ፈልግ

ለቤተሰብ የቀረበ የመስዋዕተ ቅድሴ ጸሎት ሥነ-ሥርዓት  ለቤተሰብ የቀረበ የመስዋዕተ ቅድሴ ጸሎት ሥነ-ሥርዓት  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፥ "የቤተሰብ ደስታ በችግር ጊዜም ዘላቂ ነው!"

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ለጣሊያን የቤተሰብ ማኅበራት አንድነት ኅዳር 23/2015 ዓ. ም. መልዕክት አስተላልፈዋል። ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው ክርስቲያን ቤተሰቦች ግልጽ፣ እንግዳ ተቀባይ፣ አካባቢያቸውን ጨምሮ መከራ በበዛበት ዓለም ውስጥ ድጋፋቸውን እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

"ቤተሰብ መሆን ምስጋና ማቅረብን የሚያነሳሳ አስደሳች ስጦታ ነው" ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ለቤተሰብ ማኅበራት አንድነት ባስተላለፉት መልዕክት የቤተሰብ ማኅበራትን በመወከል ለሚያሰሙት ተገቢ ድምጽ ምስጋናቸውን አቅርበው፣

ዘወትር ማጉረምረም ሳይሆን አወንታዊ አመለካከት ያለው፣ ርዕዮተ ዓለማዊ ሳይሆን ብዙውን ጊዜ ያልተገባ ቅጣት የሚደርስበት የሰፊው ቤተሰብ ማኅበር ፍላጎቶችን በተግባር የመተርጎም አቅም ያለው መሆን ይኖርበታል ብለዋል።

ቤተሰብ የመሆን ደስታ ምስክርነትን በማስገንዘብ መልዕክታቸውን የጀመሩት ቅዱስነታቸው፣ “የቤተሰብ ፍቅር” በሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው ውስጥ ዋና መልዕክት መሆኑን ገልጸው፣ ደስታው ሁሉም ነገር መልካም ከሆነበት እውነታ ጋር የማይዛመድ ደስታ መሆኑን አስረድተው፣ “የቤተሰብ ሕይወት ሁል ጊዜ የተረጋጋ ሳይሆን አስቸጋሪ ወቅቶች እንዳሉት ሁላችንም እናውቃለን" ብለዋል። ይሁን እንጂ በእነዚህ ሁኔታዎች ውስጥ ማለፍ የሚችል ደስታ እንዳለው ገልጸው፣ ይህ ደስታ ጠልቆ የሚገኝ፣ ለቤተሰብ የቀረበ ስጦታ ተደርጎ የሚወሰድ እና የምስጋና ስሜት ያለው መሆኑን አስረድተዋል። ሁሉም ሰው የሚከተለው መደበኛ የቤተሰብ ሞዴል የለም ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ይልቁንም እያንዳንዱ ቤተሰብ የራሱ መንገድ እና ታሪክ እንዳለው፣ ብዙ አባወራዎች ወደፊት መራመድ የሚፈልጉት ዓለማዊ ሞዴሎችን በመከተል ሳይሆን ቀላል የሆኑ የአገልግሎት ዘይቤን በመቀበል መሆኑን አስረድተዋል። 

ፖለቲካ ከቤተሰብ እና ለቤተሰብ ሊሆን ይገባል!

ከቤተሰብ ጋር እና ለቤተሰብ መልካም የፖለቲካ ሥርዓት ሊኖር እንደሚገባ የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የቤተሰብ ማኅበር አባላት የጋራ ጥቅምን የሚያስጠብቅ ግልጽ እና ሁሉን አቀፍ አቀራረብ ተግባራዊ እንዲያደርጉ አሳስበዋል። ክርስቲያን ቤተሰብ በራሱ ዓለም ብቻ መኖር እንደማይችል እና የክርስቲያን ቤተሰብ ባሕርያትን በአካባቢው ከሚገኝ ማኅበረሰብ ጋራ በመጋራት፣ ራሱን ለሌሎች ግልጽ በማድረግ እንግዳ ተቀባይ እና የተቸገሩትን የሚደግፍ መሆን አለበት ብለዋል። አንድ ቤተሰብ ለወንድማማችነት እና ማኅበራዊ ወዳጅነት የተጠራ መሆኑን ገልጸው፣ መሠረቱን በሚኖርበት አካባቢ በማድረግ ለሌላው ዓለምም እራሱን ክፍት ያደረገ መሆን አለበት ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መልዕክታቸውን ሲያጠቃልሉ፣ ሰዎች እንደ ባለትዳሮች እና እንደ ቤተሰብ አባላት እራሳቸውን እንዲንከባከቡ አደራ ብለው፣ ይህም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለጸሎት፣ ለውይይት እና ለማኅበራዊ ሕይወት ጊዜ እንዲኖራቸው፣ እንዲሁም ከልጆቻቸው ጋር ለመሆን የሚያበረታታቸው መሆኑን ገልጸው፣ ጣሊያንን እያጋጠማት ላለው የሕዝብ ቁጥር መቀነስ ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል።

03 December 2022, 16:23