ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፥ “ክርስቲያኖች ለሰው ልጆች ያላቸውን ርኅራሄ ማሳደግ ይገባል!”
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን የሰላምታ እና የወዳጅነት መልዕክት በጣሊያን ሪሚኒ ከተማ ከነሐሴ 14-19/2014 ዓ. ም. ድረስ የሚካሄድ 43ኛ የሕዝቦች ወዳጅነት ስብሰባ አስተባባሪ እና የሪሚኒ ከተማ ጳጳስ ለብጹዕ አቡነ ፍራንችስኮ ላምቢያሲ አስተላልፈዋል። በሕዝቦች መካከል ወዳጅነት እንዲጎለብት የሚያግዝ ዓመታዊ ጉባኤው ከ1972 ዓ. ም. ጀምሮ በየዓመቱ ነሐሴ ወር ውስጥ በሪሚኒ ከተማ ሲካሄድ መቆየቱ ሲታወቅ፣ የዘንድሮ ስብሰባ መሪ ሐሳብም “ለሰው ልጅ የሚሰጥ ፍቅር” የሚል እንደሆነ ታውቋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለስብሰባው ተካፋዮች ዓርብ ነሐሴ 13/2014 ዓ. ም. በላኩት መልዕክት የእግዚአብሔር አገልጋይ ሉዊጂ ጉይሳኒ የተወለዱበትን መቶኛ ዓመት አስታውሰው፣ ስብሰባው የኢየሱስ ክርስቶስን የምሥራች ቃል ወደ በርካታ ሰዎች ለማድረግ የሚያነሳሳ ሐዋርያዊ ቅንዓት ያለው መሆኑን አስታውቀዋል።
የዘመናችን ደካማነት
ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የዘመናችንን ደካማነት ባሰላሰሉበት መልዕክታቸው፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ያለውን ፍቅር ለማሳየት ታሪክ ችላ ያለበት፣ በዚህም የሰው ልጅ የመዳን ዕድል እንደሌለው፣ ምሕረትን ይቅርታን በሚያደርግ በኢየሱስ ክርስቶስ አባታዊ ፍቅር ጥርጣሬ ውስጥ የገባበት ጊዜ መሆኑንም ገልጸዋል። ይህም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት የሰው ልጅ ብቸኝነትን ያየበት፣ ጦርነት እና አመጽ የሚያስከትለውን አደጋ ለማምለጥ ሲል ሁሉን ነገር እርግፍ አድርጎ የተውበት የአሳዛኝ ተሞክሮ ገጽታ መሆኑን አስረድተዋል። ቅዱስነታቸው የደጉ ሳምራዊ ምሳሌን በመጥቀስ፣ የሰው ልጅ ዛሬ ላይ ላጋጠመው መከራ መፍትሄ እንደሚሆንለት ተስፋ የሚያደርገው ከሌሎች ሰዎች የሚደረግለት የመጠለያ፣ የምግብ እና የሌሎች ሰብዓዊ ዕርዳታዎችን እንደሆኑ ገልጸዋል።
ደጉ ሳምራዊ
ለእያንዳንዱ ሰው የሚሰጥ የፍቅር አገልግሎት ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ የሚቀርብ የደጉ ሳምራዊ መርህ እንደሆነ ቅዱስነታቸው ገልጸው፣ ይህም ከስብሰባው ጭብጥ ጋር የሚስማማ መሆኑን ተናግረዋል። ካለን መካከል ለሌሎች ማካፈል ለጋስነት ብቻ እንዳልሆነ የገለጹት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “ከማኅበረሰቡ ውስጥ ለተገለሉት ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን የፍቅር አገልግሎትን እንድናበረክት ኢየሱስ ክርስቶስ በልባችን ውስጥ የሚያሳደረው የበጎነት ተግባር መሆኑን አስረድተዋል። ይህ የኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር፣ እያንዳንዱ ሰው ለሌሎች ያለውን አመለካከት በማሳደግ ገደብ የሌለውን ፍቅር የሚገልጽበት እንደሆነ አስረድተው፣ ራስ ወዳድነትና ወገንተኝነት በግለሰቦችና በአገሮች መካከል የነገሠ በሚመስልበት በዛሬው ዓለም ውስጥ በዙሪያችን ካሉት ጋር መከባበር፣ በጎነትን ማሳየት፣ ልዩነትን አስወግዶ እርስ በእርስ መቀራረብ አስቸጋሪ እንደሚሆን ገልጸዋል።
ወደ ወንድማማችነት የሚወስድ መንገድ
