ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ “እግዚአብሔር ሩቅ ሳይሆን በዕለታዊ ሕይወታችን ውስጥ እንደሚገኝ እንወቅ!”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሑድ ኅዳር 18/2015 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን እና መንፈሳዊ ነጋዲያን ጋር ሆነው የእኩለ ቀኑን የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት በኅብረት አቅርበዋል። ከልዩ ልዩ የጣሊያን ከተሞች እና ሌሎች አገራት ከመጡ ምዕመናን ጋር ካቀረቡት ጸሎት አስቀድመው፣ በዕለቱ በተነበበው የማቴ. 24: 37 – 44 ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን አቅርበዋል። በስብከታቸውም “የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መምጣት በምንጠባበቅበት በገና ሰሞን፣ እግዚአብሔር በመካከላችን ሁል ጊዜ እንደሚገኝ በማወቅ እርሱን ለመቀበል ዝግጁዎች ልንሆን ይገባል” ብለዋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን ያቀረቡትን ስብከት ትርጉም ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን፥

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

በዛሬው የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት መካከል ከማቴ. 24: 37 – 44 ተወስዶ የተነበበው የቅዳሴ ወንጌል ምንባብ፣ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መምጣት የሚገልጽ የደስታ ቃል ኪዳን ያለበት ነው። በማቴ. 24:42 ላይ ‘ጌታችሁ ይመጣል’ ይላል። የተስፋችን መሠረት የሆነው ይህ ቃል ኪዳን በችግር እና በስቃይ ሕመም ውስጥ ለሚገኝ ሕይወታችን ድጋፍ ይሆነናል። እግዚአብሔር የሚመጣበት ጊዜ መቃረቡን መዘንጋት የለብንም! እግዚአብሔር ወደ እኛ ዘወትር ይመጣል፣ ይጎበኘናል፣ ይቀርበናል። በጊዜው መጨረሻ በእቅፉ ሊቀበለን ተመልሶ ይመጣል። ነገር ግን ከሁሉ አስቀድመን ራሳችንን ልንጠይቅ የሚገባን አንድ ጥያቄ አለ። ኢየሱስ ክርስቶስ በምን መልኩ እንደሚመጣ እና እርሱ መሆኑንም እንዴት ማወቅ እንችላለን? እንዴትስ እንቀበለዋለን? የሚሉ ጥያቄዎችን መመልከት ይኖርብናል።

‘ኢየሱስ ክርስቶስ በምን ሁኔታ ይመጣል?’ የሚለውን የመጀመሪያ ጥያቄ ስንመለከት፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በመንገዳችን አብሮን እንደሚጓዝ ሲነገር ብዙውን ጊዜ እንሰማለን። ነገር ግን አዕምሮአችን በብዙ ነገሮች ስለሚያዝ ይህን እውነት እንደ ሐሳብ ብቻ እንመለከተዋለን። በእርግጥ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚመጣ ብናውቅም እንኳ እውነቱን በተግባር አንኖረውም። ወይም አንዳንድ ተዓምራትን እያሳየን በአስደናቂ መንገድ እንደሚመጣ እንገምታለን። ‘በኖኅ ዘመን እንደ ነበረ የሰው ልጅ መምጣትም እንዲሁ ይሆናልና።’ (ማቴ. 24:37) እግዚአብሔር በሕይወታችን ውስጥ ተሰውሮ እንደሚገኝ እና ዘወትር ከእኛ ጋር መኖሩን ልብ ልንለው ይገባል። እርሱ በተለመደው ዕለታዊ ሕይወታችን ውስጥ ይገኛል። እግዚአብሔር ራሱን ለእኛ የሚገልጸው ልዩ ክስተቶች በማሳየት ሳይሆን በዕለት ተዕለት ክስተቶች አማካይነት ነው። በዕለታዊ ሥራዎቻችን መካከል እግዚአብሔር አለ። በተቸገሩት ሰዎች አምሳል እግዚአብሔር ራሱን ይገልጻል። ልንወጣ የማንችላቸው በሚመስሉ የመከራ ቀናት ውስጥ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር አለ። ዘወትር ይጎበኘናል፣ ይጠይቀናል፣ በሥራዎቻችንም ያግዘናል።

