ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፥ “እውነተኛ መጽናናት የእግዚአብሔርን ፈቃድ መፈጸማችንን ያረጋግጥልናል!"

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ ረቡዕ ኅዳር 21/2015 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን እና መንፈሳዊ ነጋዲያን ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ አቅርበዋል። የቅዱስነታቸውን የዛሬ አስተምህሮ ከጣሊያን ከተሞች ጨምሮ ከልዩ ልዩ አገራት የመጡ ምዕመናን ተከታትለውታል። በዛሬው ሳምንታዊ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸው እውነተኛ መጽናናት የእግዚአብሔርን ፈቃድ እየፈጽምን መገኘታችንን ያረጋግጥልናል በማለት አስገንዝበዋል። ክቡራት እና ክብራን ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በዛሬው ዕለት ያቀረቡትን ጠቅላላ የትምህርት ክርስቶስ አስተምህሮ ትርጉም ከማቅረባችን አስቀድመን ለዕለቱ እንዲሆን ያስተነተኑበትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ እናቀርብላችኋለን፥

“ፍቅራችሁ በእውቀት እና በማስተዋል ሁሉ ከፊት ይልቅ እያደገ እንዲበዛ እጸልያለሁ፤ እንዲህም ያለው ዕውቀት የሚሻለውን ነገር ፈትናችሁ እንድትወድዱ ስለሚረዳችሁ ነው፤ በዚህም ለክርስቶስ ቀን ተዘጋጅታችሁ ንጹሖችና ያለ ነቀፋ በመሆን ለእግዚአብሔር ክብርና ምስጋና ከኢየሱስ ክርስቶስ በሚገኝ የጽድቅ ፍሬ የተሞላችሁ እንድትሆኑን ነው።” (ፊል. 1: 9-11)

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

በማስተዋል ላይ የምናደርገውን አስተንትኖ በመቀጠል፣ በተለይም መጽናናት በሚለው መንፈሳዊ ልምድ ላይ በማስተንተን፣ “እውነተኛ መጽናናትን እንዴት መለየት ይቻላል?” የሚለውን ጥያቄ እንመለከታለን። ይህ ስለዚህ በእኛ የግል ጥቅም ፍለጋ እንዳንታለል የሚያደርግ እና መልካም ማስተዋል እንዲኖረ የሚረዳ አስፈላጊ ጥያቄ ነው።

ከሎዮላው ቅዱስ ኢግናጤዎስ መንፈሳዊ ልምምዶች ውስጥ አንዳንድ መመዘኛዎችን ማግኘት እንችላለን። ሃሳቦች በሙሉ መልካም ከሆኑ፣ የሃሳቡ መጀመሪያ፣ መካከለኛው እና መጨረሻው፣ ሁሉም ወደ መልካም አቅጣጫ የሚያመራ ከሆነ፣ የመልካም መልአክ ምልክት ነው። በአንጻሩ በሃሳብ ሂደት መካከል መጥፎ የሆነ፣ ትኩረትን የሚከፋፍል ወይም ቀደም ብሎ ለማከናወን ካሰብነው መልካም ነገር ያነሰ፣ ወይም ነፍስን የሚያዳክም፣ ሰላምን እና መረጋጋት በማጥፋት እና ዕረፍት በማሳጣት ሁከት ውስጥ የሚያስገባ ሊሆን ይችላል። ይህ ሲሆን እነዚያ መልካም ያልሆኑ ሃሳቦች ከክፉ መንፈስ እንደመጡ ግልጽ ምልክት ነው።’ “መንፈሳዊ ልምምድ ቁ. 333)

እነዚህ ታዲያ አጭር አስተያየት እንድንሰጥባቸው የሚፈልጉ ውድ ምልክቶች ናቸው። ወደ መልካም ነገር ያተኮረ የመጀመሪያ መርህ ማለት ምን ማለት ነው? ለምሳሌ፣ ጸሎት ለማድረስ እናስባለን። ይህ ሃሳብ ለእግዚአብሔር እና ለጎረቤት ባለን ፍቅር በመታጀብ የልግስና እና የበጎ አድራጎት ሥራዎችን እንድናከናውን ይጋብዘናል። ይህ መልካም የመጀመሪያ ሃሳብ ነው። ነገር ግን ከዚህ በተለየ መልኩ ከሥራ ወይም በአደራ ከተሰጠን ኃላፊነት እንድንሸሽ የሚያደርግ ሌላ ሃሳብ ሊመጣ ይችላል። ለምሳሌ ቤት ማጽዳት ወይም ሌሎች የቤት ውስጥ ሥራዎችን ለመሥራት በምንነሳበት ጊዜ፣ መጀመሪያ ለማከናወን ያሰብነውን ተግባር በመተው ጸሎት ማድረስ እንዳለብን ይሰማናል። ነገር ግን ጸሎት አስቀድሞ ለማከናወን ያሰብነውን ሥራ እንዳንፈጽም የሚከለክል ሳይሆን በተቃራኒው፣ ያንን ሥራ በመልካም መንገድ ሠርተን ለማሳካት የሚረዳን መሆን አለበጥ ይህ የመጀመሪያውን የሃሳብ ደረጃ የሚመለከት ነው።

