ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከአሜሪካ የካቶሊክ መጽሔት አዘጋጆች ጋር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከአሜሪካ የካቶሊክ መጽሔት አዘጋጆች ጋር   (Antonello Nusca)

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ መለያየት የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ባሕሪይ አለመሆኑን አስታወቁ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአሜሪካ ውስጥ ከሚታተም የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መጽሔት ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል። ሰፊ ርዕሠ ጉዳዮች በተነሱበት ቃለ ምልልሱ ቤተ ክርስቲያንን፣ ማኅበራዊ ጉዳዮችን፣ በዩክሬን ውስጥ የሚካሄደውን ጦርነት፣ የቫቲካን እና የቻይና ግንኙነት እንዲሁም የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳ ሐዋርያዊ አገልግሎት አስመልክቶ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ቅዱስነታቸው ምላሽ ሰጥተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“አሜሪካን ማጋዚን” ተብሎ የሚታወቅ የአሜሪካ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መጽሔት አዘጋጆቹ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ቃለ ምልልስ ማድረጋቸውን ገልጸው፣ ቤተ ክርስቲያኒቱን በሚመለከቱ ሰፊ ርዕሠ ጉዳዮች ላይ ከቅዱስነታቸው ጋር ቃለ ምልልስ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።         

በአሜሪካ ኢየሱሳውያን ማኅበር መሪነት የሚዘጋጅ መጽሔት አምስት ተወካዮች ማክሰኞ ኅዳር 13/2015 ዓ. ም. ከር. ሊ ጳ ፍራንችስኮስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ በአሜሪካ በምትገኝ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሚታዩ አለመግባባቶች የተነሳ ራስን ከእምነቱ መለየት፣ ዘረኝነት፣ በሴቶች ክኅነታዊ አገልግሎት እና የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸው አቋም፣ በዩክሬን ውስጥ ስላለው ጦርነት፣ ቫቲካን ከቻይና ጋር ያላት ግንኙነት እና የር. ሊ. ጳ ሐዋርያዊ አገልግሎት አስመልክተው ተነጋግረዋል።  

እግዚአብሔር ከእኔ ጋር ስላለ ደስተኛ ነኝ!

በሐዋርያዊ አገልግሎታቸው መካከል ሰላምን የሚሰጥ እና ደስተኛ የሚያደርጋቸው ነገር መኖሩን የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ ከእግዚአብሔር ጋር የመሆን እርግጠኝነት እና ከሕዝብ ጋር መሆናቸው ዘወትር ከፍተኛ ደስታን እንደሚሰጣቸው ገልጸው፣ አንዳንድ አስቸጋሪ በሆኑ ጊዜያት እግዚአብሔር እንደሚመራቸው እና ይህም ሰው ያለ እግዚአብሔር ድጋፍ ብቻውን መጓዝ እንደማይችል ዘወትር የሚያረጋግጥ እንደሆነ አስረድተዋል።

መለያየት ካቶሊካዊ ባሕሪይ አይደለም!

በአሜሪካ የፖለቲካ ሕይወት እንዲሁም በአገሪቱ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ውስጥም እያደገ የመጣውን ልዩነት በማስመልከት ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ቅዱስነታቸው፣ በሰሜን አሜሪካ ማኅበረሰብ መካከል ልዩ ርዕዮተ ዓለማዊን የሚከተለኡ አንዳንድ ቡድኖች መኖራቸውን በማስታወስ በተለይም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለውን የርዕዮተ ዓለም ወገንተኝነት አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል አስጠንቅቀዋል። መለያየት የካቶሊካዊነት ባሕሪይ እንዳልሆነ ገልጸው፣ ምን ጊዜ የአንድነት አቋም ያለው ካቶሊካዊነት መሠረታዊ አካሄዱን ከዘነጋ የመለያየት አደጋ ሊያጋጥመው እንደሚችል አስጠንቅቀዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ በጊዜው በፈሪሳውያን፣ በሰዱቃውያን፣ በቀናተኞች እና በሌሎች የአይሁድ ወገኖች መካከል መለያየት እንደነበር መናገሩን አስታውሰው፣ በካቶሊክ ምዕመናን መካከል መለያየት የሚኖር ከሆነ አንድነት ጠፍቶ መለያየትን ሊያስከትል እንደሚችል አስረድተዋል።

ጳጳሳት እና የጳጳሳት ጉባኤዎች

ሰሜን አሜሪካ ውስጥ እምነት እና ሥነ ምግባርን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ በብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች እና በምዕመናኑ መካከል መራራቅ እያደገ መምጣቱን የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ ይህ በሚሆንበት ጊዜ ጉዳዩን መመልከት ያለበት የጳጳሳቱ ጉባኤ ሳይሆን የሀገረ ስብከቱ ጳጳስ ከምዕመናኑ ጋር በመገናኘት ወሳኝ ሚና ሊጫወት እንደሚች አጽንኦት ሰጥተው፣ የጳጳሳት ጉባኤዎች ለመረዳዳት እና ለኅብረት ዓላማ የተመሠረቱ የአንድነት ምልክት መሆናቸውን ገልጸዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ ጳጳሳትን ሰየመ እንጂ የጳጳሳት ጉባኤ አልመሠረተም ያሉት ቅዱስነታቸው፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ በጳጳሱ፣ በምዕመናኑ እና በሀገረ ስብከቱ መካከል ባለው ግንኙነት ውስጥ መሆንኑን አስረድተዋል።

በዩክሬን ጦርነት ላይ ያለኝ አቋም ለሁሉም ግልጽ ነው!

