ፈልግ

የፍልስጤማውያን እና የእስራኤላውያን ግጭት የፍልስጤማውያን እና የእስራኤላውያን ግጭት  (AFP or licensors)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በቅድስት አገር በተፈጸሙት ጥቃቶች የተገደሉ ሰዎችን በጸሎታቸው አስታወሱ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ባለፈው ሳምንት በፍልስጤማውያን እና በእስራኤላውያን መካከል የሰዎች ሕይወት የጠፋበትን ግጭት በማስታወስ፣ ቅድስት ምድር የተረጋጋች እና ፈጣን የሰላም መፍትሄ እንዲገኝላት በማለት ተማጽነዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ እሑድ ጥር 21/2015 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የኅብረት ጸሎት ለማቅረብ እና አስተምህሮአቸውን ለመከታተል ለተሰበሰቡት ምዕመናን ባሰሙት ንግግር፣ ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ የመጣው የሰው ሕይወት የሚጠፋበት ግጭት በሁለቱ ሕዝቦች መካከል ያለውን የመተማመን ጭላንጭል የሚያጥፋ መሆኑን አስረድተዋል።  

በቅድስት ሀገር በቅርቡ በተፈጠረው ሁከት የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸው፣ “ከአዲሱ የጎርጎሮሳውያኑ ዓመት መጀመሪያ ወዲህ በደርዘን የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን በእስራኤል ጦር በተፈጸመው ተኩስ ተገድለዋል" ብለዋል። “የእስራኤል ወታደራዊ ፀረ-ሽብርተኝነት ኃይሎች ፍልስጤም ውስጥ ባካሄዱት ወረራ” አንዲት ሴትን ጨምሮ 10 ፍልስጤማውያን መሞታቸውን፣ ያለፈው ዓርብም ከምኩራብ የሚወጡ 7 እስራኤላውያን አይሁዶች የተገደሉበትን እና ሌሎች ሦስት የቆሰሉበትን ክስተት በሐዘን አስታውሰው፣ ለሁለቱ መንግሥታት እና ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ባቀረቡት ጥሪ፣ የሰላም መፍትሄ መንገዶችን ሳይዘገዩ እንዲፈልጉ፣ ውይይት እና ልባዊ ሰላም ፍለጋን የሚያካትቱ መንገዶችን እንዲፈልጉ በማለት ጠይቀው፣ ምዕመናን በሙሉ ለቅድስት ሀገር ሰላም እንዲጸልዩ አደራ ብለዋል።

በኢየሩሳሌም ውጥረት ነግሷል

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱ ጥሪ ይፋ የሆነው በፍልስጤማውያን እና በእስራኤል ፖሊሶች መካከል ተጨማሪ የኃይል ግጭት ተከትሎ ሲሆን፣ ያለፈው ቅዳሜ ምሽት በኢየሩሳሌም ከተማ ሁለት ጥቃቶች መቀስቀሳቸው ታውቋል። ቅዳሜ ማምሻውን የእስራኤል ፖሊሶች በኢየሩሳሌም ከተማ ወደሚገኙ የአረብ መንደሮች በመግባት የጥቃቶቹ ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ ፍለጋ ማካሄዳቸው ታውቋል። ያለፈው ዓርብ ማምሻውን የምሥራቅ ኢየሩሳሌም ነዋሪ የሆነ አንድ ፍልስጤማዊ ሰባት እስራኤላውያንን ገድሎ 3 ሰዎችን ማቁሰሉ ይታወሳል። ቅዳሜ ማለዳ ላይ አንድ የ13 ዓመት ዕድሜ ፍልስጤማዊ አዳጊ ሕጻን በተሰበሰቡት እስራኤላውያን ላይ ተኩሶ ከፍቶ ሁለቱን ማቁሰሉ ታውቋል።

የሟቾች ቁጥር መጨመር

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ቅዳሜ ጥር 20/2015 ዓ. ም. ማምሻውን ከጸጥታ ካቢኔያቸው ጋር ስብሰባ ማድረጋቸው ታውቋል። የመጨረሻዎቹ አመጾች መነሻ፣ ባለፈው ሳምንት የእስራኤል ጦር በምዕራብ ሰርጥ ጄኒን ከተማ ባካሄደው ወረራ 10 ፍልስጤማውያን መገደላቸውን ተከትሎ ነው ተብሏል። እንደ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መረጃ መሠረት፣ ባለፈው ጎርጎሮሳውያኑ 2022 ዓ. ም. በሁለቱ ወገኖች መካከል በተፈጠረ ግጭት ከ150 በላይ ፍልስጤማውያን እና ከ20 በላይ እስራኤላውያን መገደላቸው ታውቋል።

30 January 2023, 16:55