ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ ምዕመናን በጸሎት እንዲያግዟቸው ጠይቀዋል ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ ምዕመናን በጸሎት እንዲያግዟቸው ጠይቀዋል  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ በአፍሪካ ለሚያካሂዱት ሐዋርያዊ ጉብኝት የጸሎት ድጋፍን ጠይቀዋል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ከጥር 23 እስከ 28/2015 ዓ. ም. ድረስ በኮንጎ ዴሞክራሲዊት ሪፓብሊክ እና በደቡብ ሱዳን የሚያካሂዱትን 40ኛ ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝት፣ መላው ምዕመናን በጸሎት እንዲያግዟቸው ጠይቀው፣ እነዚህ ሁለቱ የአፍሪካ አገራት በረጅም የእርስ በእርስ አመጽ የተሰቃዩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይህን የሰላም ንግደት የሚጀምሩት ማክሰኞ ጥር 23/2015  ዓ. ም. ሲሆን፣ የመጀመሪያ መዳረሻቸው ኮንጎ ዴሞክራሲዊት ሪፓብሊክ እና ቀጥሎም ወደ ደቡብ ሱዳን እንደሚያመሩ ታውቋል። ቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ከመጀመራቸው በፊት፣ እሑድ ጥር 21/2015 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን ጋር የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ካቀረቡ በኋላ ለሁለቱ የአፍሪካ አገራት መልዕክት አስተላልፈዋል። በዚህ መልዕክታቸው ከሁለቱም አገራት የመንግሥት ባለስልጣናት እና ብጹዓን ጳጳሳት በኩል ለተደረገላቸው ግብዣ እና ዝግጅት ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።

ቅዱስነታቸው በተጨማሪም፣ ለሚጠብቋቸው ለሁለቱም አገራት ተወዳጅ ሕዝቦች እና ምዕመናንም ከልብ የመነጨ ሰላምታቸውን አቅርበው፣ አገራቱ ለረጅም ጊዜ በግጭቶች መሰቃየታቸውን አስታውሰዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ በተለይ ምሥራቃዊ የአገሪቱ አካባቢዎች በግጭቶች እና በብዝበዛ እንደሚሰቃዩ ተናግረው፣ “ደቡብ ሱዳን ለዓመታት በዘለቀው ጦርነት በርካታ ሰዎች ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ እና በችግር እንዲወድቁ ያደረገው የማያቋርጥ ብጥብጥ እንዲያቆም ትናፍቃለች” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ ኮንጎ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት አርማ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ ኮንጎ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት አርማ

የክርስቲያኖች አንድነት የሰላም ንግደት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትብ ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው፣ ከካንተርበሪው የአንግሊካዊ ሊቀ ጳጳስ ጀስቲን ዌልቢ እና ከቄስ ዶ/ር ያን ግሪንሺልድስ ጋር በመሆን በደቡብ ሱዳን ሐዋርያዊ ጉብኝት እንደሚያካሂዱ አስታውሰው፣ ከሁለቱ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ጋር በወንድማማችነት በጋራ የሰላም ንግደት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ምዕምናን በሙሉ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን በጸሎት እንዲደግፉት አደራ በማለት መልዕክታቸውን አጠናቅቀዋል።

የጉብኝታቸው አጭር መግለጫ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በአርባኛቸው ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት የመጀመሪያ መዳረሻ አገር በሆነች ኮንጎ ዲሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ከማክሰኞ ጥር 23-26/2015 ዓ. ም. ድረስ እንደሚቆዩ የሐዋርያዊ ጉብኝታቸው መርሃ ግብር አመልክቷል። በዋና ከተማ ኪንሻሳ በሚያደርጉት ቆይታ ከመንግሥት ባለስልጣናት፣ ከምሥራቁ የአገሪቱ ክፍል ከመጡ የግጭት ሰለባዎች እና ከቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ጋር እንደሚገናኙ ይጠበቃል።

ከዚያም ቀጥለው ዓርብ ጥር 26/2015 ዓ. ም. ወደ ደቡብ ሱዳን በመጓዝ በአገሪቱ እስከ ጥር 28/2015 ዓ. ም. ድረስ በሚያደርጉት ቆይታ በግጭት በቆሰለው የደቡብ ሱዳን ሕዝቦች መካከል ዕርቅን ለማውረድ ጥረታቸውን እንደሚቀጥሉ ታውቋል። ቅዱስነታቸው በዋና ከተማዋ ጁባ በሚያደርጉት ቆይታ፣ ከልዩ ልዩ የቤተ ክርስቲያን ተወካዮች ጋር፣ ሕዝባዊ ማኅበራት ተወካዮች እና ከተለያዩ ተፈናቃይ ወገኖች ጋር እንደሚወያዩ ታውቋል። እሑድ ጥር 28/2015 ዓ. ም. ከደቡብ ሱዳን ምእመናን ጋር የመስዋዕተ ቅዳሴ ካቀረቡ በኋላ ወደ ሮም እንደሚመለሱ የሐዋርያዊ ጉብኝታቸው መርሃ ጉብኝታቸው ያስረዳል።     

30 January 2023, 16:44