ፈልግ

በሊባኖስ ዋና ከተማ የሚገኘው እና በመርዛማ ንጥረ ነገር ፍንዳታ የተቃጠለው የቤይሩት ወደብ በሊባኖስ ዋና ከተማ የሚገኘው እና በመርዛማ ንጥረ ነገር ፍንዳታ የተቃጠለው የቤይሩት ወደብ  (AFP or licensors)

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በቤይሩት ወደብ የተከሰተውን ፍንዳታ ሁለተኛ ዓመት በጸሎት አስታወሱ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዛሬው ዕለት ባቀረቡት ሳምንታዊ ጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምሮአቸው ወቅት በሊባኖስ ዋና ከተማ ቤይሩት ወደብ ከሁለት ዓመት በፊት የተከሰተውን ፍንዳታ በማስታወስ የሊባኖስን ሕዝብ በጸሎታቸው አስታውሰዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው ሳምንታዊ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸውን በጳውሎስ ስድስተኛ አዳራሽ ውስጥ ባቀረቡበት ወቅት፣ በሊባኖስ ከፍተኛ ጉዳትን ያስከተለውን የቤይሩት ወደብ ላይ ፍንዳታን አስታውሰው የአደጋው ሰለባ የሆኑ ቤተሰቦችን እና መላውን የሊባኖስ ሕዝብ በጸሎታቸው በማስታወስ፣ ሕዝቡ በእግዚአብሔር ላይ ባለው እምነት መጽናናትን እንዲያገኝ፣ ፍትሕ እና እውነት ገሃድ እንዲወጣ ጠይቀዋል። ሊባኖስ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እርዳታ በመታገዝ ከደረሰበት ጥፋት ወጥታ ራሷን መልሳ የምትገነባበትን ኃይል እንድታገኝ፣ የተለያዩ ሃይማኖቶች ያሏቸው ማኅበረሰቦች በወንድማማችነት የሚኖሩባት የሰላምና የብዝሃነት ምድር እንድትሆን እና ጥሪዋን በታማኝነት እንድትጠብቅ” በማለት ጸሎታቸውን አቅርበዋል።

ከሁለት ዓመት በፊት ሐምሌ 28/2012 ዓ. ም. በቤሩት ወደብ ላይ ከፍተኛ ፍንዳታ ተከስቶ ለ215 ሰዎች ሕልፈት እና በሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች መቁሰል ምክንያት ሆኖ ማለፉ ያታወሳል። እጅግ ከፍተኛ እንደነበር የሚነገርለት ይህ ፍንዳታው የሰውን ሕይወት ከማጥፋቱ በላይ ለበርካታ ሕንጻዎች፣ አብያተ ክርስቲያናት እና ገዳማት መውደም ምክንያት መሆኑ ይታወሳል። የፍንዳታው መንስኤ በሊባኖስ ዋና ከተማ ቤይሩት ወደብ ላይ ጥንቃቄ የጎደለው መርዛማ ንጥረ ነገር በመፈንዳቱ መሆኑ ታውቋል። ፍንዳታው በተከሰተበት ወቅት የሊባኖስ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በዕርዳታ ለጋሽ ድርጅቷ አማካይነት በአደጋው ለተጎዱት ቤተሰቦች አስቸኳይ ዕርዳታን ማቅረቧ ይታወሳል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስም ለሊባኖስ ሕዝብ ያላቸውን አብሮነት ለመግለጽ፣ በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት በኩል 250,000 ዩሮ የመጀመሪያ እርዳታ በማድረግ በዚያ አስቸጋሪ ወቅት የሊባኖስ ቤተ ክርስቲያንን መርዳታቸው ይታወሳል።

በሐምሌ ወር 2013 ዓ. ም. ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከሊባኖስ አብያተ ክርስቲያናት መሪዎች ጋር በቫቲካን መገናኘታቸውም ይታወሳል። አደጋውን አስመልክተው ባደረጉት ንግግር፣ በዕለቱ በተደረገው የጸሎት እና የአስተንትኖ ቀን ከክርስትና እምነት  መሪዎች ጋር ሆነው የሊባኖስን ተስፋ እና ምኞት፣ የሊባኖስን ሕዝብ ብስጭት እና ድካም በማዳመጥ መጸለያቸው እና በሊባኖስ ውስጥ የደረሰውን ቀውስ ለማሸነፍ ከእግዚአብሔር የተስፋ ስጦታን መለመናቸውም ይታወሳል። ቅዱስነታቸው በዕለቱ ባደረጉት ንግግር፣ ሊባኖስ ከደረሰባት ውድቀት እንድትነሳ እና የ“ትንሳኤ” ጉዞን ማካሄድ እንድትችል ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ተጨባጭ እገዛን እንዲያደርግላት መማጽናቸው ይታወሳል።

03 August 2022, 17:14