስጭት፣ ሐዘንና ፍርሃት ተሰምቷቸው ነበር… ነገር ግን፣ የደቀ መዛሙርቱ ልብ እንደ ደነገጠ ስላወቀ ኢየሱስ መጣና ሰላምን ሰበከላቸው" በማለት ተናግረዋል።

ጳጳሱ እንዳሉት ከሆነ ደቀ መዛሙርቱ በሞት እንደተከበቡ እንደተሰማቸው ኢየሱስ ስላወቀ የሕይወትን ተስፋ እንደ ገለጸላቸው የተናገሩ ሲሆን ሁል ጊዜም ቢሆን ተስፋ መቁረጥ አይኖርብንም ብለዋል።

እግዚአብሔር ከ"አለት" ያነሳናል

የኢየሱስ ሰላም፣ በድንገት እና በሚያስደንቅ ሁኔታ፣ “የሰላም ጭላንጭል እንኳን ሳይኖር ሁሉም ነገር ያለቀላቸው በሚመስልበት ቅጽበት” መምጣቱን ተናግሯል።

“እግዚአብሔር የሚያደርገው ይህንኑ ነው፤ ያስደንቀናል። በምንወድቅበት ጊዜ እጁን ዘርጎቶ ያድነናል። መሬት ላይ ስንወድቅ  እሱ ያነሳናል” በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ከኢየሱስ ጋር ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ እንደ ተናገሩት ከሆነ "ክፉ መንፈስ አያሸንፍም ክፉ መንፈስ ፈጽሞ የመጨረሻው ቃል የለውም" ያሉ ሲሆን የኢየሱስ የሆኑት ሁሉ “ለሐዘን ፈጽሞ መሸነፍ” ወይም “ተስፋ መቁረጥ” የለባቸውም፣ ምንም እንኳን ያ ድባብ በዙሪያችን ቢነግስም ለኛ እንዲህ መሆን የለበትም ብሏል።

አክሎም “በአመፅና በጦርነት ተስፋ በቆረጠ ዓለም ውስጥ ክርስቲያኖች እንደ ኢየሱስ መሆን አለባቸው” ብሏል። "በጉዳዩ ላይ አጥብቆ የሚጠይቅ ያህል፣ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን አንድ ጊዜ በድጋሚ ነገራቸው፡- ሰላም ለእናንተ ይሁን!" ማለቱን በማስታወስ ስብከታችውን የቀጠሉት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የተጠራነው የራሳችንን "ይህን ተመስጧዊ እና ትንቢታዊ የሰላም መልእክት" አዘጋጅተን በዓለም ፊት እንድናውጅ ነው ብለዋል።

ይቅርታ ፣ ማህበረሰብ ፣ ተልዕኮ

ቅዱስ አባታችን በመቀጠል የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ምእመናን የኢየሱስን ሰላም እንዴት መጠበቅ እና ማዳበር እንደሚችሉ ራሳቸውን እንዲጠይቁ አበረታቷቸዋል፤ ከእነዚህም መካከል ሦስቱን “የሰላም ምንጮች” ይቅርታ፣ ማኅበረሰብ እና ተልዕኮን ማጉላት እንደ ሆኑ ተናግረዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱ ይቅርታን በተመለከተ ኢየሱስን የካዱት እና የሸሹት ሰዎች ሐዘንና እፍረት እንዴት እንደተጋፈጠ፣ ቁስሉን አሳይቶ የምሕረት ምንጭን እንደከፈተ አስታውሰዋል።

እሱ “ቃላቶችን አያበዛም” ነገር ግን የቆሰለውን ልቡን በሰፊው ይከፍታል ብለዋል ጳጳሱ።

“ወንድሞች፣ እህቶች፣ በደለኛነት እና ሀዘን ሲያሸነፉን፣ ነገሮች ጥሩ ካልሆኑ፣ የት ማየት እንዳለብን እናውቃለን፣ ወደ ኢየሱስ ቁስል፣ ማለቂያ በሌለው፣ በቆሰለው ፍቅሩ ይቅር ሊለን ዝግጁ የሆነውን የኢየሱስን ቁስል" መመልከት ይኖርብናል ብለዋል።