ኢየሱስ ክርስቶስ በምን መልኩ እንደሚመጣ፣ እርሱ መሆኑንም እንዴት እናውቃለን? እንዴትስ እንቀበለዋለን? የሚለውን ሁለተኛውን ጥያቄ እንመለከታለን። መምጫውን በንቃት ልንጠብቅ ይገባል። የመምጫ ጊዜውን ካለማወቅ የተነሳ ሳንዘጋጅ እንዳንቆይ ኢየሱስ ክርስቶስ አስጠንቅቆናል። ቅዱስ አውግስጢኖስ ‘የእግዚአብሔርን የጉብኝት ቀን በፍርሃት እጠባባቃለሁ!’ ማለቱን በሌሎች አጋጣሚዎች መናገሬን አስታውሳለሁ። ቅዱስ አውጎስጢኖስ ይህን ያለበት ምክንያት እግዚአብሔር እንደጎበኘው ሳይረዳ እንዳይቀር በመፍራት ነው።በእርግጥም ኢየሱስ ክርስቶስ፣ በኖኅ ዘመን የነበሩት ሰዎች ይበሉና ይጠጡ እንደነበር ተናግሯል። ‘የጥፋት ውሃም መጥቶ ሁሉንም ጠራርጎ እስኪወስድ ድረስ አላወቁትም ነበር፥ የሰው ልጅ መምጣትም ደግሞ እንዲሁ ይሆናል’ (ማቴ. 24:39) ይህን ልብ እንበል! በኖኅ ዘመን የነበሩ ሰዎች ምንም ነገር አላስተዋሉም ነበር! በግል ጉዳያቸው ተይዘው ነበርና የጎርፉን መምጣት አላስተዋሉም ነበር። “በዚያን ጊዜ ሁለት ሰዎች በእርሻ ይሆናሉ፤ አንዱ ይወሰዳል አንዱም ይቀራል” በማለት ኢየሱስ ክርስቶስ በማቴ. 24:40 ላይ ተናግሯል። የጌታ መምጫ ቀን እንዴት ማወቅ ይችላል? ከሌሉች ቀናት የሚለየው በምንድን ነው? ይህን ማወቅ የሚቻለው ነቅቶ በመጠበቅ ነው። በዕለት ተዕለት ሕይወት መካከል እግዚአብሔር መኖሩን በመረዳት እና በማስተዋል ነው። ነገ ግን ሃሳባችን እና ትኩረታችን የሚከፋፈል ከሆነ ምንም ላናስተውል እንችላለን።

ወንድሞች እና እህቶች ሆይ! የኢየሱስ ክርስቶስን መምጣት በምንጠብቅበት በዚህ የገና ሰሞን ከምንገኝበት የሕይወት ወጣ ውረዶች ተለይተን፣ ከአንቅልፋችንም በመንቃት ስለምገኝበት ሕይወት ራሳችንን ልንጠይቅ እንሞክር። በዕለት ተዕለት ሁኔታዎች መካከል እግዚአብሔር እንደሚገኝ ለማወቅ እሞክራለሁ? ወይስ በሃሳብ መከፋፈል የተነሳ በነገሮች ተጨናንቄያለሁ? በማለት ራሳችንን እንጠይቅ። ስለ እርሱ መምጣት ዛሬውኑ የማናውቅ ከሆነ በዘመኑ ፍጻሜ በሚመጣበት ጊዜም ዝግጁዎች ሆነን መጠበቅ አንችልም። ስለዚህ ወንድሞች እና እህቶች ሆይ! የጌታን መምጫ ቀን ነቅተን እንጠብቅ። እርሱ ከእኛ ጋር፣ አጠገባችን ቢሆንም ነቅተን መጠበቅ ይኖርብናል። በናዝሬት ከተማ ከእግዚአብሔር በትህትና ያሳለፈችውን ሕይወት የተረዳች እና እግዚአብሔርን በማህፀኗ የተቀበለች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ እኛም በመካከላችን የሚገኘው ኢየሱስ ክርስቶስ የሚመጣበትን ቀን በሕይወታችን ውስጥ ትኩረት ሰጥተን ነቅተን እንድንጠብቅ ትርዳን።”

28 November 2022, 16:24