ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፥ “ከአባካኝነት ባሕል ይልቅ ቸርነትን ማስፋፋት ይኖርብናል!”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ትናንት ጥር 21/2015 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለጸሎት ለሚሰበሰቡት ምዕመናን ከማቴ. 5: 1-12 በተወሰደው በዕለቱ ምንባብ ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን አቅርበዋል። ቅዱስነታቸው ለምዕመናኑ ባቀረቡት ስብከት፣ ከአባካኝነት ይልቅ የቸርነት ባሕልን ማስፋፋት እንደሚገባ አሳስበዋል። ክቡራት እና ክቡራን ከዚህ በመቀጠል፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እሑድ ጥር 21/2015 ዓ. ም. ያቀረቡትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ትርጉም ሙሉ ይዘቱ እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን፥

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ እንደምን አረፈዳችሁ!

በመስዋዕተ ቅዳሴው ጸሎት ላይ ከማቴ. 5: 1-12 ተወስዶ የተንበበው ምንባብ ስለ ብጹዓ ይናገራል። በዚህ ምዕራፍ በቁጥር ሦስት ላይ የተጻፈው መሠረታዊ መሆኑን እንመለከታለን። እንዲህም የሚል ነው፥ ‘በመንፈስ ድሆች የሆኑ ብጹዓን ናቸው፤ መንግሥተ ሰማይ የእነርሱ ናትና።’ (ማቴ. 5: 3)

ለመሆኑ የመንፈስ ድሆች እነማን ናቸው? በመንፈስ ድሆች የሆኑት በራሳቸው መመካት የማይችሉ፣ ራሳቸውን ችለው የማይኖሩ እና ‘በእግዚአብሔር ፊት ለማኞች’ ሆነው የሚኖሩ ናቸው። እነዚህ ሰዎች እግዚአብሔር እንደሚያስፈልጋቸው የሚሰማቸው፣ እንዲሁም መልካም የሆነው ሁሉ ከእርሱ ዘንድ በጸጋ ስጦታ እንደሚሰጣቸው የሚገነዘቡት ናቸው። በመንፈስ ድሆች የሆኑት ከእግዚአብሔር የሚቀበሉትን ስጦታ ያከብሩታል፣ ዋጋንም ይሰጡታል። ስለዚህ ምንም ዓይነት ስጦታ እንዲባክንባቸው አይፈልጉም። በዛሬው አስተምሮዬ በዚህ የመንፈስ ድህነት ዓይነተኛ ገጽታዎች ላይ በማትኮር፣ ስጦታን አለማባከን የሚለውን መመልከት እወዳለሁ። በመንፈስ ድሆች የሆኑት ምንም ዓይነት ስጦታ እንዲባክንባቸው አይፈልጉም። ኢየሱስ ክርስቶስ ስጦታ ያለማባከን አስፈላጊነትን አሳይቶናል። ለምሳሌ ተርበው ለነበሩ በርካታ ሰዎች አምስት የገብስ እንጀራ እና ሁለት ዓሣ ባርኮ በበቂ መጠን እንዲመገቡ ካደረጋቸው በኋላ ምንም ነገር እንዳይባክን፣ የተረፈው ምግብ እንዲሰበሰብ ጠይቋል። ከጠገቡም በኋላ ደቀ መዛሙርቱን ‘አንድም እንኳ እንዳይጠፋ የተረፈውን ቁርስራሽ አከማቹ’ አላቸው (ዮሐ. 6:12) አለማባከን የራሳችንን፣ የሰዎችን እና የነገሮችን ዋጋ እንድናደንቅ ያስችለናል። ይሁን እንጂ ይህ ብዙውን ጊዜ ችላ የተባለበት መርህ ነው። በተለይ በበለጸጉ ማኅበረሰቦች ዘንድ የማባከን እና የመጣል ባሕል ይታያል። ሁለቱም ጎጂዎች ናቸው። ስለዚህ በከንቱ የማባከን እና የመጣል አስተሳሰብ የሚቃረኑ ሦስት ተግዳሮቶችን ላቀርብላችሁ እወዳለሁ።

