ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከጋዜጠኞች በኩል ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከጋዜጠኞች በኩል ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል  (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ጦርነትን ከጀመሩት ጋር መወያየት አስቸጋሪ ቢሆንም ሊቀር እንደማይገባ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በካዛኪስታን ዋና ከተማ ኑር-ሱልጣን ከመስከረም 3 – 5/2015 ዓ. ም. ያደረገቱን የሦስት ቀናት ሐዋርያዊ ጉብኝት ፈጽመው ወደ ቫቲካን ተመልሰዋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በመካከለኛው እስያ አገር ካዛኪስታን ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ቀዳሚ ዓላማ በአገሪቱ ዋና ከተማ ኑር-ሱልጣን የተካሄደውን 7ኛው የዓለም ሃይማኖቶች እና ባሕላዊ እምነቶች የመሪዎች ጉባኤን ለመካፈል መሆኑን የጉብኝታቸው መርሃ ግብር ማስታወቁ ይታወሳል። ቅዱስነታቸው በካዛኪስታን ያደረጉትን 38ኛ ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ፈጽመው ወደ ቫቲካን ሲመለሱ በጉዞአቸው ወቅት ከጋዜጠኞች በኩል ለቀረቡላቸው የተለያዩ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

"የሰላምና የአንድነት መልዕክተኞች" የሚል መሪ ሃሳብ ያለውን ጉባኤ የተካፈሉት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ "በመንኮታኮት ላይ ባለው የምዕራባውያን ሕዝባዊነትን፣ የፖለቲካ ሂደቶችን ከእሴቶች መጀመር እንደሚያድፈልግ እና ከሕዝባዊት ቻይና ጋር የሚደረገውን ውይይት በትዕግስት ማካሄድ እንደሚፈልጉ ለጋዜጠኞች አብራርተዋል። በዩክሬን እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ያስታወሱት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ እራስን ከጦርነት ጥቃት ስለ መከላከል መብት እና ሕገወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውን በማስመልከት ሃሳባቸውን ገልጸዋል። የሕዝቦችን እሴቶች፣ ምኞቶች እና ስሜቶች አደጋ ውስጥ የከተተውን የምዕራቡ ዓለም ፖለቲካን ያስታወሱት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ በጀርመን ያለውን ሁኔታ አስመልክተው በሰጡት አስተያየት፣ ቤተ ክርስቲያን የሚያስፈልጋት ከሁሉ አስቀድሞ ሐዋርያዊ አገልጋዮች እንጂ የእረኝነት ዕቅድ አለመሆኑን አስረድተዋል።

ካዛኪስታ በሰላሳ ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ ዕድገቶችን እንዳስመዘገበች የገለጹ ቅዱስነታቸው፣ አሥራ ዘጠኝ ሚልዮን ሕዝብ ያላት ካዛክስታን በመልካም የዕድገት ጎዳና ላይ እንደምትገኝ፣ ዕድገትን የምትመኝ እና አኩሪ ባሕል ያላት አገር መሆኗን ተናግረዋል። ካዛኪስታን ጠንካራ የሕዝቦች ምክር ቤት ያላት መሆኑን የገለጹት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ይህም አርቆ አሳቢነት እና በተለይ ከማኅበራዊ ሕይወት የተገለሉትንም ጭምር ተሳታፊ የሚያደርጋቸው መሆኑን በማስረዳት ባሁኑ ጊዜ በዓለማችን ውስጥ የሚስተዋሉ ተራማጅ ፅንሰ-ሀሳቦ ለሐይማኖታዊ እሴቶች ዋጋ እንደማይሰጡ ገልጸዋል። ካዛኪስታን ይህን ርዕዮተ ዓለም የምትከተል አገር አይደለችም ብለው፣ ከዚህ ጋር ሰባት የዓለም ሃይማኖቶች እና ባሕላዊ እምነቶች መሪዎች ጉባኤዎችን በማስተማገዷ ልትኮራ ይገባል ብለዋል።

በጦርነት ወቅት እራስን መከላከል ፖለቲካዊ ይዘት ቢኖረውም ሥነ-ምግባርን የሚመለከት በመሆኑ ሥነ-ምግባዊ ግዴታዎችን ማክበር እንደሚባ ተናግረዋል። እራስን ከጥቃት መከላከል ሕጋዊ ብቻ ሳይሆን የሀገር ፍቅር መግለጫም ጭምር ነው ያሉት ቅዱስነታቸው፣ እራስን ከጥቃት ወይም ከአደጋ የማይከላከል እራሱን የማይወድ መሆኑን አስረድተዋል። ከብዙ ዓመታት ጀምሮ ስለ ሰላም ይወራል ያሉት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከተመሠረተ ከሰባ ዓመት ጀምሮ ስለ ሰላም ሲያወራ እንደቆየ፣ በብዙ መድረኮች ስለ ሰላም ሲነገር መቆየቱን አስታውሰዋል። በጦርነት ላይ የሚገኙ አገራት መኖራቸውን ቅዱስነታቸው አስታውሰው፣ በዩክሬን እና በሩሲያ መካከል እየተካሄደ ያለው ጦርነት፣ በአዘርባጃን እና በአርመንያ መካከል፣ አሥር ዓመታትን ያስቆጠረው የሶርያ ጦርነት አስታውሰው፣ በአፍሪካ ቀንድ በደቡብ ኤርትራ፣ በሰሜን ኢትዮጵያ እና በሰሜን ሞዛምቢክ በመካሄድ ላይ ያሉ ጦርነቶችን አስታውሰው፣ በምያንማር ሰላምን ያጣውን የሮሂንጊያ ሕዝብ አስታውሰዋል።