"የወንድማማችነት መንገድ ያልተመቻቸ፣ በማኅበረሰብ ውስጥ የሚገኙትን ብዙ መንፈሳዊ በረሃዎች ማቋረጥን እንደሚጠይቅ የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቤነዲክቶስ 16ኛ፣ በበረሃ ሕይወት ውስጥ ለኑሮ የሚያስፈልጉ ጠቃሚ ነገሮችን እንደገና ማግኘት እደሚቻል፣ በበረሃ ሕይወት ውስጥ ተስፋን በማድረግ ወደ ተስፋይቱ ምድር የሚወስደውን መንገድ የሚጠቁሙ የእምነት ሰዎች ያስፈልጋሉ” ማለታቸውንም አስታውሰዋል። የወንጌል ደስታ በሚለውን ሐዋርያዊ ቃለዕዳናቸው ውስጥ በቁ. 199 ላይ፣ "ቁርጠኝነታችን እና እንቅስቃሴያችን የዕርዳታ ሥራ ዕቅድ ብቻ አይደለም” ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ይልቁንም፣ የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ከሁሉም በላይ ሌላውን ሰው ከራስ ጋር አንድ አድርጎ መቁጠርን፣ በፍቅራዊ አመለካከት ለሰዎች ደኅንነት የሚያነሳሳ የደግነት ውጤት መሆኑን አስረድተዋል።
ከሌሎች ሰዎች ጋር የሚኖረን ማኅበራዊ ወዳጅነት
ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ “አንድ ሰው ብቻውን የሚጓዝ ከሆነ ራሱን ማወቅ እንደማይችል፣ ከሌሎች ሰዎች ጋር መገናኘት አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸው፣ የደጉ ሳምራዊ ምሳሌ፣ የእኛ መኖር ከሌሎች ጋር ያለንን ቁርኝት፣ እና ጋር ማንነታችንን በማወቅ ፍሬን ለማፍራት ቅድመ ሁኔታን የሚያመቻች መሆኑን አስረድተዋል።“እግዚአብሔር ለእኛ ሲል ራሱን አሳልፎ የሰጠው እኛም ደግሞ ራሳችንን ለሌሎች አሳልፈን እንድንሰጥ ስለሆነ፣ የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር የተቀበለውን የደግነት ስጦታ ለሌሎች ማካፈል ይኖርበታ” ብለው፣ ይህን የማያደርግ ከሆነ በሕይወት መኖር፣ ማደግ እና እርካታን ማግኘት አይችልም በማለት ቅዱስነታቸው አስረድተዋል። ኢየሱስ ክርስቶስን በመምሰል ከሌሎች ጋር የሚካፈሉት የጸጋ ስጦታ ፍሬ ማኅበራዊ ወዳጅነትን እና ወንድማማችነት በማሳደግ የልዩነት ግድግዳዎችን በማፍረስ ከሌሎች ጋር ለመገናኘት የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል።
የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ጥሪ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በሰሜን ጣሊያን ሪሚኒ ከተማ ከነሐሴ 14-19/2014 ዓ. ም. ድረስ ለሚካሄደው 43ኛው የሕዝቦች ወዳጅነት ስብሰባ በላኩት መልዕክታቸው፣ ለሁሉ ሰው ጥቅም ሲባል መላው ክርስቲያን ማኅበረሰብ፣ የእያንዳንዱ ሰው ክብር ምንጭ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት እንዲተባበር ጋብዘው፣ በሕዝቦች መካከል ያለውን ወንድማማችነትን ለማሳደግ በሚደረግ ጥረት ላይ እንዲተባበሩ እና በዓለም ውስጥ ለሰው ልጅ ያላቸውን ፍቅር እንዲያዳብሩ አሳስበዋል።
እ. አ. አ. በ 2018 ዓ. ም. በላትቪያ የተካሄደውን የክርስቲያኖች አንድነት ስብሰባን በማስታወስ፣ የወንጌልን መልዕክት የማናስተጋባ ከሆነ ከርህራሄ የተወለደው ደስታ፣ ከመተማመን የተገኘው ፍቅር እና ይቅር ከመባባል የሚገኝ የእርቅ ፍላጎት የሚጠፋ መሆኑን አሳስበዋል። የወንጌል ዝማሬ በየቤታችን፣ በየአደባባዮች፣ በሥራ ቦታዎች፣ በፖለቲካ እና በንግድ ተቋሞቻችን ውስጥ የማይሰሙ ከሆነ፣ የእያንዳንዱ ሰው ሰብዓዊ ክብርን ለማስጠበቅ የሚደረግ ጥረት ፈተና ውስጥ እንደሚወድቅ አስረድተዋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው ማጠቃለያ ዘንድሮ በጣሊያን ሪሚኒ ከተማ ከነሐሴ 14-19/2014 ዓ. ም. ድረስ የሚካሄድ 43ኛ የሕዝቦች ወዳጅነት ስብሰባ ተሳታፊዎች ጥሪያቸውን በፈቃደኝነት እንደሚቀበሉ እና ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጋር በሕዝቦች መካከል ባለው የወዳጅነት ጎዳና ላይ በኅብረት እንደሚጓዙ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።