የመጀመሪያው ተግዳሮት፥ ስጦታዎች የሆንን እኛ እራሳችን መባከን የለብን። እያንዳንዳችን አንዳችን ለአንዳችን መልካም ስጦታዎች ነን። እያንዳንዱ ሰው፣ ወንድ ወይም ሴት በችሎታው ብቻ ሳይሆን በሰዓዊ ክብሩ ሀብታም ነው። እያንዳንዳችን በእግዚአብሔር የተወደድን እና ዋጋ ያለን ውድ ስጦታዎች ነን። ኢየሱስ ክርስቶስ እኛ ባለን ሃብት ሳይሆን በማንነታችን የተባረክን እንደሆንን ይናገራል። ስለዚህ አንድ ሰው ይህን ካለመረዳት የተነሳ ራሱን በሚጥልበት ጊዜ እራሱን ያባክናል ማለት ነው። እራሳችንን ‘የማንጠቅም ወይም ለምንም ብቁዎች ያልሆንን’ ከማለት፣ የተሳሳትን እና በሐዘን እንድንወድቅ የሚያደርጉ ፈተናዎችን በእግዚአብሔር ዕርዳታ ለማሸነፍ ጥረት እናድርግ።

ሁለተኛው ተግዳሮት፥ ያሉንን ስጦታዎች አለማባከን የሚል ነው። ብዙ ሰዎች በረሃብ እየሞቱ ባሉበት በዚህ ወቅት፣ በዓለማችን ውስጥ በየዓመቱ ከጠቅላላው የምግብ ምርት ውስጥ አንድ ሦስተኛው እንደሚባክን ይነገራል። በዚህ መንገድ የተፈጥሮ ሀብቶች ጥቅም ላይ ሊውሉ አይችሉም። ማንም ሰው ለዕለታዊ ሕይወቱ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች እንዳይጎድልበት፣ የመገልገያ ዕቃዎች እንክብካቤ ሊደረግላቸው ይገባል። ያለንን ከማባከን ይልቅ የፍትህ፣ የቸርነት እና የሥነ-ምህዳር ባሕልን ማስፋፋት ይኖርብናል።

ሦስተኛው እና የመጨረሻው ተግዳሮት፣ ሰዎችን ማግለል  እና በብቸኝነት እንዲሰቃዩ ማድረግ የሚል ነው። የመጣል ባሕል እንዲህ ይላል፥ ‘የምታስፈልገኝን ያህል እጠቀምብሃለሁ! ከዚያ በኋላ ግን ሰለማታስፈልገኝ ወደ ውጭ አውጥቼ እወረውርሃለሁ!’ በተለይም በጣም የደከሙት፣ ገና ያልተወለዱ ሕጻናት፣ አዛውንት፣ የተቸገሩት እና ለድህነት ሕይወት የተዳረጉት ይህ ዕድል ያጋጥማቸዋል። ነገር ግን ሰዎች እንደ ዕቃ ሊጣሉ እና ለድህነት ሕይወት ሊዳረጉ አይገባም። ምክንያቱም እያንዳንዱ ሰው የተቀደሰ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው። በዕድሜ ወይም በሌሎች ምክንያቶች የሰው ልጅ መናቅ እና ከማኅበራዊ ሕይወት መወገድ የለበትም። በእነዚህ ሁኔታዎች ውስጥ የሚገኝ እያንዳንዱ ሰው ልዩ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው። ስለዚህ ሕይወት ሁል ጊዜ ክብር እና እንክብካቤ ሊሰጠው ይገባል እንጂ ሊጣል ወይም ሊረሳ አይገባም።

ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ ሆይ! አንዳንድ ጥያቄዎችን እራሳችንን እንጠይቅ፥ ከምንም በላይ የመንፈስ ድህነትን እንዴት እኖረዋለሁ? ለእግዚአብሔር ቦታ መስጠት እንዳለብኝ አውቃለሁ? እሱ መልካም፣ እርሱ እውነተኛ እና ታላቅ ሀብቴ መሆኑን አምናለሁ? እግዚአብሔር እንደሚወደኝ አምናለሁ? ወይንስ የእርሱ ስጦታ መሆኔን እየረሳሁ እራሴን በሐዘን እጥላለሁ? ላለማባከን እጠነቀቃለሁ? ንብረቶችን ሃላፊነት በተሞላበት መንገድ በተጠያቂነት እጠቀማቸዋለሁ? ያሉኝን ነገሮች ከሌሎች ጋር ለመካፍል ፈቃደኛ ነኝ ወይስ ራስ ወዳድ ነኝ? በመጨረሻም፣ አቅመ ደካሞች ውድ የእግዚአብሔር ስጦታዎች መሆናቸውን በመገንዘብ፣ እርሱ በጠየቀኝ መሠረት እንከባከባቸዋለሁ? የተለያዩ ዕድሎችን የተነፈጉ ድሆችን አስታውሳለሁ?

ሕይወት ውድ የእግዚአብሔር ስጦታ እንደሆነች እና እኛም እራሳችንን የእግዚአብሔር ስጦታዎች አድርገን እንድናቀርብ ብጽዕት እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትርዳን።

30 January 2023, 16:33