“ጦርነትን ከከፈቱት መንግሥታት ጋር የሚደረገውን ውይይት መረዳት ሁል ጊዜ አስቸጋሪ እንደሆነ አምናለሁ” ያሉት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣  አስቸጋሪ ቢሆንም መቅረት እንደሌለብት፣ መፍትሄው የሚገኘው ከውይይት በመሆኑ፣ በውይይት አማካይነት ሁል ጊዜ ነገሮችን መለወጥ እንደሚቻል እና ሌላ አመለካከት፣ ሌላ ትኩረት የሚንሰጥበት ዕድል በመኖሩ ለውይይት ዕድል መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል። በጦርነትም ይሁን በሌሎች አለመግባባቶች ከየትኛውም ሃይል ጋር ውይይት ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ ጥላቻ ውስጥ የሚገኙ ሁለት ወገኖች በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ ቀርበው ውይይት ማድረግ ከባድ ቢሆንም ምን ጊዜም ቢሆን ውይይት ሊኖር ይገባል ብለዋል።

ምዕራባውያን የተሳሳተ መንገድ መውሰዳቸዋን የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ በማኅበራዊ ፍትህ ትንሽ የዳበሩ አገራት እንዳሉ ገልጸው፣ የሜዲትራኒያ ባሕር እና ምዕራቡ ዓለም ወደ ትልቁ የሰው ልጅ መቃብር ሥፍራነት መቀየራቸውን ገልጸዋል። የሕዝቦችን እሴቶች፣ ምኞቶች እና ስሜቶች አደጋ ውስጥ የጣለውን የምዕራቡ ዓለም ፖለቲካ ሁኔታን ያስታወሱት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ምዕራባውያን ሌሎችን ሕዝቦች ለመርዳት ዝግጁ አለመሆናቸውን ገልጸው፣ እያሽቆለቆለ ያለው የአውሮፓ ኅብረት መሥራች አባቶች እሴት ከወደቀበት ሊነሳ ይገባል ብለዋል።

የትውልድን እና የአገሩን እሴቶችን ለመንከባከብ የቆመ ፖለቲከኛ ከባድ እና አስቸጋሪ መንገድ እንደሚጓዝ ቅዱስነታቸው ተናግረው፣ አንድ ፖለቲከኛ የሕዝብን አደራ የሚቀበለው ለግል ጥቅም ምቾት አለመሆኑን ገልጸዋል። ፓለቲካ  የተከበረ ጥሪ እንደሆነ የገለጹር ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ፖለቲከኞቻችን የሕዝብን አደራ ከልብ ተቀብለው በብቃት እንዲወጡ ልንረዳቸው ይገባል ብለዋል። ሕዝብን የማይጠቅም፣ መንግሥትን የሚያዋርድ እና አገርን ለድህነት የሚዳርግ ዝቅተኛ የፖለቲካ አካሄድ ሊኖር አይገባም ብለው፣ ዛሬ በአውሮጳ ሀገራት ያለው የፖለቲካ ችግር የሕዝብ ቁጥር መቀነስ፣ የኢንዱስትሪ ልማት፣  የተፈጥሮ ልማት ችግር መኖሩን ጠቁመው፣ አውሮፓ ይሁን ሌሎች አህጉራት ወይም አገራት ከሌሎች ክፍሎች ልምዶችን ለመቅሰም ክፍት እና ዝግጁ ሊሆኑ ይገባል ብለዋል።

ሕዝባዊት ቻይናን ለመረዳት ዘመን እንደሚጠይቅ የገለጹት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ቻይና በአስተሳሰብ የበለፀገች በመሆኑ ትንሽ የተሳሳተ ከሆነ በርካታ ሀብቶችን ልታጣ እንደሚትችል ገልጸው፣ የቻይና መንግሥት ሃሳብ በሚገባ ለመረዳት የውይይት መንገድ መምረጣቸውን ገልጸዋል። በቫቲካን እና በቻይና መካከል በመደረግ ላይ ያለው የሁለትዮሽ ግንኙነት አዝጋሚ ቢሆንም በጥሩ ደረጃ ላይ መሆኑን አስረድተዋል። በርካታ ሚሲዮናውያን ወደ ቻይና ሄደው ጠቃሚ ልምዶችን እንደቀሰሙ ሁሉ እንደዚሁም ለከፍተኛ መንፈሳዊ ትምህርት ከቻይና በርካታ ካኅናት እና ምዕመናን ወደ እውሮፓ በመምጣት ልምዶችን በመቅሰም ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል። በሕዝባዊት ቻይና እና በቫቲካን መካከል የሚደረግ ውይይት በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ገልጸው፣ በቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ በብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን የሚመራ የጋራ ምክር ቤት መኖሩን ገልጸው፣ በሁለቱ ወገኖች የሚደረግ ውይይት አዝጋሚ ቢሆንም ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻሎች መኖራቸውን አስረድተዋል።

