ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በባሕሬን ከብጹዕ ወቅዱስ በርተሎሜዎስ ጋር በተገናኙበት ወቅት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በባሕሬን ከብጹዕ ወቅዱስ በርተሎሜዎስ ጋር በተገናኙበት ወቅት   (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለዩክሬን ሰላም ከብጹዕ ወቅዱስ በርቶሎሜዎስ ጋር በጸሎት እንደሚተባበሩ ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ረቡዕ ኅዳር 21/2015 ዓ. ም. ካቀረቡት ሳምንታዊ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ በመቀጠል በዛሬው ዕለት ተከብሮ የዋለውን የቁስጥንጥንያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ባልደረባ የቅዱስ እንድርያስ ዓመታዊ በዓል የሚከበርበት ዕለት መሆኑን በማስታወስ ለፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ በርተሎሜዎስ መልካምን ተመኝተው፣ ለቤተ ክርስቲያን አንድነት እና ከጦርነት ነጻ የሆነ ዓለም እንዲኖር በማለት ጸሎት አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የስምዖን ጴጥሮስ ወንድም እና የቁስጥንጥንያ ቤተ ክርስቲያን ጠባቂ የቅዱስ እንድርያስን ዓመታዊ በዓል ቤተ ክርስቲያን ባከበረችበት በዛሬው ዕለት፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በዛሬው ዕለት ካቀረቡት የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ በመቀጥል ባቀረቡት የሰላምታ ንግግር፣ “ለውድ ወንድሜ” ላሏቸው ለብጹዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ በርተሎሜዎስ ቀዳማዊ እና ለመላዋ የቁስጥንጥንያ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን” ያላቸውን ልዩ ፍቅር ገልጸው፣  እንደተለመደው የቅድስት መንበር ልዑካን ቡድን በበዓሉ ላይ ለመገኝት መጓዙን ገልጸዋል።

የቅዱሳን ወንድማማቾች፣ የቅዱስ ​​ጴጥሮስና የቅዱስ እንድርያስን አማላጅነት በጸሎት የጠየቁት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ቤተ ክርስቲያኗ በቅርብ ጊዜ አንድነቷን እና ሰላሟን ሙሉ በሙሉ ተቀዳጅታ እንድትደሰት፣ መላውን ዓለም በተለይም በአሁኑ ወቅት በጦርነት ስቃይ ውስጥ የምትገኝ ዩክሬንን በማሰብ በጸሎትም የሚያስታውሷት መሆኑን ገልጸዋል።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በቅድስት መንበር ልኡካን በኩል ለቁስጥንጥንያው ፓትርያርክ ለብጹዕ ወቅዱስ በርተሎሜዎስ ቀዳማዊ በላኩት መልዕክት፣ በኢየሱስ ክርስቶስ በሚያምኑ ሁሉ መካከል ያለውን ግንኙነት በሙላት ለመመለስ የእያንዳንዱ ክርስቲያን የማይሻር ቃል ኪዳን መሆኑን ገልጸው፣ የክርስቲያኖች አንድነት የእግዚአብሔር ፈቃድ ብቻ ሳይሆን በዛሬው ዓለም ቅድሚያ የሚሰጠው አስቸኳይ ጉዳይ መሆኑን አስረድተዋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለብጹዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ በርተሎሜዎስ ቀዳማዊ በላኩት መልዕክት፣ የሮም ቤተ ክርስቲያን እና የቁስጥንጥንያ ቤተ ክርስቲያን በዓመታዊ በዓሎቻቸው መገናኘታቸው የአንድነት እና የትስስር ጥልቀት መግለጫ እና የተስፋ ምልክት መሆኑን ገልጸው፣ ኅብረታቸው ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ጥልቅ መሆኑን ተናግረዋል። 

ስምምነቶችን መፈራረም ብቻ ሳይሆን ለአብ ፈቃድ ታማኝ መሆን

ለቅዱስ ሲኖዶስ እና በቅዱስ ጊዮርጊስ ፓትርያርካዊ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የመስዋዕተ ቅዳሴውን ጸሎት ለሚሳተፉ ቀሳውስትና ምእመና ጭምር ሰላምታቸውን የላኩት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ በሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት መካከል የተፈጠረውን ልዩነት መነሻ በማድረግ ታሪካዊና ሥነ-መለኮታዊ ምክንያቶች ላይ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶ ቢሠራም፣ የጋራ ጥናቱ ሊቀጥልና ሊዳብር እንደሚገባ እንዲሁም በእውነተኛ ውይይት እና የእርስ በእርስ ግልጽነት ላይ የተመሠረተ ሊሆን እንደሚገባ፣ በተፈረሙት ስምምነቶች ብቻ ሳይወሰን ለእግዚአብሔር ፈቃድ ታማኞች በመሆንና በመንፈስ ቅዱስ በመመራት በክርስቲያኖች መካከል ያለውን አንድነት ወደነበረበት ለመመለስ እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል።

በሃይማኖቶች መካከል የሚደረግ ውይይት ቁርጠኝነት

ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እና የቁስጥንጥንያ ፓትርያርካዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን “ለሰው ልጅ የጋራ ጥቅም” ሲሉ በበራካታ ዘርፎች በጋራ እየሠሩ እንደሚገኙ ይታወቃል። የዚህ ትብብር ፍሬ ከሆኑት መካከል አንዱ ሃይማኖታዊ ውይይት ሲሆን፣ በተለይም ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በቅርቡ በባሕሬን ከብጹዕ ወቅዱስ በርተሎሜዎስ ጋር ያደረጉትን ስብሰባ በምስጋና አስታውሰው፣ ግጭቶችን እና ሁሉንም ዓይነት ብጥብጦችን ለማሸነፍ የሚደረገው ውይይት እና ግንኙነት ብቸኛው መንገድ መሆኑን በድጋሚ ተናግረዋል።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በመጨረሻም መሲሑን በሕይወታችን ውስጥ እንድንፈልግ እና በዙሪያችን ላሉ ሁሉ እርሱን በደስታ መመስከርን ቅዱስ እንድርያስ ያስተምረን” በማለት ሳምንታዊ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸውን ለመከታተል በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙ የስፔን ቋንቋ ተናጋሪ ምዕመናን መልዕክት አስተላልፈዋል።

30 November 2022, 16:40