ፈልግ

የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የባሕሬን ሐዋርያዊ ጉብኝት የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የባሕሬን ሐዋርያዊ ጉብኝት  

ባሕሬን፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስን ለመቀበል መዘጋጀቷ ተገለጸ

በባሕሪን የሚገኙ ክርስቲያኖች እና ሙስሊም ማኅበረሰብ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስን በእንግድነት ለመቀበል መዘጋጀታቸውን፣ በባሕሬን የመገናኛዎች ባለሙያ ወ/ሮ ኒቬዲታ ዳድፋሌ አስታውቀዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የእስልምና እምነት ተከታዮች ወደሚበዙባት ባሕሬን ሐሙስ ጥቅምት 24/2015 ዓ. ም. የገቡት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ በሁለት ጭብጦች ላይ እነርሱም በሃይማኖቶች መካከል በሚደረግ የጋራ ውይይት እና በአገሪቱ ለሚኖሩት ክርስቲያኖች ያላቸውን ቅርበት ለመግለጽ በሚሉት ላይ በማትኮር እንደሆነ ታውቋል። 

የቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ጉብኝት ለባሕሬን ታሪካዊ እንደሆነ የገለጹት የመገናኛ ባለሙያው፣ ምክንያቱን ሲገልጹ፥ “የጋራ ውይይትን ለማሳደግ በሚል ዓላማ ከዚህ በፊት ወደ ባሕሬን የመጣ ሰው የለም” በማለት የባሕሬን ብሔራዊ መገናኛዎች አማካሪ ወ/ሮ ኒቬዲታ፣ ቅዱስነታቸው ከጥቅምት 24-27/2015 ዓ. ም. ድረስ በባሕሬን የሚያደርጉትን 39ኛ ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝት በማስመልከት ባቀረቡት ገለጻ አስታውቀዋል።

እንግዳ ተቀባይ ማኅበረሰብ

ወ/ሮ ኒቬዲታ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ባሕሬን የአብያተ ክርስቲያናት እና የአምልኮ ቦታዎች የረጅም ጊዜ ታሪክ ያላት አገር መሆኗን ገልጸው፣ በቁጥር ከፍተኛ የእስልምና እምነት ተከታዮች ያሉባት አገር ብትሆንም፣ ክርስቲያን በዓላትን ጨምሮ የልዩ ልዩ እምነቶች ደማቅ በዓላት በአደባባይ የሚከበሩባት አገር መሆኗን አስረድተዋል። ከሰላሳ ዓመታት በላይ በባሕሬን እንደኖሩ የሚናገሩት ወ/ሮ ኒቬዲታ፣ ማኅበረሰቡ ግልጽ፣ ደስተኛ እና እንግዳ ተቀባይ መሆኑን ገልጸዋል። የሕንድ ተወላጅ እና የሂንዱ እምነት ተከታይ የሆኑት ወ/ሮ ኒቬዲታ፣ በተለያዩ ሃይማኖቶች መካከል ያለው ግንኙነት በመቻቻል አብሮ በሰላም እና በፍቅር መኖር ላይ የተመሠረተ እንደሆነ አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሐዋርያዊ ጉብኝታቸው አካል በሆነው እና ሁለት መቶ የሚደርሱ የልዩ ልዩ ሐይማኖቶች መሪዎች እና የእምነት ተወካዮች በሚሳተፉበት፣ “የምስራቅ እና ምዕራቡ ዓለም፣ የሰው ልጅ አብሮ መኖር” በሚል ርዕሥ በባሕሬን ለመጀመሪያ ጊዜ በተዘጋጀ የውይይት መድረክ መዝጊያ ሥነ ሥርዓት ላይ ለመገናኘት እንደሆነ ታውቋል። ሁለቱም ማኅበረሰቦች፣ ክርስቲያኑ እና ሙስሊሙ ማኅበረሰብ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስን “አባባ” ብለው እንደሚጠሯቸው የገለጹት ወ/ሮ ኒቬዲታ፣ ይህም ለቅዱስነታቸው የሚገባቸውን ፍቅር እና አክብሮት ለመግለጽ እንደሆነ አስረድተዋል። 

ሐሙስ ዕለት የታተሙት የባሕሬን ጋዜጦች፣ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና በንጉሥ ሃማድ ቢን ኢሳ አል ካሊፋ ምሥዕሎች የተሞሉ እንደነበር ተመልክቷል። ይዘው የወጡት ዜናዎች የቅዱስነታቸውን ሐዋርያዊ ጉብኝት የሚገልጹ እና በሃይማኖቶች መካከል በሚካሄድ ውይይት ላይ ያተኮሩ እንደነበር ታውቋል። የባሕሬን ሕዝብ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ ባሕሬን በመምጣታቸው የተደሰተው መልዕክታቸው እና የቆሙለት ዓላማ ለሰው ልጆ በሙሉ እጅግ ጠቃሚ እና አስፈላጊ በመሆኑ ነው በማለት፣ በባሕሬን የብሔራዊ መገናኛዎች አማካሪ ወ/ሮ ኒቬዲታ ዳድፋሌ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ገልጸዋል።

03 November 2022, 16:59