በደቡብ አሜሪካ አገር ኒካራጓ፣ በመንግሥት እና በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን መካከል ውይይት እየተካሂደ መሆኑን ያስታወቁት ቅዱስነታቸው፣ ይህ ማለት ግን መንግሥት የሚያደርገውን ሁሉ ማጽደቅ ወይም ሁሉንም ነገር መቃወም ማለት እንዳልሆነ ገልጸው፣ በውይይት በመታገዝ ችግሮችን መፍታት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። በአገሪቱ በምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን እና በመንግሥት መካከለ ችግር መኖሩን የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ በኒካራጓ ውስጥ ሐዋርያዊ ተልዕኮአቸውን በመፈጸም ላይ የሚገኙት የእናት ቴሬዛ ማኅበር እህቶች አገልግሎታቸውን በሰላማዊ መንገድ እያከናወኑ እንደሚገኙ ገልጸው፣ የአገሩ ሕዝብ ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን ከልብ የሚፈልግ መሆኑን አስረድተዋል። በአንዳንድ አገራት ለማካሄድ ያቀዷቸውን ሐዋርያዊ ጉብኝቶች ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ በደቡብ አሜሪካ፣ በደቡብ ሱዳን እና በኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፓብሊክ ሐዋርያዊ ጉብኝት ለማካሄድ ምኞት እንዳላቸው ገልጸው፣ የጤና ሁኔታቸው የሚፈቅድ ከሆነ አገራቱን ለመጎብኘት ተስፋ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

በካዛኪስታን ዋና ከተማ ኑር-ሱልጣን በመሩት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ በተገኙት ካቶሊካዊ ምዕመናን መደሰታቸውን ገልጸው፣ ምዕመናኑ በእምነታቸው ደስተኞች  እና ቀናተኞች መሆናቸውንም አስታውሰዋል። በካዛኪስታን ውስጥ በክርስቲያን እና በሙስሊም ማኅበረሰብ መካከል መልካም ግንኙነት መኖሩን ገልጸው፣ ይህም በካዛኪስታን ብቻ ሳይሆን በሰሜን አፍሪካዊቷ አገር ሞሮኮ እና በሌሎች አገራትም በሁለቱ ማኅበረሰብ መካከል መልካም የጋራ ውይይት እየተካሄደ መሆኑን አስረድተዋል። አንዱ ሌላውን ካለማወቅ የተነሳ በሃይማኖቶች መካከል አለመግባባቶች እንደሚፈጠሩ የገለጹ ቅዱስነታቸው፣ ስለ ራስ ሃይማኖት የሚጨነቁ ከሆነ ስለሌላው ሃይማኖትም መጨነቅ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል። 

የዓለማዊነት መንፈስ እና አንጻራዊነት እምነትን አደጋ ውስጥ ማስገባቱን የተነአገሩት ቅዱስነታቸው፣ ከሁሉ አስቀድሞ እምነታችንን በሚገባ መያዝ እንደሚያፈልግ ገልጸው፣ ቤተ ክርስቲያን ይሁን ሌላ የእምነት ተቋም የቆመለትን ዓላማ ዘንግቶ ከሐዋርያዊ አገልግሎት ይልቅ ስለ ልማት እና ስለ ሐዋርያዊ ዕቅዶች ይበልጥ የሚያስብ ከሆነ ሰውን ለድነት መጥራት አይችልም ብለዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን የመሠረታት በፖለቲካ መሪዎች ሳይሆን በሐዋርያዊ አገልጋዮች እንደሆነ ገልጸው፣  ቤተ ክርስቲያን ወደ ፊት ልትራመድ የቻለችው በአላዋቂዎች እንደሆነና፣ አሥራ ሁለቱ ሐዋርያት አንዱ ከሌላው የበለጠ አላዋቂ እንደነበሩ አስረድተዋል። የዘማናዊነት ጉዳይ ሳይሆን በእርግጥ አንድ ሰው እራሱን አንዳንድ ዘዴዎችን በመጠቀም ማዘመን እንዳለበት ገልጸው፣ ነገር ግን ሐዋርያዊ አገልጋይ የፍቅር፣ የርኅራሄ እና የአንድነት ልብ ከሌለ ምንም ዓይነት የሐዋርያዊ እረኝነት አገልግሎት ውጤታማ ሊሆን የማይችል መሆኑን ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በካዛኪስታን ያደረጉትን 38ኛ ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ፈጽመው ወደ ቫቲካን ሲመለሱ ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ አስረድተዋል።

17 September 2022, 18:20