ታላቅ 'የልብ ምህረት'

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ለአገሪቱ ምእመናን ባደረጉት ስብከት እንደገለጹት ከሆነ ኢየሱስ "የአገራችሁን፣ የወገኖቻችሁን፣ የምድራችሁን ቁስል ያውቃል!" ያሉ ሲሆን "እነሱ የሚያሙ ቁስሎች ናቸው፣ ያለማቋረጥ በጥላቻ እና በዓመፅ የተለከፉ፣ የፍትህ መድኅኒት እና የተስፋ ጭላንጭል መቼም የሚደርሱ አይመስሉም። ወንድሜ፣ እህቴ፣ ኢየሱስ ካንቺ ጋር ተሠቃይቷል፣ የተሸከማችሁን ቁስል አይቶ ሊያጽናናችህ እና ሊፈውሳችሁ ይፈልጋል" ማለታቸው ተገልጿል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱ  አክለውም በአንድነት "ኢየሱስ ሁል ጊዜ ይቅርታ እንዲደረግልን እና እንደገና እንድንጀምር እድል እንደሚሰጠን እናምናለን ነገር ግን ራሳችንን፣ ሌሎችንና ታሪክን ይቅር እንድንል የሚያስችል ጥንካሬም እንደሚሰጠን እናምናለን!" ያሉ ሲሆን "ክርስቶስ የሚፈልገው ይህንን ነው" ማለታቸው ተገልጿል።

"በይቅርታው ሊቀባን ይፈልጋል፣ ሰላማችንን እና በተራው ሌሎችን ይቅር እንድንል ድፍረትን፣ ለሌሎች ታላቅ የልብ ምህረትን ለመስጠት ድፍረትን ሊሰጠን ይፈልጋል። ልባችንን ከቁጣ እና ጸጸት ማፅዳት ምንኛ ጥሩ ነው? ሲሉ ጥያቄ ማንሳታቸው የተገለጸ ሲሆን የቂም እና የጥላቻ ምልክቶች ሁሉ!" ማስወገድ ተገቢ ነው ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ዛሬ "የኢየሱስን ይቅርታ ለመቀበል እና ለመለማመድ የጸጋ ጊዜ እንዲሆንላችሁ ጸልዩ!" በማለት አክለው ተናግረዋል።

'የጦር መሳሪያዎቻችሁን አውርዱ፣ ምሕረትን አንሱ'

ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በልባቸው ውስጥ ከባድ ሸክም የያዙ ነፃ እንዲወጡ ምኞታቸውን የገለጹ ሲሆን "እናም በዚህች ሀገር ለምትኖሩ ራሳችሁን ክርስቲያን ለምትሉ ሁላችሁም መልካም ጊዜ ይሁንላችሁ" ያሉ ሲሆን "ጌታ እየተናገራችሁ ነው፡- የጦር መሣሪያዎችን መሬት ላይ አኑሩ፣ ምህረትን ተቀበሉ" ማለታቸው ተገልጿል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሱ በመቀጠል በዲሞክራቲክ ሪፖብሊክ ኮንጎ የቆሰሉት እና የተጨቆኑ ሰዎች ሁሉ ጌታ ቁስላቸውን እንዲሽር ጸሎታቸው መሆኑን ተናግረዋል።

"መስቀሉን ከአንገታችሁ እና ከኪሳችሁ ለማውጣት አትፍሩ፣ በእጆቻችሁ መካከል ወስዳችሁ ወደ ልባችሁ  አስጠጉት፣ ቁስላችሁን ከኢየሱስ ቁስል ጋር ለመካፈል አትፍሩ። ከዚያም ወደ ቤታችሁ ስትመለሱ መስቀሉን ከግድግዳው ላይ ውሰዱና እቅፍ አድርጉት” ማለታቸው ተገልጿል።

"ልባችሁን እንዲፈውስ ለክርስቶስ እድል ስጡ፣ ያለፈውን ጊዜን ከፍርሃቶችህ እና ከችግር ሁሉ ጋር ለእሱ አስረክቡ" ብለዋል ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ።

