ፈልግ

የእህት ኮፒ ዕረፍት የሚገልጽ ጨርቅ ከሞዛምቢክ የእህት ኮፒ ዕረፍት የሚገልጽ ጨርቅ ከሞዛምቢክ  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ የእህት ኮፒ ሞት የሚያስታውስ ጨርቅ ከሞዛምቢክ ተልኮላቸዋል

የሬዲዮ ኮፕ ጋዜጠኛ ኤቫ ፈርናንዴዝ ቅዱስነታቸው ወደ ካዛክስታን በሚያደርጉት ጉዞ ላይ ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሴቶች ሕይወት የሚያመለክት ጨርቅ በስጦታ ማቅረቧ ታውቋል። ስጦታው ጳጉሜ 1/2014 ዓ. ም. ታጣቂዎች በሰነዘሩት ጥቃት ሕይወቷን ያጣችውን እህት ማርያ ኮፒን ለማስታወስ እንዲሁም በሁከትና ብጥብጥ የቆሰለችው ሞዛምቢክን ቅዱስነታቸው በጸሎት እንዲያስታውሷት በመጠየቅ ከቅዱስ ኮምቦኒ ማኅበር ሚሲዮናዊ መነኮሳት የተበረከተ መሆኑ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ስጦታውን የተቀበሉት ወደ ካዛክስታን በሚያደርጉት ጉዞ ወቅት አብረዋቸው ለተጓዙት ጋዜጠኞች ሰላምታቸውን ባቀረቡበት ወቅት መሆኑ ታውቋል። ለቅዱስነታቸው የተበረከተው ጨርቅ በሞዛምቢክ ውስጥ የተለመደ እና “ካፑላና” ተብሎ የሚጠራ ሲሆን በሌሎች በርካታ የአፍሪካ ሕዝቦች፣ በተለይ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት ለልብስነት የሚጠቀሙት የሕይወት ምሳሌ መሆኑ ተነግሯል። ስጦታውን ልዩ የሚያደርገው በመሣሪያ ታጣቂዎች ጥቃት ጳጉሜ 2/2014 ዓ. ም. በሞዛምቢክ ቺፔኔ ግዛት ውስጥ ሕይወቷን ያጣችውን የቅዱስ ኮምቦኒ ማኅበር መነኩሲት እህት ማሪያ ኮፒን ለማስታወስ በመሆኑ ነው ተብሏል።

የሕይወት ምልክት ነው

ነጭ ንድፍ ያለበትን ጥቁር ጨርቅ ለር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በስጦታነት ያቀረበችው የስፔን ራዲዮ ኮፕ ዘጋቢ ኤቫ ፈርናንዴዝ መሆኗ ታውቋል። ዘጋቢዋ በስጦታነት ካቀረበችው ጨርቅ ጋር የጨርቁን ትርጉም ከሚገልጽ ጽሑፍ ጋር ለቅዱስነታቸው ያቀረበች ሲሆን፣ ከጽሑፉ ለመረዳት እንደተቻለው ጨርቁ አዲስ የተወለዱ ሕፃናትን ለመጠቅለል ወይም ከእናታቸው ጀርባ ለማዘል የሚጠቅም መሆኑ ታውቋል።

ከቅዱስ ኮምቦኒ ማኅበር እህቶች የቀረበ ስጦታ ነው

ለቅዱስነታቸው በስጦታ መልክ የቀረበው ጨርቅ ከጨርቅነት በላይ መሆኑ ሲነገር፣ የመላው ሞዛምቢክ ሕዝብ ሕይወት የሚወክል እንደሆነ ተገልጿል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በንግግራቸው “የከተማ ዳርቻ እህቶች” በማለት የገለጻቸው በእነዚህ እህቶች አገልግሎት በመደነቅ መሆኑ ታውቋል።

የቅዱስ ኮምቦኒ ማኅበር እህቶች ስጦታቸውን በኤቫ ፈርናንዴዝ በኩል ቅዱስነታቸውን እንዲደርሳቸው መወሰናቸውን ገልፀው፣ “የሞዛምቢክ ሕዝብ ሕይወት በአሁኑ ጊዜ እንክብካቤ ሊደረግለት እንደሚያስፈልግ፣ በጸሎታቸው እንዲደግፏቸው፣ የሞዛምቢክ ሕዝብ ፍትህ፣ አንድነት እና አለኝታ የሚያስፈልገው መሁኑን ገልጸዋል። በሞዛምቢክ እ. አ. አ. ከ2017 ጀምሮ በተለይም በካቦ ዴልጋዶ አካባቢ የተለያዩ ጂሃዲስቶች እና አሸባሪ ቡድኖች ወደ 800,000 የሚጠጉ ሰዎችን ለስደት ያበቃቸውን ሁከትና ብጥብጥ መፈጸማቸው ይታወሳል። በእውነቱ በእህት ኮፒ ግድያ ከፍተኛ ሐዘን ያጋጠማቸው መሆኑን እና በአረመኔያዊ ወረራ በጣም መደንገጣቸውን ገልጸዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መስከረም 1/2015 ዓ. ም. ባቀረቡት የመልዓከ እግዚአብሔር ጸሎታቸው “የእህት ማሪያ ኮፒን ምስክርነት ለክርስቲያኖች እና ለመላው የሞዛምቢክ ሕዝብ ብርታትን እና ድፍረትን ሊሰጥ ይችላል” ማለታቸው ይታወሳል።

ያለ ፍርሃት የሚሄድ ተልዕኮ

"የእህታችን ሞት በሞዛምቢክ እና በዓለም ውስጥ የሚገኙ የሚስዮናዊነት ሕይወትን ያድሳል" በማለት የቅዱስ ኮምቦኒ ሚሲዮናውያን እህቶች ማኅበር አባላት በመልዕክታቸው ገልጸዋል። እህቶቹ በማከልም “በእህታችን ማሪያ ዴ ኮፒ ግድያ እና በቺፔን ተልዕኮ ላይ ለተሰነዘረው ጥቃት ታላቅ ሐዘን ይሰማናል” ብለው “እኛ የቅዱስ ኮምቦኒ ሚስዮናውያን እህቶች በጸሎት፣ በመተሳሰብ እና በመተባበር አንድነታችንን ለመቀጠል ያለንን ቁርጠኝነት ማረጋገጥ እንፈልጋለን” ብለዋል። በዚህች ምድር ያሉ የሚስዮናውያን እርምጃ በዓመፅ ምክንያት ሊቋረጥ እንደማይችን አስረድተው፣ የእህት ማርያ ዴ ኮፒ ሞት በሞዛምቢክ እና በመላው ዓለም የሚገኙ የሚስዮናዊነት ሕይወትን የሚያድስ እንደሚሆን በመልዕክታቸው አረጋግጠዋል።

14 September 2022, 17:17