ከዚያም ቀጥሎ ማለትም ከኋላ የሚመጣው ሁለተኛው እና መካከለኛው ሃሳብ አለ። አሁንም በቀደመው ምሳሌ ላይ በመሆን፣ መጸለይ ብንጀምር የሚለውን በማሰብ፣ በሉቃ. 18፡9-14 ላይ የተገለጸው ፈሪሳዊ እንዳደረገው፣ ሌሎችን በመናቅ ራስን ብቻ ለማስደሰት መፈለግን ያካትታል። እነዚህ ምልክቶች መጥፎው መንፈስ ወደ ልባችን ውስጥ በመግባት መልካም ለማድረግ የነበረንን ሃሳብ ተግባራዊ እንዳናደርግ ይከለክለናል።

ከዚያም የመጨረሻ እና ሦስተኛው ሃሳብ አለ። ይህም ቀደም ሲል የተመለከትነው እና በልባችን ውስጥ ሊመጣ የሚችል የሃሳብ ዓይነት ነው። ይህም “ልቤ ውስጥ የመጣው ሃሳብ ወዴት ይወስደኛል?” የሚል ነው። ለምሳሌ የምንወደው እና ጠንክረን ከሠራን ደግሞ ጥሩ ውጤት የምናመጣበት ሥራ ሊገኝ ይችላል፣ ነገር ግን ይህ ሥራ የጸሎት ጊዜያችንን በመሻማት እንዳንጸልይ ያደርገናል። ነገር ግን እንደ ምንም ብለን ወይም ጨክነን ጸሎታችንን ሳናቋርጥ እናደርሳለን። በእግዚአብሔር በመታመን የተቀረው ሁሉ በእኛ ውሳኔ ላይ የተመሠረተ መሆኑን እምናለን። እዚህ ላይ መልካም ተግባር እንዳንፈጽም የሚያግድ የክፉ መንፈስ አስተዋጽዖ መኖሩን በግልጽ እንገነዘባለን።

እንደምናውቀው ጠላት የሚጠቀምበት መንገድ በጣም ረቂቅ ነው። በማይታይ ወይም በማናውቀው መንገድ ወደ ልባችን በመግባት ቀስ በቀስ ወደ ራሱ ይስበናል። ክፉ መንፈስ ሳናውቀው በስውር መንገድ ወደ ልባችን ውስጥ ይገባል። ከጊዜ በኋላም ጣፋጭ እና ጠንካራ ይሆናል። ያ ክፉ ሃሳብ ቀስ በቀስ ራሱን እውነት አድርጎ ይገልጻል።

ስለዚህ ይህን በመሰለ ችግር ውስጥ የሚገኝ ሰው ታሪክ፣ የተለያዩ ሃሳቦች ከየት እንደሚመጡ ለማወቅ እና እውነትን መርምሮ ለመረዳት እጅግ አስፈላጊ ነው። ተመሳሳይ ስህተቶችን ላለመድገም ከተሞክሮ እንድንማር ይጋብዘናል። እራሳችንን በሚገባ ባወቅን መጠን መጥፎ መንፈስ ከየት እንደመጣ እናስተውላለን። በየትኛው የልባችን በሮች እንደገባ ወይም ደካማ ጎናችን የቱ እንደሆነ በማወቅ ለወደፊት ትኩረት እንድንሰጥ ያግዘናል።

ዕለታዊ ሕይወታችንን ስናጤበው እንደ ምሳሌ ማቅረብ የምንችላቸው ታሪኮች ብዙ ናቸው። በየዕለቱ የሚናደርገው የህሊና ምርመራ እጅግ አስፈላጊ የሆነው ለዚህ ነው። ከተወሰነ እይታ አንጻር የሕይወት ልምድን እንደገና ማንበብ ጥረትን ይጠይቃል። በሕይወታችን ውስጥ እየሆነ ያለውን ነገር መገንዘብ አስፈላጊ ነው። የእግዚአብሔር ጸጋ በእኛ ውስጥ እየሰራ መሆኑን የምናውቅበት፣ በነጻነት እና በማወቅ እንድናድግ የሚረዳን ምልክት ነው።

እውነተኛ መጽናናት እግዚአብሔር ከእኛ የሚፈልገውን ነገር እየሠራን መሆናችንን፣ በእርሱ መንገዶች ማለትም በሕይወት፣ በደስታ እና በሰላም መንገዶች መጓዛችንን የሚያሳይ ማረጋገጫ ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ ማስተዋል በመልካም ነገር ላይ ብቻ የሚያተኩር ወይም ከሁሉ በላይ በሆነ መልካም ነገር ላይ ብቻ የሚያተኩር አይደለም። ማስተዋል አሁን በምንገኝበት ቦታ ስለሚጠቅመን ነገር፣ በዚህ መንገድ እንድናድግ መጠራታችንን፣ ማራኪ ነገር ግን እውነተኛ ባልሆኑ ምርጫዎች ላይ ገደብ እንድናደርግ እና መልካም የሆነ እውነተኛ ነገር ለማግኘት በምናደርገው ፍለጋ እንዳንታለል የሚረዳን ነው።”

30 November 2022, 16:33