ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በስፔን ሳላማንካ የሚገኘውን የአውሮፓ ዓለም አቀፍ ጥናት ኢንስቲትዩት አባላትን በቫቲካን ባገኙበት ወቅት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በስፔን ሳላማንካ የሚገኘውን የአውሮፓ ዓለም አቀፍ ጥናት ኢንስቲትዩት አባላትን በቫቲካን ባገኙበት ወቅት  (Vatican Media)

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ለሰላም በሚደረገው ትግል በፍጹም ተስፋ አትቁረጡ ማለታቸው ተገለጸ!

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በሳላማንካ በሚገኘው የአውሮፓ ዓለም አቀፍ ጥናት ተቋም ተመራማሪዎች እና ባለሙያዎች ወደ ሰላም በሚወስደው መንገድ ላይ ተስፋ ከመቁረጥ ወደኋላ ስይሉ ወደ ፊት እንዲራመዱ አበረታተዋል

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስቸስኮስ “እያንዳንዱ ጦርነት ዓለም አሁን ካለችበት አሁናዊ ሁኔታ በባሰ መልኩ በከፋ ሁኔታ ላይ ይጥላታል” በማለት ያላቸውን ስጋት ደጋግመው የተናገሩ ሲሆን “በሰዎች መካከል ሰላም ልንገነባ የሚገባን እና እግዚአብሔርን አጥብቀን የመለመን አስፈላጊ እና መልካም ነገር ነው” ሲሉ አክለው ገልጸዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በስፔን ሳላማንካ የሚገኘውን የአውሮፓ ዓለም አቀፍ ጥናት ኢንስቲትዩት አባላትን ባነጋገሩበት ወቅት፣ በዓለም አቀፍ ግንኙነት የትምህርት ሥራቸው መሪዎች በተሻለ ዓለም ግንባታ ላይ ለውጥ እንዲያደርጉ ማዘጋጀት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱ የሰላምን ጽንሰ ሐሳብ ማንፀባረቅን በተመለከተ እንዳሉት ሰላም “በኃይል ሚዛን ላይ ብቻ የተመሠረተ ወይም ፍትሐዊ ጥያቄዎች ጸጥ ለማድረግ ያለመ መሆኑ” ፈተና ነው ብለዋል። ነገር ግን በምትኩ “እግዚአብሔርን በቅንዓትና በፍቅር ልንለምነው የሚገባን ጠቃሚ ነገር ” ነው ሰላም ሲሉ አክለው ተናግረዋል።

እንደ አለመታደል ሆኖ አሁን ያለው ሁኔታ ጦርነት ሁል ጊዜ በሰው ልጆች ላይ ሽንፈትን የሚወክል መሆኑን ብቻ ሊያጎላ እንደሚችል ጠቁመዋል።

"ጦርነት የፖለቲካ እና የሰብአዊ ውድቀት ነው፣ አሳፋሪ በሆነ ሁኔታ እጅ መስጠት እና በክፉ ኃይሎች ፊት ሽንፈት ነው" ሲሉ በግንኙነቱ ወቅት በቁጭት የተናገሩት ቅዱስነታቸው እናም ያለፉት 100 አመታት በግጭት እና በሰው ሰራሽ ውድመት የተሞላ መሆኑን አውግዟል።

"ለዚህም ነው ለሰው ልጅ መግባባት እና ሰላም የሚደረገው ትግል ስንታክት መሥራት አለብን የምለው በዚሁ ምክንያት ነው፣ በዚህ ውስጥ ጠንክረን መሥራት ይኖርብናል" ብለዋል።

ባለፈው ክፍለ ዘመን ሶስት የዓለም ጦርነቶች

በዚህ ባለፈው ክፍለ ዘመን ሶስት የዓለም ጦርነቶች መኖራቸውን በምሬት በማስታወስ በዩክሬን ጦርነት ውስጥ የሚታየውን የአሁኑን ጨምሮ፣ የጦር መሳሪያ ማምረት ትርፋማ መሆኑን ብዙዎቹ እየተረዱ መምጣታቸውን በአሉታዊ መልኩ የጠቆሙት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ “ጦር መሣሪያ ለአንድ አመት የማይመረት ከሆነ አንድ ዓመት ብቻ በዓለም ውስጥ ያለውን የረሃብ ችግር ይፈታል” ያሉ ሲሆን እናም የሰው ልጅ “የጦርነት አቅጣጫ ወደ ጥፋት” እንደሚወስድ እስካሁን ድረስ በቅጡ አልተረዳም በማለት ስለ ሁኔታው አሳሳቢነት ተናግረዋል።

በወቅቱ ባለው የጦር መሳሪያ ቴክኖሎጂ "በአንድ ቦምብ ብቻ ከተማዋን ማፍረስ ትችላላችሁ" የሚለውን እውነታ እንዲያስቡበት ቅዱስነታቸው የጋበዙ ሲሆን እናም "ምን እንጠብቃለን? ወደዚህ አቅጣጫ እየሄድን ነው ይህንን ያልተረዳን ይመስላል ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ “ጦርነት አስከፊ ነው፣ ሆኖም ተስፋ ልንቆርጥ አይገባም” ሲሉ በድጋሚ የተናገሩ ሲሆን ዛሬ ከምናየው አመድ አዲስ ነገር ሊወለድ ይችላል በዚህ ውድቀት ውስጥ ለህይወት ትምህርት እናገኛለን ሲሉ ያላቸውን ተስፋ ቅዱስነታቸው ገልጸዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ እ.ኤ.አ. በ 2014 የጦርነት ሰለባ የሆኑ ሰዎች የተቀበሩበትን መካነ መቃብርን ሲጎበኙ የተሰማቸውን ሀዘን አስታውሰዋል ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እ.አ.አ በሕዳር 2 በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ የሚከበረውን “የሁሉም ሙታን ቀን” በሚከበርበት እለት በጦርነት የተገደሉትን በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሞት ለማስታወስ መካነ መቃብር እንደሚጎበኝ ተናግረዋል ።

የናዚን ፍጻሜ እና የአውሮጳን ነፃ መውጣት ማክበር በጣም ጥሩ ነው ሲሉ ቅዱስነታቸው ንግግራቸውን የቀጠሉ ሲሆን  ነገር ግን የሰው ልጅ የጦርነትን ድራማ አለመዘንጋት አስፈላጊ ነው፡- “ጦርነት በጣም አስፈሪ ነው። እናም ከዚህ ውድቀት አዲስ ነገር መፍጠር አለብን ፣ በእሱ ውስጥ የህይወት ትምህርት ማግኘት አለብን” በማለት አክለው ገለጸዋል።

መፍትሄዎችን መፈለግ

በመጨረሻም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ እንደ ተናገሩት ከሆነ በጸሎት እና በስራ መፍትሄ ለማምጣት መጣር አለብን ያሉ ሲሆን “በመልካም ፈቃድ ላይ በተመሰረተ መልኩ ተባበሩ፣ ፍቅር፣ ወንድማማችነት እና እውነተኛ ሰብአዊነት ከእምነት የተወለደ ጥላቻን፣ እምቢተኝነትንና ጭካኔን እንደሚያሸንፉ መስክሩ!” ካሉ በኋላ ቅዱስነታቸው ንግግራቸውን አጠናቀዋል።

 

27 January 2023, 16:28