ጌታ መንገዱን ያሳየናል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በመቀጠል ወደ ሁለተኛው የሰላም ምንጭ ወደ ሆነው ማኅበረሰብ ትኩረታቸውን በማድረግ ስብከታቸውን ቀጠሉ።

"ከሙታን የተነሣው ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ለአንዱ ብቻ አይደለም የሚናገረው፤ ለእነርሱ በቡድን ሆኖ ይገለጣል" ብሏል። "በዚህም ለመጀመርያው የክርስቲያን ማህበረሰብ ሰላምን ይሰጣል። ያለወንድማማችነት ሰላም እንደሌለ ሁሉ ያለ ማህበረሰብ ክርስትና የለም" ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በህብረተሰቡ ውስጥ እና በቤተክርስቲያን ውስጥ እንኳን" ስልጣንን፤ ስራን፣ የራሳችንን ምኞት የመፈለግ ዝንባሌ አሉታዊ ገጽታ ስላለው መጠንቀቅ ይኖርብናል በማለት አስጠንቅቀዋል።

"በእግዚአብሔር መንገድ ሳይሆን በራሳችን መንገድ እንሄዳለን፣ እናም እንደ ደቀ መዛሙርት እንሆናለን፡ በተዘጋ በር ጀርባ፣ ያለ ተስፋ፣ በፍርሃትና በብስጭት ተሞልተን እንጓዛለን" ብሏል። "ይህ ቢሆንም ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይግባውና ይህን የሚከፋፍለንን ግላዊ ዝንባሌ አልፈን አንድነትን ማግኘት እንችላለን" ያሉት ቅዱስነታቸው ቀላል ቢሆንም የማህበረሰቡን ስሜት በሚሸረሽረው ዓለማዊነት እንዳንፈተን "ጌታ መንገዱን ያሳየናል" ብሏል።

"በዓለማችን ላይ የሰላም ሕሊና"

ሦስተኛው የሰላም ምንጭ፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ያቀረቡት 'ተልዕኮ' የሚለው ነው።

“የተጠራነው የሰላም ሚስዮናውያን እንድንሆን ነው” ያሉት ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ይህ ሰላም ያስገኝልናል ብለዋል።

"ለሁሉም በልባችን ውስጥ ቦታ መፈለግ አለብን፣ የብሔር፣ የክልል፣ የማህበራዊ እና የሃይማኖት ልዩነቶች ሁለተኛ ደረጃ እንጂ እንቅፋት እንዳልሆኑ ማመን፣ ሌሎች ወንድሞቻችንና እህቶቻችን፣ የአንድ ሰብአዊ ማህበረሰብ አባላት መሆናቸውን ማመን እና ሰላሙ ወደ መጣበት እንዲመጣ ማድረግ አለብን። ዓለም በኢየሱስ የታሰበው ለሁሉም ነው ሲሉ አክለው ገልጸዋል።

“እኛ ክርስቲያኖች ከሁሉም ጋር እንድንተባበር፣ የአመፅን አዙሪት እንድንሰብር፣ የጥላቻ ሽንገላን እንድናፈርስ የተጠራን መሆናችንን ማመን አለብን። አዎን፣ በክርስቶስ የተላኩ ክርስቲያኖች በዓለማችን የሰላም ሕሊና እንዲሆኑ ተጠርተዋል ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ይህ ትብብር ወሳኝ ሕሊናዎችን ብቻ ሳይሆን "በዋነኛነት የፍቅር ምስክሮች" ያስፈልገዋል ብለዋል።

"ሰላም ለእናንተ ይሁን" ኢየሱስ ዛሬ በዚህ ታላቅ ሀገር ውስጥ ላሉ ቤተሰብ፣ ማህበረሰብ፣ ጎሳ፣ ሰፈር እና ከተማ ሁሉ ይሁን በማለት ተናግሯል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዲሞክራቲክ ሪፖብሊክ ኮንጎ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ የጌታችንን ቃል በልባችን ውስጥ በጸጥታ እንድናሰላስል ከጋበዙን በኋላ ስብከታቸውን በጸሎት አጠናቅቀዋል።

Photogallery

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በኮንጎ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት
01 February 2023, 20:10