ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ 'እምነት ህመምን ያበራል እና እንደገና ለመገንባት ጥረት ያደርጋል' ማለታቸው ተገለጸ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ወደ መካከለኛው የጣሊያን ግዛት በመጓዝ በእዚያው የምትገኘውን ላኲይላ ከተማ መጎብኘታቸው የሚታወስ ሲሆን ከ13 ዓመታት በፊት በደረሰው ከባድ የመሬት መንቀጥቀጥ 309 ሰዎች በእዚያው ከተማ ሕይወታቸው ማለፉ የሚታወስ ሲሆን ቅዱስነታቸው በእዚያው ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ነዋሪዎቹ በእግዚአብሔር በመተማመን ሕይወታቸውን እንዲገነቡ አበረታተዋል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ እሁድ ጠዋት ነሐሴ 22/2014 ዓ.ም ከሮም በስተሰሜን ምስራቅ 100 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የምትገኘውን የመካከለኛው የጣሊያን ከተማ ላኲይላ በጎበኙበት ወቅት ነበር ቅዱስነታቸው ይህንን የተናገሩት።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

እ.ኤ.አ. ሚያዝያ 6 ቀን 2009 እኩለ ሌሊት ላይ በደረሰው የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ሳቢያ የደረሰውን ከፍተኛ አደጋ ለመጎብኘት ወደ እዚያው ቅዱስነታቸው ማቅናታቸው የሚታወስ ሲሆን በወቅቱ ከሲቪል ባለስልጣናት እና ከቤተሰቦቻቸው ጋር በመገናኘት ከአደጋው የተረፉትን ሰዎች ማጽናናት ያሰበ ሐዋርያዊ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል። በወቅቱ ወደ 66,000 የሚጠጉ ሰዎች ቤት አልባ ሆነዋል፣ እና 309 ሰዎች በመሬት መንቀጥቀጡ እና በተከሰቱት ተያያዥ አደጋዎች ሕይወታቸውን ማጣታቸው ይታወሳል።

እሁድ ነሐሴ 22/2014 ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የመሬት መንቀጥቀጡ ከተከሰተ ከአንድ ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ ላኲይላ ጎብኝተው ከነበሩ የቀድሞ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የነበሩት ቤኔዲክት 16ኛን ፈለግ በመከተል ሚያዚያ 28 ቀን 2009 ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ የፈረሰውን የቅዱስ ማክሲሞስ ካቴድራል ፍርስራሽ መጎብኘታቸው ይታወሳል፣ በወቅቱ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ በመሬት መንቀጥቀጥ መለኪያ መሳሪያ ሬክቴል እስኬል 6.3 ማስመዘገቡ ይታወሳል።

በህመም መካከል እምነት እና ክብር

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ለላኲይላ ህዝብ ንግግር ሲያደርጉ ለሟች ቤተሰቦች እና በአደጋው ክፉኛ ለተጎዱት ማህበረሰብ በሙሉ ያላቸውን ቅርበት ገልጿል።

ከተማዋ ከዚያ አሳዛኝ ምሽት በኋላ ያሳየችውን “ታላቅ ክብር” እና የእምነት ምስክርን ቅዱስነታቸው አወድሰዋል የሚከተለውን ብለዋል. . .

"በእኛ በእምነት መንፈሳዊ ንግደት ውስጥ ባሉት ስቃይ እና ድንጋጤዎች እይታችንን በተሰቀለውና በተነሳው ክርስቶስ ላይ ማድረግ ይገባል፣ እሱም በፍቅሩ ህመምንና ሞትን ትርጉም አልባ አድርጎዋቸዋል” ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ አክለውም ኢየሱስ ላኲይላ ከተማ ሰዎች “አንድም እንባ በከንቱ እንዲፈስ የማይፈቅድ ለአብ ክንድ” አደራ ሰጥቷቸዋል ማለታቸው ተገልጿል።

"ሞት ፍቅርን አያፈርስም"

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ለ309 ሟቾቹ ቤተሰቦች ባደረጉት ንግግር የሚወዷቸው እና ከእነርሱ በሞት የተለዩት በሙሉ በእግዚአብሔር መሐሪ ልብ ውስጥ ያርፋሉ ማለታቸው የተገለጸ ሲሆን “ከእነሱ ጋር ያለን ኅብረት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ሕያው ነው ሞት ፍቅርን አያፈርስም" ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በተጨማሪም በከተማው ውስጥ የሚኖሩ ካቶሊኮች "የመታሰቢያ ቤተመቅደስ" የገነቡበትን መንገድ አወድሰዋል።

“ትዝታ የሰዎች ጥንካሬ ነው ይህ ትዝታ በእምነት ሲበራ ሰዎች ላለፉት ጊዜያት እስረኛ ሆነው ለመቆየት አይችሉም፣ ይልቁንም አሁን ባለው የወደፊቱን ጊዜ እየሄዱ ሁልጊዜ ከሥሩ ጋር ተጣብቀው ይራመዳሉ። ያለፉትን ተሞክሮዎች ጥሩ እና መጥፎ ሀብቶችን ማድነቅ እና እምነትን ማዳበር ይችላሉ” ብለዋል።

መንፈሳዊ እና አካላዊ ተሃድሶ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ እንዳሉት አሁንም በላኲይላ ውስጥ ብዙ ሕንፃዎች እንደገና መገንባት አለባቸው ያሉ ሲሆን ነገር ግን አካላዊ ተሃድሶ “በመንፈሳዊ፣ ማህበራዊ እና ባህላዊ መልሶ ግንባታ” ጋር መታጀብ እንዳለበት ነዋሪዎችን አሳስቧል።

“የግል እና የጋራ ዳግም መወለድ የጸጋ ስጦታ ነው እናም በእያንዳንዱ ሰው እና በአንድ ላይ በሚያደርገው ጥረት ያድጋል። በተቋማትና በማኅበራት መካከል፣ በትጋት የተሞላ፣ አርቆ አሳቢ ጥረትን፣ ትብብርን ማጠናከር አስፈላጊ ነው” ሲሉ አክለው ገልጸዋል።

ለአምልኮ ቤቶች እንክብካቤ

ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለላኲይላ ሕዝብ ባደረጉት የተስፋና የበረከት መልእክት እንደ ገለጹት መልሶ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት አብያተ ክርስቲያናት ልዩ ትኩረት እንደሚሹም ያሳሰቡ ሲሆን "በታሪክም ሆነ በባህላዊ መልኩ ብቻ ሳይሆን በማንነታችሁም የማህበረሰቡ ቅርሶች ናቸው" ብሏል። "እነዚያ ድንጋዮች በሰዎች እምነት እና እሴቶች የተሞሉ ናቸው፣ እናም አብያተ ክርስቲያናት ለህብረተሰቡ ህይወት እና ተስፋ መነሳሳትን ይሰጣሉ" በማለት ከተናገሩ በኋላ ቅዱስነታቸው ንግግራቸውን አጠናቀዋል።

28 August 2022, 16:42