በዩክሬን ውስጥ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ላይ ባላቸው አቋም ጥቃትን እያደረሰች የምትገኝ ሩሲያን በቀጥታ መተቸት ያልፈለጉበት ምክንያት ምን እንደ ሆነ የተጠየቁት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፥ “በዚህ ጦርነት ውስጥ ማንን ማውገዝ እንደምፈልግ ግልጽ ቢሆንም ላለማስከፋት ስል በአጠቃላይ ለማውገዝ ሞክሬአለሁ።” ብለዋል። ስለ ዩክሬን ስናገር በመከራ እና በስቃይ ውስጥ ስለሚገኝ ሕዝብ እንደሚናገሩ የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ የሚሰቃይ ሕዝብ ካለ የሚያሰቃይ ክፍል መኖሩ ግልጽ መሆኑን ተናግረው፣ ስለ ዩክሬን ጦርነት በሚናገሩበት ጊዜ አገሪቱን የወረራት የሩሲያ መንግሥት እንደሆነ እና ጭካኔያዊ ተግባር የሚፈጸመው በወታደሮቿ ስለመሆኑ በርካታ መራጃዎች ያሏቸው መሆኑን ገልጸዋል። አክለውም ግጭቱን ለማስቆም እና ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባት ዩክሬንን ለመደገፍ የግል ጥረት ማድረጋቸውን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ ጦርነቱ ከተጀመረ በሁለተኛው ቀን ሮም በሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲ ደርሰው ጦርነቱ እንዲቆም አቤት ማለታቸውን፣ ከዩክሬኑ ፕሬዚደንት ጋር በስልክ ሁለት ጊዜ መገናኘታቸውን፣ በሁለቱም ወገኖች በኩል የሚገኙ የጦር እስረኞች እንዲፈቱ እና እንዲሁም ኪየቭን እና ሞስኮን ለመጎብኘት መፈለጋቸውንም ተናግረዋል።

ዘረኝነት በእግዚአብሔር ላይ የሚፈጸም ኃጢአት ነው!

በሰሜን አሜሪካ ውስጥ የሚታየውን ዘረኝነት ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በሰሜን አሜሪካ ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ አፍሮ-አሜሪካዊ ካቶሊካዊ ምዕመናን ጉዳይ ትኩረት አለማግኘቱ በምዕመናኑ መካከል ቅሬታን ሊፈጥር እንደሚችል ተናግረዋል። የአፍሮ-አሜሪካዊያን ካቶሊካዊ ምዕመናን ስቃይ እንደሚረዱት የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ ለምዕመናኑ ያላቸውን ፍቅር ገልጸው፣ የሚደርስባቸውን በደል በትክክለኛው መንገድ መቃወም እንጂ እምነቱን መተው እንደሌለባቸው አሳስበዋል። “ዘረኝነት በእግዚአብሔር ላይ የሚፈጸም ኃጢአት ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ፣ ሐዋርያዊ አባቶች እና ምእመናን ተባብረው ዘረኝነትን ለማጥፋትና የበለጠ ፍትሐዊ ዓለምን ለማምጣት በኅብረት ጥረት ማድረግ እንደሚገባ አደራ ብለዋል። አያይዘውም በሰቤን አሜሪካ የሚገኙ ነባር ተወላጆችን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ በአገሪቱ ለሚገኙ ላቲኖ-አሜርካዊ ዜጎችም ከፍተኛ ፍቅር ያላቸው መሆኑን ገልጸዋል።

ቤተ ክርስቲያን እናት ናት!

የሴቶች ክኅነታዊ አገልግሎት በማስመልከት ለቀረበላቸው ጥያቄ ማብራሪያን የሰጡት ቅዱስነታቸው፣ ጥያቄው  የቤተ ክርስቲያን የአገልግሎት ገጽታ የሚመለከት ሥነ-መለኮታዊ ጥያቄ እንደሆነ በመናገር፣ ቤተ ክርስቲያን ከአገልግሎት በላይ መሆኗን እና ከቅዱስ ጴጥሮሳዊነት መርሕ በተጨማሪ በጣም አስፈላጊ ሌላ መርህ መኖሩን፣ ይህም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ማርያማዊ መርህም መኖሩን እና ቤተ ክርስቲያንም የኢየሱስ ክርስቶስ ሙሽራ መሆኗን አስረድተዋል። የቤተ ክርስቲያን አስተዳደርን የሚመለከት ሦስተኛው መንገድ መኖሩን የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለሴት ምዕመናን ተጨማሪ የአገልግሎት ሥፍራ መስጠት አስፈላጊ መሆኑን እንደሚያምኑ ተናግረው፣ በቅድስት መንበር ሥር የሚገኙ ጳጳሳዊ ምክር ቤቶችም ለሴት ምዕመናን ተጨማሪ ሃላፊነቶችን በመስጠት ዕድገት በማሳየት ላይ እንደምትገኝ አስረድተዋል።

29 November 2022, 16:19